ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በአፍሪካ ህብረት ንግግር ለማድረግ በድጋሚ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በአፍሪካ ህብረት መሪዎችን ለማነጋገር በድጋሚ ጥያቄ እንዳቀረቡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ አስታውቀዋል።
ሊቀ መንበሩ በትዊተር ገጻቸው እንዳሰፈሩት ጥያቄው የመጣው ከዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ነው።
በዚህ ውይይት ላይ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ "ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የጠበቀ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት" እንዳላቸውም መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ተገልጿል።
ፋኪ የፕሬዚዳንቱ ጥያቄ ተቀባይነት ይኖረው እንደሆነ ያልገለጹ ሲሆን ነገር ግን "ከሩሲያ ጋር ላለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አጥብቀው መናገራቸውን" በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ለሴኔጋሉ አቻቸውና ለወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል የአፍሪካ መሪዎችን ለማነጋገር ጥያቄ አቅርበው ነበር።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሩሲያ ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት እንድትታገድ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጽ ያልሰጡ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ የአፍሪካ ሀገራት የበላይነቱን መያዛቸው ይታወሳል።
ውሳኔው በ93 ድጋፍ፣ በ24 ተቃውሞ እና በ58 ድምጸ ተአቅቦ ጸድቋል።
በአህጉሪቱ ከሚገኙት 54 ሀገራት አንጎላ፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ 24ቱ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።
ከሩሲያ ጋር በታሪክ ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው አልጄሪያ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኙ እርምጃውን ተቃውመዋል። ሌሎች 11 አገራት ድምፃቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል።
10 ሃገራት ብቻ የሩሲያን ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መታገድ ደግፈዋል። እነዚህም ቻድ፣ ኮሞሮስ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሊቢያ፣ ማላዊ እና ሲሼልስ ነበሩ።
አፍሪካ ሩሲያን ለመደገፍ ዝንባሌ የምታሳየው ለምንድነው?
በተባበሩት ጠቅላላ ጉባኤው ሩስያን በመቃወም ሁለት ጊዜ ድምጽ ከመስጠት የተቆጠበችው የአህጉሪቱ ትልቁ ኢኮኖሚ ደቡብ አፍሪካ በኩል የተሰጡት አስተያየቶች በተወሰነ መልኩ ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
"ግጭቱ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የአለም አቀፉን ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ተልዕኮውን መወጣት አለመቻሉን አጋልጧል" ሲል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጠቅሶ ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካን ያካተተውና አምስት ቋሚ አባላት ያሉት የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባልነት "ጊዜ ያለፈበት እና የማይወክል ነው" ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶርም የአገራቸውን ገለልተኝነት አቋም አስመልክቶ በመደገፍ የተከራከሩ ሲሆን ግጭቱ "የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ኢ-ፍትሃዊነት" አሳይቷል ሲሉም ተናግረዋል።












