ዶናልድ ትራምፕ ሊጥሉ ያሰቡት ታሪፍ የትኞቹን ሀገራት ሊጎዳ ይችላል?

ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በዓለም አቀፉ ንግድ ተጎጂ ናት ብለው ያምናሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በዓለም አቀፉ ንግድ ተጎጂ ናት ብለው ያምናሉ

ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛ ዘመን የሥልጣን ዘመናቸውን መጀመራቸውን ተከትሎ በውጭ ምርቶች ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ እየዛቱ ነው።

ከካናዳ እና ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚገቡትን ሕገወጥ ስደተኞች እና ፌንታኒል የተሰኙ ዕጾችን መቆጣጠር ካላስቻሉ በሁለቱ አገራት ምርቶች ላይ 25 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ ተናግረዋል።

ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ 10 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ምርቶችም ታሪፉ እንደሚጠብቃቸው አስታውቀዋል።

ቻይና፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ቀዳሚዎቹ ሦስቱ የአሜሪካ የንግድ አጋሮች ናቸው። ታሪፍ መጣሉ የሀገራቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል። ይህም በአሜሪካውያን የምርቶቹ ተጠቃሚዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ አይቀርም።

ታሪፍ ምንድን ነው?

ታሪፍ ከውጭ ሀገራት በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የሚከፈል ግብር ነው።

ታሪፉ ከላኪው ይልቅ ዕቃውን በሚያስገቡ ድርጅቶች ላይ የሚጣል ሲሆን፣ ክፍያውም በሚገባው የምርት መጠን ላይ ይወሰናል።

አንድ ድርጅት እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ዶላር የሚገመቱ እና 25 በመቶ ታሪፍ የሚጣልባቸው መኪኖችን ካስመጣ፤ ለእያንዳንዱ መኪና 12 ሺህ 500 ዶላር መክፈል ይኖርበታል ማለት ነው።

ከቅድመ ክፍያ ሂሳብ በተቃራኒው የታሪፍ "ኢኮኖሚያዊ" ሸክም የት ይወድቃል? የሚለውን መመለስ ውስብስብ ሊሆን ይችላል።

የአሜሪካ አስመጪ ድርጅት ታሪፉን በአሜሪካ ውስጥ የችርቻሮ ዋጋ ላይ በመጨመር ምርቱን ወደ ሚገዛው ሰው ያስተላልፋል። በዚህ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ሸክሙ የአሜሪካ ሸማች ላይ ይወድቃል ማለት ነው።

ትራምፕ ለምን ታሪፍን ይመርጣሉ?

ዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ የአሜሪካን የአገር ውስጥ ምርቶች እና ሥራን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሥራ ለመፍጠርም እንደሚጠቅም ደጋግመው ይናገራሉ። የአሜሪካን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እና የታክስ ገቢን ለመጨመርም እንደ አንድ አማራጭ አድርገው ይመለከቱታል።

በአውሮፓውያኑ 2024 የምርጫ ዘመቻ ወቅት "በእኔ ዕቅድ መሠረት አሜሪካውያን ተቀጣሪዎች ከአሁን በኋላ ሥራችሁን በውጭ ሀገራት ስለመጠነቅ አይጨነቁም። ይልቁንም የውጭ ሀገራት ሥራቸውን በአሜሪካ ስለማጣት ይጨነቃሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ የዓለምን የኢኮኖሚ ሂደት በመሠረታዊነት ለመቀየር ይፈልጋሉ ሲል የቢቢሲ የምጣኔ ሀብት አርታኢ የሆነው ፋይሰል ኢስላም ይናገራል። "አሜሪካን መዝረፍ" በሚሉት ዕይታቸው ቻይና እና አውሮፓ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የንግድ ትርፍ መቀነስ ይፈልጋሉ ብሏል።

በአውሮፓውያን 2018 የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው በብረት እና በአሉሚኒየም ላይ የጫኗቸው ዓይነት ታሪፎች የአሜሪካን ብሔራዊ ደኅንነት ይከላከላሉ ብለው ትራምፕ ያምናሉ። ሁለቱ ምርቶች "የእኛ የጦር ኢንዱስትሪ መሠረት" ናቸው ብለዋል።

የአሜሪካንን የብረት ምርት ለመጠበቅ በሚል ትራምፕ ከውጭ በሚመጣ ብረት ላይ ታሪፍ ጥለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካንን የብረት ምርት ለመጠበቅ በሚል ትራምፕ ከውጭ በሚመጣ ብረት ላይ ታሪፍ ጥለዋል

