ጠፍቶ የነበረው 50 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣው ስዕል ከ100 ዓመት በኋላ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
በኦስትሪያዊው ሰዓሊ ጉስታቭ ክሊመት የተሳለው እና ለ100 ዓመታት ጠፍቶ የነበረው ስዕል ቪዬና ውስጥ ተገኘ።
ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ እንደሚያወጣ የሚገመተው ይህ ስዕል በአንድ አይሁዳውያን ቤተሰብ አባላት እጅ ላይ ይገኝ ነበር።
ለመጨረሻ ጊዜ ስዕሉ በአደባባይ የታየው እአአ 1925 ላይ ነበር።
ስዕሉ እስካሁን ድረስ ጠፍቶ ቆይቶ አሁን ላይ በሌላ የቤተሰብ አባላት ጋር ተገኝቷል። እነዚህ የቤተሰብ አባላት ስዕሉ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ይዘው ስለመቆየታቸው ተገልጿል።
ዘ ኢን ኪንስኪይ የተባለ የጥበብ ሥራ አጫራች ድርጅት ይህ “ፖርትሪዬት ኦፍ ፍራኡሌን ሌይሰር” የሚል መጠሪያ ያለው ስዕል ከ54 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ አለው ይላል።
ተቋሙ እንደዚህ አይነት ትልቅ የጥበብ ዋጋ ያለው ስዕል በመካከለኛው አውሮፕ ገበያ ላይ ለአስርት ዓመታት ቀርቦ አያውቅም ካለ በኋላ የስዕሉን ዳግም መገኘት “እጅግ አስደሳች” ሲል ገልጾታል።
ስዕሉ ሚያዚያ 2016 ላይ ለጨረታ እንደሚቀርብ ተገልጿል።
ስዕሉ ለጨረታ ቀርቦ ከመሸጡ በፊት በዩናይትድ ኪንግደም፣ ስዊትዘርላንድ፣ ጀርመን እና ሆንግ ኮንግ ለዕይታ ይቀርባል።
በአንድ ወቅት የስዕሉ ባለቤት የነበሩት ባለጸጋ አይሁዳውያን ቤተሰብ ስዕሉ ከይዞታቸው እንዴት ሊወጣ እንደቻለ አያውቁም።
ይሁን እንጂ ስዕሉ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ጀርመን በኃይል ከተወሰደ በኋላ ደብዛው ጠፍቶ እንደቆየ ይገመታል።
የቤተሰቡ ጠበቃ ግን በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከጦርነቱ በፊት ስዕሉ በናዚ ስለመዝረፉ ማረጋገጫ የለም ብለዋል።
ኦስትሪያዊው ሰዓሊ ጉስታቭ ክሊመት የስዕል ስራ የሆነ “ሌዲ ዊዝ ኤ ፋን” የተባለ ስዕል ከዚህ ቀደም ለጨረታ ቅርቦ 85.3 ሚሊዮን ፓዎንድ ከተሸጠ በኋላ በአውሮፕ በጨረታ በትልቅ ገንዘብ የተሸጠ የጥበብ ሥራ ሆኖ ክብረ ወሰን ይዟል።












