ህወሓት ግጭት ለማስቆም የፀጥታው ምክር ቤት “በኃይል ጣልቃ” እንዲገባ ጠየቀ

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ላለፉት 22 ወራት ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የትግራይ ኃይሎች “ዳግም የተከፈተብን” ያሉትን ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት “በኃይል ጣልቃ ገብቶ” ያስቁም ሲሉ ጠየቁ።
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ለወቅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ በጻፉት ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች የተቀናጀ እና መጠነ ሰፊ ጥቃት ትግራይ ላይ ከፍተዋል ብለዋል።
ደብረጺዮን በደብዳቤያቸው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኃይል ጣልቃ ገብቶ የኤርትራ ሠራዊትን ከኢትዮጵያ ካላስወጣ፣ ግጭት ካላስቆመ፣ በክልሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ ካለስጀመረ “የትግራይ ሕዝብ በእነዚህ ሁለት ጨካኝ ሠራዊቶች ይጠፋል” ብለዋል።
የህወሓት ሊቀመንበሩ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ለተመድ ደብዳቤ ሲጽፉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ሊቀመንበሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሠራዊት ግጭት እንደ አዲስ ለመጀመር የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ነው ሲሉ ደብዳቤ ጽፈው ነበር።
ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል ተኩስ አቁመው ጦርነቱ ለአምስት ወራት ያክል ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደ አዲስ መቀስቀሱ ይታወሳል።
ለጦርነት መቀስቀስ አንዱ ሌላኛውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የጦርነት ተጠናክሮ መቀጠል
ይህ ጦርነት ለሦስተኛ ዙር ካገረሸ በኋላ በደቡብ፣ በምዕራብ እና በሰሜን ትግራይ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ እንደሚገኝ እየተገለጸ ነው።
የህወሓቱ ሊቀመንበር ይህን ደብዳቤ የጻፉት ጦርነቱ ማገርሸቱን ተከትሎ የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር አዲስ አበባ በሚገኙበት ጊዜ ነው።
ማይክ ሐመር ኢትዮጵያ ከደረሱ በኋላ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጋር መነጋገራቸውን እና ተመሳሳይ መልዕክት ለህወሓት ሊቀመንበር ማስተላለፋቸውን አንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ትናንት ገልጸዋል።
ደብረጺዮን (ዶ/ር) ለተመድ በጻፉት በዚህ ደብዳቤ፣ የፌደራሉ መንግሥት በደቡብ ግንባር (ቆቦ)፣ በደቡብ ምዕራብ ግንባር (ሰቆጣ) እና በምዕራብ ግንባር ከፍተኛ ሠራዊት አሰማርቷል ያሉ ሲሆን፣ በእነዚህ እና በሌሎች ስፍራዎች ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠዋል።
“የሰላም ሂደቱ ፈርሷል” ያሉት ደብረጺዮን (ዶ/ር) ይህ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ከዚህ በፊት ከነበሩት በላይ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ እልቂትን ይፈጥራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን (ዶ/ር) በተመድ ጥረት ግጭት ካቆመ በኋላ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በባለሙያዎች የተደገፈ ዓለም አቀፍ የአደራዳሪዎች ቡድን እንዲሰየም ጠይቀዋል።
በአፍሪካ ኅብረት ልዑካን ተወካዮች ላይ ያለንን አቋም ከዚህ ቀደም ግልጽ አድርገናል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ በተመድ የሚሾሙት አደራዳሪ ቡድን አባላት በእኛ ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ክትትል የሚድረግባቸው፣ ጥፋተኞች ተጠያቂ የሚሆኑበት እና የጊዜ ሰሌዳ ያለው የሰላም ሂደት የመርህ ስምምነት መደረስ አለበት ሲሉም ደብረጺዮን ጠይቀዋል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለወራት ቆሞ የነበረ ሲሆን ባለፈው ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም ዳግም መቀስቀሱ ይታወሳል።
በተለያዩ ወገኖች ሲካሄድ የነበው የሰላም ጥረት ውጤት ሳያመጣ የቆየ ቢሆንም፣ ጦርነቱ ዳግም ካገረሸ በኋላ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መንግሥት እና ህወሓት ተኩስ አቁመው ድርድር እንዲጀምሩ አጥብቀው እየጠየቁ ነው።












