ሜታ ተጠቃሚዎቹ ትራምፕን እንዲከተሉ አስገድዷል መባሉን አስተባበለ

የትራምፕ የፌስቡክ ገጽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ማህበራዊ ሚዲያዎች ባለቤት የሆነው ሜታ፣ ተጠቃሚዎቹ በአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ሁነኛ የተባሉ ባለስልጣናትን ይፋዊ ገጽ እንዲከተሉ አስገድዷል መባሉን አስተባበለ።

አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎቹ ተጠቃሚዎች ዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን ከፈጸሙ በኋላ አዲሱን ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕን እንድንከተል ተደርገናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር።

ገጾቹ የሚተዳደሩት በዋይት ሃውስ መሆኑን እና በአዳዲሶቹ ባለስልጣናት እንዲተኩ መደረጋቸውን የሜታ ቃል አቀባይ አንዲ ስቶን አስታውቀዋል።

"በባለፈው ፕሬዝዳንታዊ የሽግግር ወቅትም የተከተልነው ተመሳሳይ አሠራር ነው" ሲሉ በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል በመግለጫው ላይ ጽፏል።

በማህደር የተቀመጡ የገጾቹ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ የፖተስ [የፕሬዚዳንቱ] እና የፍሎተስ [የቀዳማዊት እመቤት] ገጾች ከዚህ ቀደም የጆ ባይደንን እና የጂል ባይደን ስም እና ይፋዊ ምስል የያዙ ነበሩ።

ስቶን አክለውም "እነዚህ መለያዎች ሲቀየሩ ገጾቹን ለመከታተል እና ላለመከተል የሚደረግ ጥያቄ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ ይችላል" ብለዋል።

ትራምፕ ሰኞ፣ ጥር 12/ 2017 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በዓለ ሲመታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን የሚያሳዩ ዓለም ጤና ድርጅት ከመውጣት እስከ ሜክሲኮ ድንበር ላይ ብሔራዊ ድንገተኛ የአደጋ ጊዜ ማወጅ የሚደርሱ የተለያዩ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን እና መመሪያዎችን በፍጥነት ማውጣት ጀምረዋል።

በበዓለ ሲመቱ ወቅት የሜታው አለቃ ማርክ ዙከርበርግ እና የኤክስ ኃላፊ እና በአዲሱ አስተዳደር ውስጥ የአማካሪነት ሚና ያለው ዋና ኢሎን መስክን ጨምሮ በጣም ተደማጭነት ያላቸው የቴክኖሎጂ ቢሊየነሮች ተገኝተዋል።

በ2021 በካፒቶል ሂል የተፈጠረውን ሁከት ተከትሎ "በአመጽ የተሳተፉ ሰዎችን አወድሰዋል" በሚል እገዳ የጣለባቸው ሜታ ላይ ትራምፕ ከፍተኛ ትችት ሰንዝረው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ እና አጋሮቻቸው ከባይደን ልጅ ሃንተር ጋር የተያያዙ አንዳንድ ይዘቶችን ለማፈን ከባይደን አስተዳደር ጋር አብሯል በሚል ኩባንያውን ከመክሰሳቸውም በላይ እና በኮቪድ ወረርሽኝ ዙሪያ ተመሳሳይ ሚና ተጫውቷል ብለዋል። ዙከርበርግ በውሳኔው ተጸጽቻለሁ ብሏል።

በነሐሴ ወር ትራምፕ በመጽሐፍ ላይ እንደጻፉት ከሆነ ዙከርበርግ በ2024ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ለመግባት ከሞከረ ቀሪ ህይወቱን በእስር ቤት ያሳልፋል ብለው ነበር።

ትራምፕ ምርጫ ካሸነፉ ወዲህ ግን ዙከርበርግ ከትራምፕ ጋር በማርአ ላጎ መኖሪያቸው ቤታቸው አብሯቸው ከመመገቡም በላይ ለበዓለ ሲመታቸው አንድ ሚሊየን ዶላር ሰጥቷል።