የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች ጊዜያዊ አስተዳደሩ በአዲስ እንዲዋቀር 'መወሰናቸውን' አሳወቁ

በትግራይ ክልል ያሉ የወታደራዊ ኃይል አመራሮች ህወሓት በወሰነው መሠረት 'የተዳከመ' ያሉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተነስቶ በሌላ እንዲዋቀር መወሰናቸውን ገለጹ።
ራሳቸውን የትግራይ ኃይል አመራሮች ብለው የሚጠሩት እነዚህ የክልሉ መኮንኖች ለቀናት ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ሐሙስ ጥር 15/2017 ዓ.ም. መቀለ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ነው የጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደ አዲስ እንዲዋቀር ውሳኔ ማሳለፋቸውን ያሳወቁት።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም በማለት የሌሎች መጠቀሚያ ሆኗል የሚል ብርቱ ክስ አቅርበዋል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በወታደራዊ አመራሮቹ ስለቀረበበት ክስ እና ስላሳለፉት ውሳኔ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
በመግለጫው በጊዜያዊ አስተዳደሩ "ቁልፍ ሥልጣን የነበራቸው አመራር እና አባላት ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ክህደት በመፈጸም የውጭ ኃይል መሣሪያ ሆነዋል" ብሏል።
ነገር ግን መግለጫው በሕዝብ ጥቅም ላይ ስለደረሰው ጉዳትም ሆነ "የውጭ ኃይል" ያሉት አካል ማንነትን በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም።
ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ፓርቲው በሊቀመንበሩ እና በምክትል ሊቀመንበሩ በሚመራ ቡድኖች ተከፍሎ ሲካሰስ መቆየቱ ይታወሳል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን በዶ/ር ደብረጽዮን በሚመራው ሌላኛው ቡድን ምክንያት ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን እንቅፋት እንደገጠመው በመግለጽ ክስ ሲሰነዝር ቆይቷል።
በድርጅቱ ሊቀመንበር የሚመራው የህወሓት ቡድን ከዚህ ቀደም ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፍ የገለጸው የወታደራዊ አመራሮቹ መግለጫ፣ ድጋፉን ለዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን መስጠቱን በተዘዋዋሪ አመልክቷል።
በንባብ የቀረበው መግለጫ በአመዛኙ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር "ድክመቶች" ላይ የሚያተኩር እና አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየሞከረ ነው በማለት ወቅሷል።
በዚህም ምክንያት "የተዳከመ" እና "ተልዕኮውን የዘነጋ" ያለውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማጠናከር አመራሮቹ ተነስተው በሌሎች መተካት እንዳለባቸው አሳስቧል።
በዚህም መሠረት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለተካሄደውን የህወሓት 14ኛ ጉባኤ እውቅና በመስጠት በጉባኤው ውሳኔ መሠረት የጊዜያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
አወዛጋቢ የነበረው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ በምርጫ ቦርድ እና ጥቂት በማይባሉ የድርጅቱ አመራሮች ዕውቅና ያልተሰጠው ሲሆን በአመራሮች እና በአባላት መካከልም ለተፈጠረ መከፋፈል ምክንያት ሆኗል።
በርካታ አመራሮች እና አባላት እራሳቸውን ባገለሉበት የህወሓት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ከ17 በላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከጉባኤው ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል።
በጉባኤው ድጋሚ ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ደብረፂዮን "የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚው ህወሓት ነው። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ድርሻ 50 እጅ በላይ የህወሓት ስለሆነ የፈለግነውን መተካት እንችላለን" ሲሉ ተናግረው ነበር።
የሠራዊቱ አመራር አባላት መግለጫ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በአካባቢያዊ እና በአውራጃዊነት መከፈሉን በመጥቀስ፣ በወሳኝ የአመራር ውድቀት ምክንያት "የሕዝቡ ጥቅም ተዘንግቶ ወደ መጠቃቃት አምርቷል" ብሏል።
ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ያሉ የመገናኛ ብዙኃንን የወቀሰው መግለጫ ሚዲያዎች የግለሰብ ፖለቲከኞችን ግላዊ ፍላጎት ማሳኪያ እና "የውጭ ኃይሎች መሳሪያ" ሆነዋል በማለት በስም ያልጠቀሳቸውን ሚዲያዎች ከሷል።
በስብሰባቸው ላይ ተመሳሳይ አቋም ያስተጋቡት ወታደራዊ አመራሮቹ "ህወሓት የትግራይን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማሻሻል ያሳለፈው ውሳኔ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን" ድጋፋቸውን መግለጻቸውን አሳቋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሠራዊቱን ወክለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት የሆኑትን ግለሰቦች በመገምገም "እምነት የሚጣልባቸው ያልሆኑትን" በሌሎች እንዲተኩ መወሰናቸውንም ገልጿል።
እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሠራዊቱ ላይ የሚካሄደውን የስም ማጥፋት ዘመቻን መከላከል ባለመቻሉ "በክህደት" ወንጅለውታል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በትግራይ ኃይል ሥር የሚገኙ ግለሰቦች በክልሉ ውስጥ በሚፈጸመው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የማዕድን ቁፋሮ ውስጥ ተሳትፎ አላቸው በሚል ሲካሳቸው እንደነበር ይታወቃል።
ለዚህም በሰጡት ምላሽ በሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች ያላቸው ኃላፊነት "ምንም ይሁን ምን" በሕግ ተጠያቂ እናደርጋለን ሲሉ የሠራዊቱ አመራሮች ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ ያለው ችግር "ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚሻ ነው" ያለው መግለጫ ማንኛውም ነገር "ከትግራይ ሠራዊት አቅም በላይ አይደለም" በማለት ይህንን ሰበብ በማድረግ "የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን አንቀበልም" ብለዋል።
አለመግባባት ውስጥ ያሉት በአቶ ጌታቸው እና በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመሩት የህወሓት ቡድኖች ባለፉት ወራት ሲካሰሱ የነበረ ሲሆን፣ የደብረጽዮን ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩ በድጋሚ እንዲዋቀር በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያርብ ነበር።
ሁለቱ ወገኖች ባለፈው ኅዳር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይት ይኸው ጥያቄ ተነስቶ፣ በክልሉ ምርጫ ተካሂዶ መደበኛ አስተዳደር እስኪቋቋም ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሥራ ላይ እንደሚቆይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለጹ ይታወሳል።












