ቻድ ታዳጊ ሴቶች ከአገር እንዳይወጡ ክልከላ ጣለች

ስልክ የያዘች ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻድ መንግሥት ታዳጊ ሴቶች የቤተሰባቸውን ፈቃድ ሳያገኙ ከአገሪቱ ለቀው መውጣት አይችሉም ሲል ዕገዳ ጣለ።

የአገሪቱ የደኅንንት ሚኒስትር ጄኔራል ኢድሪስ ዶኮያ አዲኬር ውሳኔውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ከአገር የሚሰደዱ ታዳጊ ሴቶች “ለብዝብዛ እየተጋለጡ” መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ይህ ታዳጊ ሴቶች ከአገሪቱ እንዳይወጡ የሚከለክለው እገዳ መውጣቱን ተከትሎ የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድኖች መንግሥት ውሳኔውን እንዲቀለብሰው ተቃውሟቸውን እኣሰሙ ነው።

የማዕከላዊቷ አገር ቻድ መንግሥት እገዳውን ማሳወቁን ተከትሎ አየር መንገዶችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ታዳጊ ሴቶችን እንዳያሳፍሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

ከአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስትር በኩል የተሰራጨው ማሳሰቢያ እገዳውን ከማሳወቅ ውጪ፣ እገዳው ተግባራዊ የሚሆነው በየትኛው የእድሜ ክልል ባሉ ታዳጊ ሴቶች ላይ እንደሆነ እንዲሁም ከአገር እንዲወጡ የማንን ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ያለው ነገር የለም።

የቻድ የሴቶች መብት ሊግ ይህንን የጉዞ ዕገዳን ተከትሎ እንዳለው፣ ውሳኔው ታዳጊ ሴቶች ያላቸውን መሠረታዊ የሰብአዊ መብት መርኅን የሚቃረን ነው ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።

ቡድኑ በተጨማሪም የአገሪቱ ዜጋ የሆኑ ታዳጊ ወንዶች ለሕገውጥ ዝውውር የተጋለጡ ሆነው ሳለ ታዳጊ ሴቶች ላይ በተናጠል የተጣለው የጉዞ ዕገዳ የፆታ መድልዎን የሚንጸባርቅ ነው ብሏል።

ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተመለከተ የወጣ ዓለም አቀፍ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ቻድ ውስጥ የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር በቅርብ ዓመታት ውስጥ መጨመር አሳይቷል።

ሪፖርቱ ጨምሮም ቀደም ባለው የፈረንጆች ዓመት የቻድ አጎራባች በሆኑ አገራት ውስጥ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን ጠቅሷል።

የአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስቴር ከቻድ የሚደረጉ ሕገወጥ የሰዎች በተለይም የታዳጊ ሴቶች ዝውውርን እና ብዝበዛን ለመቆጣጠር ያወጣው ይህ የጉዞ ዕገዳ የዜጎችን መብት የሚጋፋ ነው በሚል ተቃውሞ እየበረታበት ነው።