ተመትቶ ወደቀ ስለተባለው አንቶኖቭ አውሮፕላን ምን የሚታወቅ ነገር አለ?

አንቶኖቭ-32 የተባለው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Indian air force

የምስሉ መግለጫ, አንቶኖቭ-32 የተባለው የአንቶኖቭ አውሮፕላን አይነት (የሕንድ)

በተለይ ለወታደራዊ ማጓጓዣነት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው አንቶኖቭ አውሮፕላን በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ለዓለም የተዋወቀ ግዙፍ አውሮፕላን ነው።

አውሮፕላኑ ካለው የመጫን አቅም የተነሳ አገራት ወታደሮችን፣ ትጥቅ እና ስንቅን ለማጓጓዝ ለወታደራዊ አገልግሎት ይጠቀሙበታል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት ይህ ግዙፍ ወታደራዊ የማጓጓዣ አውሮፕላን ያላቸው ሲሆን፣ በአብዛኛው በአገራት አየር ኃይል ስር የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

ስለዚህም እነዚህ ግዙፍ የጭነት ወታደራዊ አውሮፕላኖች ጦርነት እና የሠራዊት እንቅስቃሴዎች ባሉባቸው ስፍራዎች መታየታቸው የተለመደ ነው።

በቅርቡም ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት በሚካሄድበት የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ እነዚህ አንቶኖቭ አውሮፕላኖች ታይተዋል መባሉ በስፋት መነጋገሪያ ሆኗል።

ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ደግሞ ፈቃድ ያላገኘ አንቶኖቭ አውሮፕላን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ከገባ በኋላ፣ በአገሪቱ አየር ኃይል ተመትቶ መውደቁን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አሳውቋል።

መንግሥት፤ አውሮፕላኑ ስማቸውን ባልጠቀሳቸው “የአገሪቱ ጠላቶች” አማካይነት የትጥቅ ድጋፍ የማቅረብ አላማ ነበረው ሲል ብሏል።

ለመሆኑ አንቶኖቭ የተሰኙት የጭነት አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ ክልል እየገቡ ነበር? በቅርቡ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ተመትቷል ስለተባለው አውሮፕላን ምን የሚታወቅ ነገር አለ?

“ተሽሎክሉከው የሚገቡ አውሮፕላኖች”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከመላው አገሪቱ ከተሰባሰቡ ወጣቶች ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ ወደ ትግራይ ክልል አውሮፕላኖች በድብቅ ሲገቡ እንደነበር ተናግረዋል።

“ባለፉት ጥቂት ወራት ጥቂት አውሮፕላኖች ሌሊት ተሽሎክሉከው ሽሬ እየገቡ ትጥቅ ያሳርፋሉ። አንዱም ሚዲያ ነግሮን አያውቅም። በእነሱ ሒሳብ እኛም አናውቀውም” ብለው ነበር።

ነገር ግን የጦር መሳሪያ ጭነው ወደ ትግራይ ሲገቡ ነበር ባሏቸው አውሮፕላኖች ላይ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ስለኖሩ የገለጹት ነገር የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ከተናገሩ ከቀናት በኋላ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም ምሽት አን-26 የተሰኘ አንቶኖቭ አውሮፕላን መትቶ መጣሉን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው በወቅቱ እንዳሉት፣ አውሮፕላኑ በሱዳን በኩል የጦር መሳሪያዎችን ጭኖ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ ተመትቶ መውደቁን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የአገሪቱን የአየር ክልል ጥሶ ገባ የተባለውን አንቶኖቭ 26 አውሮፕላንን በተመለከተ፣ በአገር ውስጥ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ቀርበው አስረድተዋል።

በወቅቱ አውሮፕላኑ የተመታበት ጊዜ እና ቦታ በሚመለከት እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃ የወጣ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው “የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ንብረት የሆነው አውሮፕላን መሣሪያ ጭኖ መቀለ ሲያራግፍ” ተመቷል ብለው ነበር።