ከዚህ በፊት የተጣሉ ታሪፎች እና ያስከተሉት ምላሽ

ትራምፕ በ2018 ከውጭ በሚገቡ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች እና ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ማፓናሎች ላይ እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ ጥለዋል። በሁለቱም ዘርፎች የተሰማሩ የአሜሪካ አምራቾች ፍትሃዊ ያልሆነ ውድድር እያጋጠማቸው መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት በውቅቱ አስታውቋል።

ከውጭ በሚገቡ ብረቶች ላይ 25 በመቶ እና በአሉሚኒየም ላይ ደግሞ 10 በመቶ ታሪፍ ጥለው ነበር።

ከሜክሲኮ እና ከካናዳ የሚገቡ የብረት እና የአሉሚኒየም ምርቶች ከታሪፉ ነጻ ሆነዋል። ሁለቱ አገራት ከአሜሪካ ጋር የነበራቸው ነጻ የንግድ ስምምነት ለዚህ ጠቅሟቸዋል።

ብረትን ወደ አሜሪካ በብዛት ከሚልኩት መካከል አንዱ የሆነው የአውሮፓ ኅብረት ጂንስ፣ ዊስኪ እና የሃርሊ ዴቪድሰን ሞተር ሳይክሎችን ጨምሮ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚገመቱ የአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ በመጣል ምላሽ ሰጥቷል።

ትራምፕ ከሥጋ እስከ የሙዚቃ መሳሪያዎች በሚደርሱ ከ360 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚገመቱ የቻይና ምርቶች ላይም ታሪፍ ጥለዋል። ቻይና በበኩሏ ከ110 ቢሊየን ዶላር በላይ በሚሆኑ የአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ በመጣል ምላሽ ሰጥታለች።

በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን በቻይና ላይ የተጣሉት አብዛኞቹ ታሪፎች እንዲቀጥሉ ከማድረግ ባለፈ እንደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባሉ ምርቶች ላይም አዳዲስ ታሪፎች ተጥለዋል።

የትራምፕ ታሪፍ ያሳደረው ተጽእኖ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ያጣሉት ታሪፍ አሜሪካ ከአንዳንድ ሀገሮች የምታስገባቸውን ምርቶች መጠን ቀንሷል። ግን ሌሎች ሀገራት ወደ አሜሪካ የሚልኩትን ምርት መጠን ደግሞ ጨምሯል።

ከ2018 በፊት ወደ አሜሪካ ከሚገቡ ምርቶች የቻይና ምርቶች ከ20 በመቶ በላይ ይይዙ ነበር። ይህ አሃዝ አሁን ላይ ከ15 በመቶ በታች መድረሱን የአሜሪካ ሴንሰስ ቢሮ አስታውቋል።

በ2023 ሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ምርቶችን በመላክ ቻይናን በመቅደም አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሜክሲኮ 476 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ወደ አሜሪካ ስትልክ፣ የቻይና ደግሞ 427 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል።

ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በርካታ ኩባንያዎች (በተለይም መኪና አምራቾች) ሜክሲኮ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የነጻ ንግድ ስምምነቶች እና ያለውን ርካሽ የሰው ኃይል ለመጠቀም ማምረቻቸውን ወደ አገሪቱ በማዞራቸው ነው።

ሜክሲኮ በ2023 በዓለም ሰባተኛዋ የመንገደኞች ማሳፈሪያ ተሽከርካሪዎች አምራች ለመሆን በቅታለች።

ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ በምሥራቅ እስያ ያሉ አገራት ወደ አሜሪካ የሚላኳቸው ምርቶች ጨምረዋል።

ይህ የሆነበት ምክንያት ምርቶቻቸው በከፊል ከቻይና ምርቶች አንጻር ለአሜሪካ ሸማቾች ርካሽ ስለነበሩ እንዲሁም በከፊል ብዙ የቻይና ኩባንያዎች የአሜሪካን ታሪፍ ለማስቀረት ወደ እነዚህ ሀገራት በመዘዋወራቸው ነው።

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ እንደ ኢንዶኔዢያ፣ ፊሊፒንስ፣ ታይላንድ እና ቬትናም ያሉ አገራት በአውሮፓውያ 2016 ብቻ 158 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ልከዋል። በ2023 ግን ቁጥሩ ወደ 338 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።

"በ2018 ታሪፎች በጣም የተጎዳችው ቻይና ነበረች" ሲሉ በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ሰሴክስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ኒኮሎ ታምቤሪ ተናግረዋል።

"እንደማስበው ከሆነ ቬትናም በዚህ ታሪፍ አሸናፊ ከሆኑት መካከል አንዷ ሆናለች።"

