ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ውጊያ ለእናት አገር የሚደረግ ትግል ነው፡ ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ ጦር በዩክሬን ለሚኖረው የወደፊቱ የሩሲያ ምድር እየተዋጋ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በድል በዓል ቀን ተናገሩ።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር አገራቸው ዩክሬን ላይ የከፈተችውን ወረራ ትክክለኛነት በሰፊ ማብራሪያ ይገልጻሉ ከሚለው ግምት የተቃረነ ሆኖ ተገኝቷል።
ፑቲን ሰሞነኛውን ጦርነት እንደ አውሮፓውያኑ በ1945 ከቀናቸው ድል ጋር ያመሳሰሉት ሲሆን እየሆነ ላለው ሁሉ ምዕራባውያን እና ኔቶን ተጠያቂ አድርገዋል።
10ኛ ሳምንት እየያዘ ባለው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የሲቪል ሰዎች ሞት በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው።
ባለፈው እሁድ ሩሲያ 60 ሲቪል ሰዎች እንደነበሩበት በተገመተ ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን ሌላ የዩክሬን ከተማ ደግሞ ትናንት ሰኞ የቦንብ ጥቃት ሰለባ ሆኗል።
ታዲያ ትናንት ፑቲን ኪዩቭ ያለውን መንግስት አዲሱ ናዚ ሲሉ ጠርተውታል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ አሁን ላይ የጥቃቷ ዋነኛ ኢላማ የሆነውን ምስራቃዊ ክፍልን በመጥቀስ እናት ምድራችንን መጠበቅ ተገቢ ተግባር ነው ያሉ ሲሆን "ዛሬ በዶንቦስ ለሚገኘው ሕዝባችን እየታገላችሁ ነው። ለሩሲያ እናት ምድር እየተዋደቃችሁ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
በተጨማሪም ፑቲን ወረራው አገራቸው የኔቶና የዩክሬን ጥቃት ቀድሞ ለመመከት የተደረገ ነው ሲሉ ማስረጃ ያላቀረቡበትን ወቀሳ ሰንዝረዋል።
"ታሪካዊ የሆነው መሬታችን ዶምቦስ ላይ መከራ ሊያደርሱ ሲዘጋጁ ነበር። ኪዮቭ የኒውክለር መሳሪያ ሊታጠቁ እንደሚችሉ ሲገልጹ ነበር። ኔቶ ደግሞ ለእኛ የቀረበ መሬት ማሰስ ጀምሮ ነበር። ያ ደግሞ ለኛ እና ለድንበራችን የሚታይ ስጋት እየሆነ ሄዶ ነበር "ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ አንዱ የዩክሬን ከፍተኛ አመራር በትዊተር ገጻቸው ላይ በሰጡት አሰተያየት ለጦርነቱ ምክንያታዊ መነሻ የለም ብለዋል።
"የኔቶ አባላት ሩሲያን የማጥቃት ዓላማ አልነበራቸውም። ዩክሬንም ክሪሚኒያን የማጥቃት ዕቅድ አልነበራትም" ሲሉም አክለዋል።
በዚህም መነሻ የሩሲያ ፕሬዝዳንት የጦርነት ስትራቴጂ ለውጥ ሳያደረጉ እንደማየቀር ተገምቷል።
አሁን "ልዩ ዘመቻ" እያሉ የሚጠሩትን ወረራ ወደ ተሟላ ጦርነት ሊቀይሩት ወይም የሩሲያን ጦር እንቅስቃሴ ለማጠናከር የወታደሮችን ቁጥር ከፍ ሊያደርጉት እንደሚችል ተተንብዮዋል።