ነገር ግን ሁሉም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ “የጦር መሳሪያዎችን ጭኖ ለህወሓት ሊያደርስ ነበር” ሲል ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ አማፂው ኃይል ህወሓት በቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ አማካይነት “ይህ ፍፁም ሐሰት ነው” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ሶቪየት ሰራሹ አን-26 አውሮፕላን (የማሌዢያ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሶቪየት ሰራሹ አን-26 አውሮፕላን (የማሌዢያ)

ተመታ የተባለው አውሮፕላን

በአውሮፕላኖች እና በረራዎችን ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን በመከታተል እንዲሁም በመተንተን የሚታወቁት ኼርዮን፤ ከአንቶኖቩ ክስተት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሰጠው መረጃ “በቂ ባይሆንም ትክክለኛ ነው” የሚል ዕምነት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአየር ኃይል አዛዡ በማስረጃ የተደገፈ መግለጫ በመስጠት መንግሥት አውሮፕላኑን መትቶ መጣሉን አስረድተዋል።

የአቪዬሽን ተንታኙ እንደሚሉት ይህ አን-26 የተሰኘው አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር የገባው በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1፡50 ላይ ነው።

ኼርዮን፤ አውሮፕላኑ ወደ ምሥራቅ በማቅናት ወደ ደቡባዊ ሽሬ ቀጥሎም ወደ አክሱም አምርቷል፣ “ከዚያ በኋላም የኢትዮጵያን ራዳር ሽፋንን ጥሎ ቢወጣም የበረራውን አቅጣጫ በማየት ወደ መቀለ እያቀና እንደነበረ መናገር ይቻላል” ይላሉ።

ከዚያም በኋላ ከምሽቱ 3፡14 ገደማ አውሮፕላኑ መጨረሻ የታየበት ምዕራባዊ መቀለ አካባቢ ድጋሚ መታየቱን፣ ቀጥሎም ወደ ሱዳን ድንበር ሊያቀና እንደሚችል ተንታኙ ያስረዳሉ።

የአየር ኃይል አዛዡ እንደሚሉት አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀው 3፡30 ገደማ ነው።

ኼርዮን እንደሚሉት የአየር ኃይል አዛዡ አውሮፕላኑ ከራዳር ከጠፋ በኋላ ምን እንደተፈጠረ ግልፅ ባያደርጉም፣ “የአንቶኖቩን የመብረር ፍጥነትን በማጤን መግለጫቸው ትክክል ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

አን-26 ተመትቶ የወደቀው በሩሲያ ሰራሹ ሱ 27 የጦር አውሮፕላን እንደሆነ፣ ቱርክ ሰራሹ ባያራክታር ቲቢ2 ሰው አልባ አውሮፕላን ደግሞ ድንበር አቋርጦ የገባውን አንቶኖቭ የሚያሳዩ ምስሎችን ማንሳቱ ይነገራል።

ይህን ክስተት በዝርዝር መርምረው በድረ-ገፃቸው ላይ የፃፉት የአቪዬሽን ተንታኙ እንደሚያጠቃልሉት “የኢትዮጵያ አየር ኃይል መግለጫ ትክክለኛ ይመስላል፤ ከሱዳን ወደ ትግራይ ክልል በረራዎች የመኖራቸው ዕድልም ሰፊ ነው” ይላሉ።

ከኢትዮጵያ አየር ኃይል የወጣ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, fana

የምስሉ መግለጫ, ከኢትዮጵያ አየር ኃይል የወጣ ፎቶ

ወደ ትግራይ ድብቅ በረራዎች ነበሩ?

ክራይሲስ ግሩፕ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዊሊያም ዴቪሰን ወደ ትግራይ በድብቅ ሲደረጉ ነበሩ የተባሉት በረራዎች ምን እንደጫኑ ባይታወቅም ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ትግራይ ክልል በረራዎች ሲካሄዱ ነበር ሲሉ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግረዋል።

ዊሊያም ዳቪሰን “አዎ ያልኩት ነገር ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። ወደ ትግራይ ክልል ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ሲገቡ እንደነበር መረጃው አለኝ” ብለዋል።

