ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ለተተኪያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላለፉ

የፎቶው ባለመብት, State House Kenya
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ነሐሴ 3፣ 2014 ዓ.ም በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላሸነፉት ዊሊያም ሩቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላለፉ።
አንጋፋው ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ ቀጣዩ የኬንያ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ድጋፋቸውን የሰጡት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ዛሬ መስከረም 3፣ 2015 ዓ.ም በሚደረገው ቃለ መሓላ ስነ ስርዓት እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ይህንን የተናገሩት የአስተዳደራቸውን ቁልፍ ስኬቶች አስመልክቶ በነበረው ንግግራቸው ነው።
ባለፈው ሳምንት የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዊሊያም ሩቶን አሸናፊነት የሚቃወሙ በርካታ አቤቱታዎችን ውድቅ በማድረግ ቀጣዩ ፕሬዚዳንትነታቸውን አፅንቷል።
ኡሁሩ ኬንያታ በስልጣን ዘመናቸው ሃገሪቱ ለውጥ እንዳመጣች በመግለፅ ተተኪያቸው የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖራቸውንም ሁሉንም ኬንያውን በእኩልነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ የአስተዳደራቸው ዘመን ስኬቶች በሚል ከጠቀሷቸው መካከል ማዕከላዊ ስልጣንን ወደተለያዩ ግዛቶች እንዲከፋፈል ማድረግ እንዲሁም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አባል እንድትሆን ማስቻል ነው።
ማክሰኞ መስከረም 3፣ 2015 ዓ.ም የሚደረገውን የስልጣን ሽግግር በበላይነት እንዲከታተል የተመደበው ቡድን በስነ ስርዓቱ ላይ ከ20 በላይ የሃገር መሪዎች ተጋዘብዘዋል ሲል ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጿል።








