የጋና የነፃነት አባት ክዋሜ ንክሩማህ እንደገና ሊቀበሩ ነው

ክዋሜ ንክሩማህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጋናን ለነፃነት ያበቁትና የመጀመሪያ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ እንደገና ሊቀበሩ መሆኑን የጋና ፓርቲ አስታውቋል።

የጋና መሥራች ክዋሜ ንክሩማህን በኅዳር ወር ለመቅበር ዕቅድ እንደተያዘም ተቃዋሚው ኮንቬንሽን ፒፕልስ ፓርቲ (ሲፒፒ) ነው ይፋ ያደረገው።

በነፃነት ዘመን ገዥ የነበረው ይህ ፓርቲ እንዳለው በአውሮፓውያኑ 1972 የነበረው የታላቁ መሪ ክዋሜ ንክሩማህ ሥርዓተ ቀብር እዚህ ግባ የማይባል ነው።

ተገቢው የቀብር ስሥርዓት ባለመፈጸሙም "ነፍሳቸው አሁንም እረፍት አጥታለች" ሲልም አትቷል።

የተባበረች አፍሪካን በማለም እንዲሁም አገራቸውን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ተላቃ ነጻነቷን እንድታገኝ ያደረጉት ንክሩማህ ሕይወታቸው ያለፈው ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ነበር።

በሮማንያዋ ቡካሪስት ሕክምና ሲደረግላቸው ከቆየ በኋላ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ የተቀበሩትም በደቡባዊ ጋና በምትገኘው ንክሮፉል መንደር ነበር።

በኋላም አስከሬናቸው በመዲናዋ አክራ ወደሚገኝ መካነ መቃብር ተወስዷል።

የሲፒፒ ፓርቲ የንክሩማህ እውነተኛ የቀብር ሥነ ሥርዓት አፈጻጸምን በተመለከተ መርሃ ግብር ይፋ አደርጋለሁ ብሏል።

የንክሩማህ አፅም መቼ ተቆፍሮ እንደሚወጣ እንዲሁም የት ቦታ እንደሚቀበሩ ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥቧል።

የአገር ውስጥ ሚዲያ የሆነው ጆይ ኒውስ የፓርቲው ዋና ጸሃፊ ናና ያ ጃንቱህ በድጋሚ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሰጡትን አስተያየት የሚያሳይ ቪዲዮ አትሟል።