ዊሊያም ከዚህ ባለፈ በረራዎቹ ከየት ይነሱ እንደነበር፣ አሊያም ንብረትነታቸው የማን እንደሆነ የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ተመራማሪው አክለው “በተለይ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ካየነው ጦርነት በኋላ ሁለቱም ወገኖች አቅማቸውን እያጠናከሩ ነበር። ሁለቱም ወገኖች ምልመላ፣ ሥልጠና እና የመሣሪያ ግዥ ሲያደርጉ እንደነበር አምናለሁ” ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ከወጣቶች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ባደረጉት በንግግር፣ የጦር መሣሪያ የጫኑ አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ ክልል ሲገቡ እንደነበር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወደ ትግራይ ክልል ይገቡ የነበሩ አውሮፕላኖች ስለመኖራቸው መረጃው ይኖረው እንደሆን ለመጠየቅ ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የአቪዬሽን ተንታኙ ኼርዬን የተኩስ አቁም በነበረበት ወቅት ወደ ትግራይ ክልል “እርዳታ ከጫኑ የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች፣ የሳማሪታንስ ፐርስ ዲሲ-8 ከተሰኘ እርዳታ ጫኝ አውሮፕላኖች ውጪ ሌላ መረጃ የለኝም” ይላሉ።

ታዛቢዎች እንደሚሉት ጦርነቱ ጋብ ብሎባቸው በነበሩት ወራት ውስጥ ሁለቱም ወገኖች ድጋሚ ላገረሸው ጦርነት ሲሰናዱ ነበር።

በስትራቴጂክና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ካሜረን ሃድሰን “ሁለቱም ወገኖች ወደ ግጭት ሊመለሱ እንደሚችሉ አምን ነበር” ይላሉ።

“ድርድሩ መሬት ላይ የረባ የሚባል ለውጥ ባለመምጣቱ መልሰው ጦርነት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ፍንጮች ነበሩ።”

አሜሪካዊው ተንታኝ ይህን ይበሉ እንጂ ከሁለቱም ወገን ለወራት ትልቅ ዝግጅት ነበር ማለት ይከብዳል ባይ ናቸው።

“ህወሓት ጠንከር ያለ ዕቅድ ቢኖረው ኖሮ ነዳጅ ያከማች ነበር። ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጅ መውሰዳቸው ሙሉ ዝግጅት እንዳላደረጉ ያሳያል” ይላሉ ሃድሰን።

“መንግሥትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖችን ተጠቅሞ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ መሣሪያ ልኳል ተብሎ ይወቀሳል። ነገር ግን ዕቅዱ ቢኖረው ወታደራዊ መንገዶችን ተጠቅሞ ሠራዊቱን በተጠንቀቅ ማቆም ይችል ነበር” ሲሉ ለጦርነት ዝግጅት ነበረ በሚለው ሐሳብ ላይ ጥርጣሬያቸውን ይገልጻሉ።

ድንበር ጥሶ ስለገባው አውሮፕላን የበረራ መስመር የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያመላከተበት ካርታ

የፎቶው ባለመብት, fana

የምስሉ መግለጫ, ድንበር ጥሶ ስለገባው አውሮፕላን የበረራ መስመር የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያመላከተበት ካርታ

አውሮፕላኖች ከራዳር ዕይታ ውጪ መብረር ይችላሉ?

የኢትዮጵያ መንግሥት መትቼ ጥየዋለሁ ያለው አንቶኖቭ አውሮፕላንም ሆነ፣ የክራይሲስ ግሩፑ ተመራማሪ ዊሊያም ዴቪሰን ወደ ትግራይ ገብተዋል ያሏቸው አውሮፕላኖች ግዙፍ የሚባሉ ናቸው።

ዊሊያም ዴቪሰን “ምንም እንኳ ውስጣቸው ምን እንዳለ ዕውቀቱ ባይኖረኝም አውሮፕላኖች ዕቃ ጫኝ [ካርጎ] ናቸው” ይላሉ።

አንቶኖቭ፣ ቦይንግ እና ኤይርባስ የሚያመርቷቸው ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች በአማካይ 70 ሜትር ርዝመት ያላቸው ክንፋቸው ደግሞ 73 ሜትር የሚረዝሙ ናቸው።

ለመሆኑ መሰል ግዙፍ አውሮፕላኖች ከራዳር ዕይታ ውጪ መብረር ይችላሉ?

