በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን እስር እና እንግልት በረታብን አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በኤርትራውያን ላይ የጅምላ እስራት እየተካሄደ እንደሆነ ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው በርካታ በከተማዋ የሚኖሩ ኤርትራውያን ገለጹ።
ምንም እንኳን መሰል ክስተቶች አዲስ ባይሆኑም በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ የጅምላ እስራት ግን ከፍተኛ ስጋት እና ተስፋ መቁረጥ እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ።
በተለያዩ ምክንያቶች ከኤርትራ እንደተፈናቀሉ የሚገልጹት ስደተኞቹ ሕይወታቸውን የሚፈታተን ስጋት እያጋጠማቸው በመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ለጉዳያቸው ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኤርትራውያን ስደተኞች እስርን በተመለከተ መረጃ እንዳለውና የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ በኩል እንዲፈቱ መጠየቁን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግሯል።
የተገለጸው እስራት በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች ያጋጠመ ሲሆን፣ ከእነዚህ ጥቂቶቹ ሲፈቱ ሌሎች ግን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።
በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ለ20 ዓመታት የቆየው “የጦርነት ሁኔታ” ከስድስት ዓመት በፊት በሰላም የተፈታ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየተቀዛቀዘ መሆኑ ይነገራል።
በአዲስ አበባ ለስድስት ዓመታት ያህል በመሥራት እና በትምህርት ላይ የሚገኘው ኤርትራዊው ሃኒባል ሚካኤል ሁኔታው ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋ መሆኑን ገልጿል።
“በርካቶች እየታሰሩ ሲሆን፣ የባሰው ደግሞ ለመጠየቅ የሄዱ ቤተሰቦች እና ጓደኞችም እዚያው እየታሰሩ ነው። እስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ከተለያዩ ቦታዎች ታስረዋል” በማለት ወጣቱ ስጋት ላይ እንደሚገኝ ይገልጻል።
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በኤርትራውያን ላይ እስር እና እንግልት በመድረሱ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እስር እንዲቆም መጠየቁ ይታወሳል።
ሃኒባል እንደሚለው የታሰረች እህቱን ለመጠየቅ የሄደ ሕጋዊ ሰነድ ያለው ጓደኛው ያለምንም ጥፋት መገናኛ አካባቢ ባለ ማቆያ መታሰሩን ገልጿል።
በተጨማሪም “ይህ ሆን ተብሎ የሚደረግ እስር ኤርትራዊያን በሚኖሩባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ያነጣጠረ ነው” ይላል።
ጨምሮም እስሩ በጥናት ወይም በሕገወጥ ተግባር በተጠረጠሩ ላይ የሚደረግ ባለመሆኑ ሁሉንም እያስጨነቀ መሆኑን ጠቅሶ፤ ስለዚህም ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ኤርትራውያን ስደተኞች እንቅስቃሴያቸውን መገደቡን አመልክቷል።
ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደው የእስራት ሰለባ ሆኖ የቆየ ኤርትራዊ ላፍቶ አካባቢ እንደተያዘና ገንዘብ ከፍሎ እንደወጣ ለቢቢሲ ገልጿል።
“ካፌ ውስጥ እያለን አንድ ሲቪል ሰው ደውሎ ፖሊሶችን ጠርቶ ሁላችንንም ወሰዱን። ሕጋዊ የመንቀሳቀሻ ሰነድ ብናሳይም ያለምንም ምክንያት እና ምረመራ ሁለት ቀን በእስር አቆዩን” ይላል።
ከዚያም ጉዳያቸውን የሚከታተል ኢነስፔክተር በተናጠል እንዳናገራቸው እና ሕጋዊ ሰነድ ስላላቸው በአጠቃላይ 13 ሺ ብር እና 50 ዩሮ ከፍለው መውጣታቸውን ገልጿል። በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች ለመለቀቅ ከ5 እስከ 15 ሺ እንደሚጠየቁም አመልከቷል።
ጨምሮም ከእስር ለመውጣት የሚለፈለው ገንዘብ ማስረጃ እንዳይገኝ ለማድረግ በውጭ የሚቀበልላቸው ሰው አዘጋጅተው በጥሬ ገንዘብ ብቻ መሆኑንም ተናግሯል።
በርካታ ኤርትራውያን በእስር ላይ እንዳሉ የሚናገራው ግለሰቡ ያለምንም ሕጋዊ ሂደት ከሁለት ወር በላይ በእስር ቤት የሚገኙ መኖራቸውን ገልጿል።
ቢቢሲ ትግርኛ ጉዳዩ አስመልክቶ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ኤርትራውያንን ባነጋገረበት ወቅት በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ቢሮ ጉዳያቸውን ለመከታተል ከሄዱ መካከል በቡድን ተይዘው ለአንድ ሳምንት ያህል ጠፍተው የቆዩ እንደነበረ ማወቅ ችሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ ምናልባት የተከሰተው እስር ምክንያት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም የተመዘገቡ እና ሰነድ ያላቸው እንዲሁም በሱዳን ባለው ቀውስ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው።
በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በኤርትራውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ሰፊ የዘፈቀደ እስራት እና የመብት ረገጣ በተመለከተ የመንግሥታቱን ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነርን (UNHCR) ስለሁኔታ መረጃ እንዳለው ለቢቢሲ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ለቢቢሲ ትግርኛ በኢሜል በሰጠው ምላሽ መንግሥት እና የሚመለከተው ተቋም ታልቃ እንዲገቡ ማሳሰቡን እና ከታሰሩት መካከል የተወሰኑት መፈታታቸውን፣ የተቀሩትም እንዲለቀቁ የስደተኞች መሥሪያ ቤት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጠቁሟል።
ቢቢሲ ትግርኛ ለአዲስ አበባ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።