የታሪፍ ጭማሪው የአሜሪካን የብረታ ብረት እና የአሉሚኒየም ምርትን ብቻ ሳይሆን ዋጋውንም ማሳደጉን የፒተርሰን ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክስ ኢንስቲትዩት ገልጿል። ይህም በሌሎች የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሥራዎች እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

የፒተርሰን ኢንስቲትዩት አክሎም የትራምፕ የታሪፍ እርምጃዎች የዋጋ ንረት እንዲጨምር በማድረግ የአሜሪካን ሸማቾች ይበልጥ እንዲሸሹ አድርጓል ብሏል።

ሜክሲኮ ከአሜሪካ ጋር ባላት የነጻ ንግድ ስምምነት ምክንያት የዓለም የመኪኖች ምርት ማዕከል ለመሆን ችላለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሜክሲኮ ከአሜሪካ ጋር ባላት የነጻ ንግድ ስምምነት ምክንያት የዓለም የመኪኖች ምርት ማዕከል ለመሆን ችላለች

ትራምፕ አሁን ምን ዓይነት ታሪፎችን ይጥላሉ?

ትራምፕ ከሜክሲኮ እና ከካናዳ በሚገቡ ምርቶች ላይ 25 በመቶ ታክስ እንደሚጥሉ ዝተዋል። ይህ የሚሆነው በአገራቱ ድንበሮች የሚኖረው የስደተኞች እና የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር እስኪቆም መሆኑን አክለዋል።

በቻይና ምርቶች ላይ ከነበረው በተጨማሪ 10 በመቶ "የቅጣት" ታሪፍ መጣል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ለዚህ እንደ ምክንያት ያስቀመጡት ፌንታሊን ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ አብዛኞቹ ኬሚካሎች ከቻይና የሚመጡ በመሆናቸው ነው።

ይህም በመጪው የካቲት ወር ሊተገበር ይችላል።

"በጣም በጣም በመጥፎ ሁኔታ ይዘውናል" በሚል ትራምፕ የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት ላይ ታሪፍ ለመጣልም ዝተዋል።

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በአሜሪካ ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚገመት ታሪፍ በመጣል ለመበቀል ዝተዋል። "ካናዳ ምላሽ ትሰጣለች። ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው" ብለዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ "ብሔራዊ ጥቅሟን ለመጠበቅ" የታሪፍ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቷን አስታውቋል።

ካናዳ እና ሜክሲኮ እንዴት ሊጎዱ ይችላሉ?

አዲሱ ታሪፍ ተግባራዊ ከሆነ በዋናነት የካናዳ እና የሜክሲኮን ኢኮኖሚ ይጎዳል ሲሉ የብሔራዊ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ምርምር ተቋም ባልደረባው ፕሮፌሰር ስቴፈን ሚላርድ ተናግረዋል።

ሁለቱም ሀገራት ለምርታቸው ገበያ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ በጣም ጥገኛ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ሜክሲኮ ወደ ውጭ ከምትልከው ዕቃዎች 83 በመቶውን፣ ካናዳ ደግሞ 76 በመቶውን ምርት ወደ አሜሪካ ይልካሉ።

"ካናዳ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እና ማሽነሪዎችን ለአሜሪካ ትሸጣለች። 25 በመቶ ታሪፍ መጣሉ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የአገር ውስጥ ምርትን (ጂዲፒ) በ7.5 በመቶ ሊቀንስ ይችላል። ይህም ጉልህ የሆነ ጉዳት ያስከትላል" ሲሉ ፕሮፌሰር ሚላርድ ተናግረዋል።

"25 በመቶ ታሪፍ በሜክሲኮ ላይ ከተጣለ በሀገሪቱ የተቋቋሙ የመኪና አምራች ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ።"

"ታሪፉ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሜክሲኮን የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) መጠንን በ12.5 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል። ይህ ትልቅ ኪሳራ ነው።"

ዊልሰን ሴንተር ከሚገኘው የሜክሲኮ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሊላ አብዴል የአሜሪካ ታሪፍ ለመጣል የሰነዘረችው ዛቻ ለሜክሲኮ ሠራተኞች "አውዳሚ" ነው ሲሉ ገልጸዋል።

"አሜሪካ ውስጥ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሥራቸው በአሜሪካ-ሜክሲኮ የንግድ ግንኙነት ላይ ተንጠልጥሏል። በቅርቡ በተደረገ ጥናት መሠረትም 14.6 ሚሊዮን ሥራዎች በሁለቱ አገራት ንግድ ላይ መመሥረቱን አስታውቋል" ብለዋል።