የቢቢሲው ክሪስ ፓርትሪጅ አንቶኖቭ አውሮፕላኖች ከራዳር ዕይታ ውጪ የመሆን ዕድላቸው በጣም የጠበበ ነው ይላል።

አልፎም እኒህ ግዙፍ አውሮፕላኖች በጦር ጄቶች አሊያም ከየብስ በሚወነጨፍ ሚሳዔል ሊመቱ ይችላሉ ሲል ይተነትናል።

በሌላ በኩል የአቪዬሽን ተንታኙ ኼርዬን እንደሚሉት እንደ አንቶኖቭ ያሉ ግዙፍ አውሮፕላኖች ‘ትራንስፖንደር’ [መቆጣጠሪያቸውን] ቢያጠፉ እንኳ በቅርብ ያለ የአየር ትራፊክ ተቀጣጣሪ ሊያያቸው ይችላል።

“አን-26 አውሮፕላን በጣም ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ የአውሮፕላኑ ዓይነት ባይታወቅ እንኳ በራሪ መኖሩን በራዳር መመልከት ይቻላል።”

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የቀድሞ የኤርትራ አየር ኃይል አባል ደግሞ “ወፍ እንኳ” ቢሆን በራዳር ዕይታ ውስጥ ይገባል በማለት ከዕይታ ውጪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ያስረግጣሉ።

ባለሙያው ራዳሮች እስከ 3500 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ የማየት አቅም እንዳለቸው በማመልከት፣ ግዙፉ አውሮፕላን ከቁጥጥር ውጪ መሆን የማይችልበትን ሁኔታ ያብራራሉ።

“አንድ በራሪ ቁስ ከ400 መቶ ጫማ በታች ከበረረ ከራዳር ዕይታ ውጪ ሊሆን ይችላል። አንቶኖቭ አውሮፕላኖች ደግሞ በዚህ ዝቅታ መብረር አይችሉም” ይላሉ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባይራክታር ቲቢ2 ድሮም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባይራክታር ቲቢ2 ድሮን

ሱዳን ምን አለች?

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚዋሰነው ክልል ውስጥ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ተመትቶ ወድቋል የተባለው አውሮፕላን፣ ከሱዳን በኩል የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ መግባቱ ተነግሯል።

ይህም በግልጽ ወጥቶ አይሰማ እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ባሉት መስመሮች ከሱዳን በኩል ማብራሪያ ሳይጠይቅ እንደማይቀር ይታመናል።

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንዲሁም በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ያለችው የሱዳን ክስተቱን አስተባብላላች።

የአውሮፕላኑ ተመትቶ መውደቅ ዜና እንደተሰማ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ናቢል አብደላህ ለብሉምበርግ እንደተናገሩት “ሱዳን ከዚህ ክስተት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላትም” ሲሉ አስተባብለዋል።

የአየር ክልል ጥሶ በመግባቱ ተመትቶ ወድቋል ከተባለው አውሮፕላን ጋር በተያያዘ እስካለፈው ማክሰኞ ድረስ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ይፋ የወጣ ውዝግብና መወነጃጀል አልተሰማም።

ነገር ግን ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 24/2014 ዓ.ም. አንቶኖር አውሮፕላኑን በተመለከተ ሱዳን በካርቱም የሚገኙትን የኢትዮጵያን አምባሳደር ጠርታ አነጋገግራለች።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ሰጥተውታል በተባለው መግለጫ ደስተኛ ባለመሆኑ ነው አምባሳደሩን የጠራው።

የሱዳን መንግሥት ዜና ወኪል፣ ሱና እንደዘገበው አምባሳደር ይበልጣልን ያነጋገሩት፣ በሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፋደለ አብዱላህ ፋደለ ሲሆኑ፣ አምባሳደሩ ለመገናኛ ብዙኃን የሰጡትን አስተያየት እንዲያስተባብሉ ጠይቀዋል።

ከዚህ በዘለለ ግን እስካሁን በጉዳዩ ላይ በአዲስ አበባ እና በካርቱም መካከል ስላለው ምልልስ በይፋ የተባለ ነገር የለም።