በትግራይ ከባድ ቅጣት የሚያስከትል ክስ የቀረበባቸው ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ሲፒጄ ጠየቀ

በአስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች ምስግና ስዩም፣ ሐበን ሐለፎም፣ ዳዊት መኮንን እና ተሾመ ጠማለው
የምስሉ መግለጫ, በአስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች ምስግና ስዩም፣ ሐበን ሐለፎም፣ ዳዊት መኮንን እና ተሾመ ጠማለው

የእድሜ ልክ ወይም ሞት ሊያስፈርድ የሚችል ክስ የቀረበባቸው አምስት ጋዜጠኞችን የትግራይ ባለሥልጣናት እንዲለቁ የጋዜጠኞች መብት ተከራከራው ድርጅት ሲፒጄ ጠየቀ።

ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ያሉት አምስቱ ጋዜጠኞችና ሌሎችም እንዲለቀቁ የጠየቀው ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስት (ሲፒጄ) የጋዜጠኞቹን ቤተሰቦችና የሥራ ባልደረባቸውን ማነጋገሩን ገልጿል።

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ ባሉት የክልሉ ባለሥልጣናት ታስረው የሚገኙት የትግራይ ቲቪ ጋዜጠኞች ተሾመ ጠማለው፣ ምስግና ስዩም፣ ሐበን ሐለፎም፣ ኃይለሚካኤል ገሰሰ እና ዳዊት መኮንን መሆናቸው ተገልጿል።

ምንጮች ለሲፒጄ እንደነገሩት መቀለ ውስጥ በአስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች፣ ከፌደራል መንግሥቱ እና ከገዢው ፓርቲ ብልጽግና ጋር ሠርተዋል በሚል “ከጠላት ጋር በመተባበር” በባለሥልጣናቱ ክስ ቀርቦባቸዋል።

በክልሉ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በፕሮፓጋንዳ፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ ወይም ማንኛውንም አይነት ግንኙነት ማድረግን ጨምሮ በየትኛውም ጊዜ “ከጠላት ጋር መተባበር” እንደሚያስጠይቅና በእድሜ ልክ ወይም በሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል የመብት ተቆርቋሪው ድርጅት ገልጿል።

ከሳምንታት በፊት አምስቱ የትግራይ ቲቪ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ባልደረቦቻቸው መናገራቸውንና ክስ ሳይመሰረትባቸው መቆየታቸውን ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።

በወቅቱም የመቀለ ከተማ ዐቃቤ ሕግ አቶ አዲስ ገብረ ሥላሴ፣ ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ሳይሆን “በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው” መሆኑን በመግለጽ፣ ጉዳያቸውም በምርመራ ላይ መሆኑን ገልጸው ነበር።

ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ የቆዩት ከአምስቱ ጋዜጠኞች መካከል በሦስቱ ላይ “ከጠላት ጋር መተባበር” የሚል ክስ እንደሚመሰረትባቸው ዐቃቤ ሕግ ገልጿል። ከቀናት በፊትም ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት መጀመሩ ተዘግቧል።

“ትግራይ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት ኢላማ እንደረጋለን ብለው ስጋት ሳያድርባቸው በነጻነት ለመኖርና መሥራት ሊፈቀድላቸው ይገባል” ሲሉ የሲፒጄ ከሰሃራ በታች አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ ተናግረዋል።

በአስር ላይ የሚገኙት አምስቱ ጋዜጠኞች በክልሉ መንግሥት በሚተዳደረው እና በኋላም የፌደራል መንግሥቱ ትግራይን በተቆጣጠረበት ወቅት ድግሞ በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ስር ሥራውን ሲያከናውን ነበር።

ሲፒጄ ያነጋገራቸው ሰዎች እንዳሉት ለጋዜጠኞቹ እስር ለአጭር ጊዜ ከቆየው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስር በትግራይ ቴሌቪዥን ውስጥ መሥራታቸው ነው ብለው ያምናሉ።

ጋዜጠኞቹ በቴሌቪዥን ጣቢያው ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሰሩ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ሦስቱ ከመታሰራቸው ጥቂት ወራት በፊት ከሥራቸው ታግደው ነበር ተብሏል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ በተደረገ ሪፖርት መሠረት ምስግናን፣ ሐበንን፣ ተሾመን እና ኃይለሚካኤልን ጨምሮ በአጠቃላይ 15 ጋዜጠኞች ትግራይ ውስጥ በእስር ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል። ነገር ግን ታስረዋል ያላቸውን የሌሎቹን 11 የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞችን ማንነት አላመለከተም።

ሲፒጄ የታሰሩት ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ የጠየቀበትን ይህንን መግለጫ ከማውጣቱ በፊት ትግራይ ቴሌቪዥን፣ የትግራይ የውጭ ግንኙነት ቢሮ፣ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረ ሕይወት እንዲሁም የህወሃት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳን ስለጋዜጠኞቹ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል።