የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሬዚዳንት ፑቲን ታመዋል መባሉን አስተባበሉ

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ታመዋል መባሉን አስተባበሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላቭሮቭ ከፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፕሬዚዳንት ፑቲን በየቀኑ በአደባባይ እንደሚታዩ እና እንደማኛውም ጤነኛ ሰው የህመም ምልክት አያይባቸውም ብለዋል።

በያዝነው ዓመት 70 ኛ ዓመታቸውን የሚደፍኑት ፕሬዚዳንት ፑቲን በጤና እክል ምናልባትም በካንሰር ህመም እየተሰቃዩ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ያልተረጋገጡ የመገናኛ ብዙኃን ሪፖርቶች ወጥተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ቃለ መጠይቅ የሰጡት ሩሲያ በዩክሬን ዶንባስ ግዛት ግስጋሴዋን በቀጠለችበት ማግስት ነው።

ላቭሮቭ በዚህ ጉዳይ ላይም አስተያየት የሰጡ ሲሆን ምሥራቃዊ ግዛትን ነፃ መስጠት ለሩሲያ ቅድመ ሁኔታ የሌለውና ቅድሚያ የምትሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

በእሳቸው አስተያየት ሩሲያ “የኒዮ ናዚ አገዛዝና ርዕዮተ ዓለምን” እየተዋጋች ነው በማለት በክሬምሊን በሰፊውና በተደጋጋሚ የሚነገረውን ትርክት ደግመዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን አዘውትረው በአደባባይ እንደሚታዩ አፅንኦት በመስጠት ላቭሮብ ለቲኤፍ1 እንደተናገሩት “ጤናማ የሆኑ ሰዎች በፕሬዚዳንቱ ላይ የህመም ምልክቶች ሊያዩ ይችላሉ ብዬ አላምንም” ብለዋል ።

“በቴሌቪዥን ስክሪኖቻችሁ ላይ ማየት፣ ንግግሮቻቸውን ማንበብ እና ማዳመጥ ትችላላችሁ” በማለትም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ሚኒስትሩን ዋቢ አድርጎ አካቷል።

“ማንም ሰው በየቀኑ ተመልክቶ ለመገምገም ዕድሎች ቢኖሩም እንዲህ አይነት ወሬዎችን ለሚነዙ ሰዎች ህሊና ትቼዋለሁ” ብለዋል።

የብሪታኒያ የስለላ ምንጮች ፕሬዚዳንት ፑቲን ባለፈው ሳምንት በጠና መታመማቸውን ለሚዲያዎች መናገራቸው ሪፖርት ተደርጓል።

ይሁን እንጂ በጤናማ የኑሮ ዘይቤያቸው እና በስፖርት ፍቅራቸው የሚታወቁት የሩሲያው መሪ ጤናቸውን በተመለከተ የሚነዙ ወሬዎች ለዓመታት ቀጥለዋል።

የምዕራቡ ዓለም የስለላ ተቋማትየፕሬዚዳንት ፑቲንን አዕምሯዊና አካላዊ ጤናቸውን በተመለከተ ጥብቅ ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።