በቻይና ላይ ታሪፍ መጣልን እንደማይመርጡ ትራምፕ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ላይ ታሪፍ አለመጣልን እንደሚመርጡ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።
በቻይና ታሪፍ ከመጣል በተጨማሪ የሩስያ-ዩክሬን ጦርነት፣ ሰሜን ኮሪያን እና ሌሎችንም ጉዳዮች በሚመለከት
ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ስላላቸው ግንኙነት የተጠየቁት ትራምፕ በቅርቡ ከቻይናው መሪ ጋር ያደረጉትን ውይይት "መልካም" እና "በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ" ሲሉ ገልጸውታል።
ሁለቱ መሪዎች ከኮቪድ በፊት "በጣም ጥሩ ግንኙነት" እንደነበራቸውም ተናግረዋል።
"በጣም ትልቅ ህልም ያላት አገር ናት። እሱም ትልቅ ህልም ያለው ሰው ነው...እንደ ጓደኛዬ ነበር። በጣም ጥሩ ግንኙነት ነበረን" ብለዋል ትራምፕ።
"ቻይና አብዛኛውን ገንዘቧን ከአሜሪካ ታገኛለች። ይህንን ገንዘብ ደግሞ ጦሯን ለመገንባት ትጠቀምበታለች" ሲሉ ቤጂንግ ላይ ታሪፍ ለመጣል የደረሱበትን ውሳኔ ትክክለኛ መሆኑን አሳውቀዋል።
"ከቻይና የሚበልጥ አንድ በጣም ትልቅ ኃይል አለን። እሱም ታሪፍ ነው። እነሱ ታሪፎቹን አይፈልጓቸውም። ይህንን መጠቀም ባይኖርብኝ እመርጣለሁ። ግን በቻይና ላይ ያለን ትልቅ ኃይል ነው" ሲሉ ለመነጋገር እንዲሁም ስምምነት ላይ መደረስ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ከጥር 24/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ለመጣል እንደሚያስቡ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ደግሞ አሜሪካ "እንደገና ሃብታም ሀገር" እንድትሆን ኢነርጂ "ፈር ቀዳጅ መሆኑን" ትራምፕ አስታውቀዋል።
አረንጓዴ የኃይል ማመንጫዎችን በመተቸት የጀመሩት ፕሬዝዳንቱ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን ከተፈጥሮ ጋዝ አንጻር ወጥ ያልሆኑ ሲሉ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፓነሎች የሚይዙትን የቦታ ስፋት ደግሞ "አስቂኝ" ገልጸዋቸዋል።
ከሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ደግሞ ጦርነቱ "በአፋጣኝ ማቆም አለበት" ከማለት ባለፈ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፍጹም ወደዚህ መግባት አልነበረባቸውም ብለዋል።
ጦርነቱ የጀመረው እሳቸው በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ቢሆን ኖሮ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር "ስምምነት በመድረስ" ግጭቱን ያስቀሩ እንደነበር አክለዋል።
ፑቲን ጦርነቱን ካላቆሙ በሩሲያ ላይ "ከፍተኛ ታሪፍ" እንደሚጥሉም ትራምፕ ተናግረዋል።
እአአ በ2022 በሩሲያ ወረራ የጀመረውን ጦርነት ተደራድረው በአንድ ቀን እንደሚያስቆሙ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።
ትራምፕ ቀደም ሲል ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመገናኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
"ከእሱ ጋር እንግባባለን" ሲሉ ትራምፕ ስለ ኪም ገልጸዋል።
"እሱ ጠንካራ ሃይማኖተኛ አይደለም። እሱ ብልህ ሰው ነው።" ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እአአ በ2019 ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ መካከል በሚገኘው ከወታደራዊ ነጻ በሆነው ዞን ውስጥ ነው።
በትራምፕ የመጀመርያ የስልጣን ዘመን ከኪም ጋር ሦስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ስልጣን ላይ እያሉ ሰሜን ኮሪያን የረገጡ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንትም ነበሩ።












