የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ፑቲን በመጥፎ የጤንነት ሁኔታ ላይ ናቸው የሚል መረጃ የለም አለ

ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ዳይሬክተር፣ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ባልተረጋጋ እና በመጥፎ የጤንነት ሁኔታ ላይ ናቸው የሚል መረጃ የለም አሉ።

በዚህ ዓመት 70ኛ ዓመታቸውን ያከበሩት ፑቲን፣ የጤንነት ሁኔታቸው እንደታወከ ምን አልባትም በካንሰር እየተሰቃዩ እንደሆነ የሚያመለክቱ ያልተረጋገጡ ግምቶች በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ እየጨመሩ መጥተዋል።

ይሁን እንጂ የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ፣ይህንን የሚያመልክት ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ሲሉ ፑቲን በጣም ጤነኛ መስለው እንደሚታዩም ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ይህንን የተናገሩት አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የረጅም ርቀት የጦር መሣሪያዎችን እንደምትሰጥ ባስታወቀችበት ወቅት ነው።

ቀደም ብሎ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የሩሲያ ጦር በዩክሬን የሚኖረው ትኩረት ምሥራቃዊ ክፍል ላይ ብቻ እንዳልሆነና ምዕራባውያኑ ለዩክሬን መሰል የጦር መሣሪያዎችን ካቀረቡ በኋላም የሞስኮ ስትራቴጂ ተቀይሯል ማለታቸው ይታወሳል።

የስለላ ድርጅቱ ዳይሬክተር ዊሊያም፣ በኮሎራዶ፣ አስፐን በተካሄደው የደኅንነት ፎረም ላይ፣ ስለ ፕሬዚደንት ፑቲን የጤንነት ሁኔታ ብዙ የሚናፈሱ ወሬዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ “እስከምናውቀው ድረስ ፑቲን ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ነው” ብለዋል።

ይህም የስለላ ድርጅቱ ውሳኔ አለመሆኑን በሳቅ ታጅበው ተናግረዋል።

በሞስኮ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ዊሊያም፣ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የሩሲያን መሪ በቅርበት ሲታዘቡ እና ሲያነጋግሩ እንደነበርም አስታውሰዋል።

 “ ፑቲን በቁጥጥር፣ በማስፈራራት እና በቅጣት ያምናል። ባለፈው አስር ዓመት በዙሪያቸው ያሉ አማካሪዎቻቸው በመቀነሳቸውም እነዚህ ባህርያት አይለዋል” ሲሉም የሲአይኤው ኃላፊ ተናግረዋል።

"እንደ ሩሲያ መሪም መዳረሻቸው ሩሲያን ወደ ኃያልነቷ መመለስ እንደሆነ እርግጠኛ ናቸው። ለዚህም ዋናውና ቁልፉ ነገር በሩሲያ ቀጠና ተፅዕኖ መፍጠር ነው ብሎ ያምናል ። በመሆኑም ዩክሬንን ሳይቆጣጠር ይህንን ማድረግ አይችልም።” ሲሉም አክለዋል።

ዊሊያም የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ስለማቀዷ መረጃ መሰብሰቡን ተከትሎ ዩክሬንን መውረር አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትል ለማስጠንቀቅ ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ወደ ሞስኮ አቅንተው ነበር።

የሩሲያ ፕሬዚደንት እቅዶች በተሳሳቱ ግምቶች በተለይም በዩክሬን ላይ ባላቸው አንዳንድ ቅዠቶች እንዲሁም የሚመጣውን ሁሉ ለመቋቋም ባላቸው ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውንም ዊሊያም ተናግረዋል።

“ፑቲን ንግግራቸውን ያምናሉ። እናም ላለፉት ዓመታት ዩክሬን እውነተኛ አገር አይደለችም ሲሉ በግል ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እንግዲህ እውነተኛዎቹ አገራት እየተዋጉ ነው። ዩክሬናውያንም እያደረጉ ያሉት ይኸው ነው ” ብለዋል።

የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊለሊያም በርን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊለሊያም በርን በሞስኮ አሜሪካ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስካሁን ሩሲያ በዩክሬን 15 ሺህ ሰዎች እንደተገደሉባት እና ምናልባትም 45 ሺህ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አሜሪካ ግምቷን ማስቀመጧን የተናገሩት ዊሊያን፣ በዩክሬን ላይ የደረሰው ጉዳት ግን ከዚህ ያነሰ እንደሆነ ገምተዋል።

አክለውም ሩሲያ በአሁኑ ወቅት በዶንባስ ውስጥ ያላት የኃይል ክምችትም ጦሩ ጥሩ ትምህርት እንደወሰደ የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ሩሲያ፣ በዩክሬን ምሥራቃዊ ግዛት “የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል፤ በመሆኑም ነጻ መውጣት አለባቸው” ስትል በዩክሬን ላይ ወረራ የፈፀመችው ባለፈው የካቲት ወር ላይ ነበር።

ባለፉት አምስት ወራትም ሩሲያ ምሥራቃዊ እና ደቡባዊ የዩክሬንን ክፍል ተቆጣጥራለች። ይሁን እንጂ ቀድሞ ያለመችውን ኪዬቭን የመያዝ እቅዷ አልተሳካላትም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ዋና ዓላማዋ ዶንባስን ነጻ ማውጣት እንደሆነ ገልጻለች።

አሜሪካ ሩሲያ የዩክሬንን አንዳንድ ግዛቶች ለመጠቅለል እየተዘጋጀች ነው ስትል ከሳለች።

ይሁን እንጂ ረቡዕ ዕለት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ የረጅም ርቀት የጦር መሣሪያ ለዩክሬን ማቅረቧ የሞስኮን ጦር ትኩረት ሊያሰፋው እንደሚችል ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ሚኒስትር ላቭሮቭ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የረጅም ርቀት የጦር መሣሪያዎች እንደምትሰጥ ረቡዕ ዕለት አስታውቃለች።

ዩክሬን የሩሲያ ወታደሮችን ግስጋሴ ለመግታት ተጨማሪ አራት የሂማርስ ዘመናዊ ሮኬት ሥርዓት የምትቀበል ሲሆን፣ ይህም በአጠቃላይ ያላትን መሣሪያ ቁጥር ወደ አስራ ስድስት እንደሚያደርሰው የአሜሪካ የመከላከያ ኃላፊ ሊሎይድ ኦስቲን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ቀዳማዊት እመቤት ኦሌና ዜለንስኪ በአሜሪካ ኮንግረንስ ላይ “ዩክሬናውያን ላይ የሚደርሰው የሽብር ጥቃት ለማስቆም ይረዳል” በሚል ተጨማሪ የአየር መቃወሚያ ሥርዓት እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።