አሜሪካ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያዘጋጀቻቸው ረቂቅ ሕጎች ውሳኔ ምን ላይ ደረሰ?

የፎቶው ባለመብት, congress.gov
የአሜሪካ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም እና ለደረሱት ጥፋቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ተጽዕኖ ይፈጥራሉ ያለቻቸው ረቂቅ ሕጎች እንዲዘገዩ ተወስኗል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ቢሆንም ቢቢሲ ግን ጉዳዩ አሁንም ሂደት ላይ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች አግኝቷል።
ቢቢሲ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ጉዳይ ኮሚቴን ጉዳዩን እንዲያብራራ ጥያቄ አቅርቦ ጉዳዩ በመደበኛ ሂደት ላይ መሆኑን የሚጠቁም ምለሽ አግኝቷል።
ከእነዚህ ረቂቅ ሕጎች መካከል 'ኤችአር6600 የኢትዮጵያን ሰላም ዲሞክራሲ እና መረጋጋት መደገፍ' በሚል የተዘጋጀ ረቀቂ ሕግ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
የአሜሪካ ሴኔት ደግሞ በኢትዮጵያ ሰላም እና ዲሞክራሲ ለማበረታታት ወይም 'The Ethiopia Peace and Democracy Promotion Act' በሚል ያረቀቀውንና ኤስ3199 የተሰኘው ረቂቅ ሕግ በሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ተመርቷል።
የእነዚህ ረቂቅ ሕጎች መዘጋጀት ከተሰማ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ለሰብዓዊነት በሚል የተኩስ አቁም ያወጀ ሲሆን ሲሆን ሰብዓዊ እርዳታም ወደ ትግራይ እንዲጓዝ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ እነዚህ ረቂቅ ሕጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገቡ፣ በተለይ ደግሞ የሰላም ሂደቱን አስተዋጽኦ የማያበረክቱ እንደሆኑ በማንሳት የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገሩን ጠቁመው ነበር።
በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ረቂቆቹ እንዳይፀድቁ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ በአሜሪካ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በርግጥ ረቂቅ ሕጎች እንዲዘገዩ ተወስኗል?
ባለፉት ሁለት ቀናት የሕግ ረቂቆቹ በአሜሪካ ኮንግረስ ከመጽደቅ እንዲዘገዩ ተወስኗል የሚሉ መረጃዎች በአገር ውስጥ ሚዲያዎች በስፋት ተዘግበዋል።
እነዚህ የሚዲያ ተቋማት ለዚህ ዘገባቸው 'ኢትዮጵያን አሜሪካን ሲቪል ካውንስልን' በመረጃ ምንጭነት በመጠቀም እንዲዘገይ ተወስኗል ብለዋል።
ይህንን ዘገባም ገዢው ፓርቲ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ አጋርቷል።
ከዚህ በተቃራኒ ግን የረቂቅ ሕጎቹ በመደበኛ የሕግ የማርቀቅ ሂደት ውስጥ እያለፉ መሆኑን አንዳንድ የአሜሪካ ሴናተሮች እና ጉዳዩን የሚከታተሉ ሌሎች ሰዎች ጽፈዋል።
ቢቢሲ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ጉዳይ ኮሚቴን ጉዳዩን እንዲያብራራ ጥያቄ አቅርቦ ጉዳዩ በመደበኛ ሂደት ላይ መሆኑን የሚጠቁም ምለሽ አግኝቷል።
የኮሚቴው ኮሙኑኬሽን ቡድን ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ረቂቅ ሕጎቹ እንዲዘገዩ ተወስኗል በሚለው ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ምላሽ አልሰጠም።
ይሁን አንጂ በእነዚህ በረቂቅ ደረጃ ባሉ ሕጎች ላይ በመንተራስ ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ ኮሚቴው ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጿል።
"በእነዚህ ሕጎች በመጠቀም የአሜሪካ አስተዳደር የእርስ በእርሱ ጦርነቱ እንዲቀጥል፣ ሰብዓዊ እርዳታ እነዳይደርስ የከለከሉ፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈፀሙ ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ቁርጠኝነት አለ" ብሏል።
በዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ፍፁም አረጋ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው "በመንግሥታችን በጎ እርምጃዎች በዲያስፖራው ጥረት እና በለጋሾች ትብብር የሰብዓዊ አቅርቦት እየተሻሻለ በመምጣቱ በአሜሪካ ሁለቱ ምክር ቤቶች ሲታዩ የነበሩ ረቂቅ ሕጎች 'ለጊዜው ባሉበት እንዲቆዩ' የሚለው ሃሳብ በውስጣቸው መንሸራሸሩ መልካም ነው" ብለዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 1
