የዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል የመሆን ጥያቄ አስርት አመታትን ይወስዳል ተባለ

ፕሬዚዳንት ማክሮን ከጀርመን ባለስልጣን ጋር

የፎቶው ባለመብት, EPA

ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ አስርት አመታትን እንደሚወስድ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስታወቁ።

ፕሬዚደንቱ በስትራስቡርግ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ዩክሬን ውሳኔውን እየጠበቀች በምትኩ ወደ ትይዩው የአውሮፓ ማህበረሰብ ልትቀላቀል እንደምትችል ጠቁመዋል።

ይህም ሁኔታ የአውሮፓ ህብረት አባል ያልሆኑ አገራት የአውሮፓን የደህንነት መዋቅር በሌላ መንገድ እንዲቀላቀሉ ያስችላቸዋል ብለዋል ፕሬዚዳንት ማክሮን።

የፕሬዚዳንቱ ንግግር የተደመጠው ሩሲያ ምስራቃዊ ዶንባስን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፍልሚያ እያደረገችበት ባለችበት ወቅት ነው።

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መከላከያ ባለስልጣን የሩሲያን ግስጋሴ "አንድ አሃዝ ያለው የኪሎ ሜትር እርምጃ" ሲሉ ገልጸውታል። በሉሃንስክ ግዛት የሚገኙ የዩክሬን ባለስልጣን በበኩላቸው ከባድ ጦርነቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዩክሬን ለአውሮፓ ህብረት አባልነት ጥያቄ ያቀረበችው በዚህ አመት የካቲት ወር ላይ ከሩሲያ አራት ቀናት ወረራ በኋላ ነው።

"ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል እንድትሆን የመፍቀድ ሂደት ብዙ አመታትን ምናልባትም በርካታ አስርት ዓመታትን እንደሚወስድ ሁላችንም በሚገባ እናውቃለን" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

አክለውም " የአባልነት መስፈርቶችን ዝቅ ለማድረግ ካልወሰንን በስተቀር እውነታው ይህ ነው። የአውሮፓ አንድነትን በሌላ መልኩ ልናስበው ይገባል" ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዩክሬንን የአውሮፓ ህብረት አባል ለማድረግ የአውሮፓ ህብረት ጥብቅ የአባልነት መስፈርቶችን ከማስተካከል ይልቅ "ትይዩ የአውሮፓ ማህበረሰብ" ሊታሰብበት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህ ትይዩ የአውሮፓ ማህበረሰብ "በአውሮፓ ውስጥ ያሉና የእኛን እሴቶች የሚጋሩትን አንድ ላይ የማምጣት መንገድ ነው" ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌር፣ በሰኔ ወር በዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባልነት ጥያቄ ላይ የህብረቱ ስራ አስፈጸሚ የመጀመሪያ ምላሹን በጽሁፍ ይሰጣል ብለው ነበር።

የዩክሬን ባለስልጣናት ሰኞ እለት እንዳረጋገጡት ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት የአባልነት ማመልከቻ ሁለተኛውን ጥያቄ ለብራሰልስ ማቅረቧን አስረድተዋል።