ሩሲያ ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መታገድ ላይ የአፍሪካ አቋም

ጦርነቱ ይቁም የሚል ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን የጦር ወንጀሎች ፈፅመዋል መባሉን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያን ከተመድ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት እንድትታገድ ሃሙስ እለት ድምጽ ሰጥቷል ፤ ነገር ግን የአፍሪካ ዲፕሎማቶች እርምጃውን ብዙም አልደገፉትም።

በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ለማውገዝ በተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከተሰጠው ድምጽ ጋር ሲነጻጸር፣ በአሁኑ በርካታ የአፍሪካ አገራት ውሳኔውን ተቃውመው ድምጽ ሰጥተዋል።

በአህጉሪቱ ከሚገኙት 54 ሀገራት አንጎላ፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ 24ቱ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።

ከሩሲያ ጋር በታሪክ ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው አልጄሪያ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኙ እርምጃውን ተቃውመዋል። ሌሎች 11 አገራት ድምፃቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል።

10 ሃገራት ብቻ የሩሲያን ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መታገድ ደግፈዋል። እነዚህም ቻድ፣ ኮሞሮስ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሊቢያ፣ ማላዊ እና ሲሼልስ ነበሩ።

አፍሪካ ሩሲያን ለመደገፍ ዝንባሌ የምታሳየው ለምንድነው?

በተባበሩት ጠቅላላ ጉባኤው ሩስያን በመቃወም ሁለት ጊዜ ድምጽ ከመስጠት የተቆጠበችው የአህጉሪቱ ትልቁ ኢኮኖሚ ደቡብ አፍሪካ በኩል የተሰጡት አስተያየቶች በተወሰነ መልኩ ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

"ግጭቱ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የአለም አቀፉን ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ተልዕኮውን መወጣት አለመቻሉን አጋልጧል" ሲል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጠቅሶ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካን ያካተተውና አምስት ቋሚ አባላት ያሉት የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባልነት "ጊዜ ያለፈበት እና የማይወክል ነው" ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶርም የአገራቸውን ገለልተኝነት አቋም አስመልክቶ በመደገፍ የተከራከሩ ሲሆን ግጭቱ "የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ኢ-ፍትሃዊነት" አሳይቷል ሲሉም ተናግረዋል።