አምባሳደር ፍፁም እነዚህ ረቂቅ ሕጎች እንዲዘገዩ ውሳኔ ተላልፏል ሲሉ በግልጽ አላስቀመጡም።
"ጉዳዩ ገና ውሳኔ ያላገኘ በመሆኑ የማዕቀብ አጀንዳው እስኪወገድ ድረስ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።" በማለት አስፍረዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምሳደር የነበሩት ቲቦርናዥ በትዊተር ገጻቸው ላይ የአሜሪካው ኮንግረስ 'ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዲሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት' ላይ ተጨማሪ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቧል በማለት እንዲዘገይ መደረጉን ጠቁመዋል።
"የተኩስ አቁሙ እንዴት እንደሚሄድ ማየት እና አካባቢው ለሰብዓዊ ርዳታ ሙሉ በሙሉ ክፍት መሆኑን ለማረጋገጥ ሲባል" ረቂቆቹ ከመጽደቅ መዘግየታቸውን በምክንያትነት ገልፀዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 2
ሌላው የምክር ቤቱ የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ አባል የሆኑት የኢዳሆ ተመራጭ ጂም ሪሽ በትዊተር ገጻቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ምዕራብ ትግራይ ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጽዳት ወንጀል አስመልከቶ ያወጣጡት ሪፖርት አስከፊ መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ኤስ3199 ዓይነት ረቂቅ ሕጎቹን አስፈላጊነት ጠቁመዋል።
ሴናተሩ ሁለቱ ኢትዮጵያን የተመለከቱት ረቂቅ ሕጎች "በመደበኛ የሕግ አካሄድ ውስጥ እያለፈ ነው" ብለዋል ሴናተሩ።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 3
ረቂቆቹ እንዲዘጋጁ ሲወተውቱ ከነበሩ አንዷ የሆኑት እና ኦላ የተሰኘ የአድቮኬሲ ድርጅት መስራቿ ሴና ጂምጂሞ ረቂቆቹ እንዲዘገዩ ተወስኗል ለሚለው "በፍፁም እውነት አይደለም" በማለት ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የረቂቁ ዝግጅት ብዙ አካላትን ያሳተፈ እና ምክክር የተካሄደበት እንደመሆኑ እንዲዘገይ ሲወሰንም ባለድርሻ አካላት ይወያዩበት ነበር በማለት ዘገየ መባሉን ሐሰት መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አሜሪካን ሲቪልካውንስል ቃል አቀባይ አቶ አምሳሉ ካሳሁን የሕዘብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ለውጥ፣ የተኩስ አቁም እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዳይደናቀፍ ተዘጋጅቶ የነበረውን ረቂቅ አዋጅ ከማጽደቅ ለማዘግየት መወሰኑን መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የቀረበውና ባለፈው ሳምንት ወደ መወሰኛው ምክር ቤት የተመራው ኤስ3199 ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ ሰላም እና መረጋጋትን ለመደገፍ የአሜሪካ አስተዳደር ዲፕሎማሲያዊ፣ ልማታዊ እና ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅና ይህንንም ሂደት እያደናቀፉ ያሉ አካላት ላይ አስተዳደሩ ማዕቀብ የሚጥልበትን ማዕቀፍ ለመፍጠር ማለሙንም አሜሪካ አስታውቃለች።
ለኢትዮጵያ መንግሥት በፀጥታ ጉዳዮች ላይ አሜሪካ የምትሰጠውን ድጋፍ ከማገድ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ፣ ከጦርነቱ የሚያተርፉ እንዲሁም ጦርነቱ እንዲባባስ በገንዘብ እንዲሁም በቀጥታ የተሳተፉ አካላት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ነው።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የተመለከተው ኤችአር 6600 ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ከግጭት ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሶች ላይ ማዕቀብ መጣል ያስችላል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ የተቃወማቸው እነዚህ ረቂቅ ሕጎች በፕሬዝዳንት ባይደን የሚጸድቁ ከሆነ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ/በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ትጥላለች












