የሶማሊያዋ ጁባላንድ ክልል ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, Jubaland State House
ከምርጫ ጋር በተያያዘ በማካሄዷ ከሶማሊያ የፌደራል መንግሥት ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ከፊል ራስ ገዟ የጁባላንድ ክልል ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነትም ሆነ ትብብር ማቋረጧን አስታወቀች።
ጁባላንድን ከአውሮፓውያኑ 2013 ጀምሮ የመሩት የፕሬዚዳንት አህመድ መሐመድ ኢስላም ወይም ማዶቤ አስተዳደር የሶማሊያ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን እየጣሰ እንዲሁም የሕዝቡን አንድነት እያናጋ ነው ሲልም ወንጅሏል።
ኬንያ እና ኢትዮጵያን የምታዋስነው እና ከሶማሊያ አምስት ከፊል ራስ ገዝ ክልሎች አንዷ የሆነችው ጁባላንድ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባደረገችው ምርጫ የክልሉ ፕሬዚዳንት ማዶቤ ለሦስተኛ ጊዜ መመረጣቸውን አስታውቃለች።
መቀመጫውን በሞቃዲሾ ያደረገው የሶማሊያ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ያለ ፌደራሉ መንግሥት ተሳትፎ የተደረገ ነው በሚል ምርጫውን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የምርጫው ውዝግብ መጋጋልን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት በማዶቤ ላይ የእስር ትዕዛዝ ሲያወጣ ጁባላንድ በምላሹ በፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ ነው የጁባላንድ ፕሬዚዳንት ማዶቤ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ያላቸውን ማንኛውም ግንኙነት እንዳቋረጡ ያስታወቁት።
“የጁባላንድ መንግሥት ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር ያለውን ማንኛውንም ግንኙነት እና ትብብር በይፋ ሙሉ በሙሉ አቋርጧል” ሲል የጁባላንድ መንግሥት ሐሙስ፣ ኅዳር 19/2017 ዓ.ም. መግለጫ አውጥቷል።
በፕሬዚዳንት ማዶቤ የሚመራው የጁባላንድ መንግሥት የሶማሊያን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ፣ ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም እንዲሁም በሙስና ከሷቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ በተረጋጋችው የጁባላንድ ግዛት የፀጥታ ችግር እንዲፈጠር ማድረግን ጨምሮ “የእርስ በርስ ጦርነቶች እና የጎሳ ግጭቶችን” እያነሳሱ እንዲሁም አማጺያንን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ በመጣል ወንጅሏቸዋል።
የጁባላንድ ወታደሮች ከበርካታ አስርት ዓመታት ግጭት በኋላ ማምጣት የቻሉትን ሰላም በፌደራሉ መንግሥት እርምጃዎች እየተበጠበጠ እንደሆነም ነው የፕሬዚዳንት ማዶቤ አስተዳደር ያስታወቀው።
በፌደራሉ መንግሥት የተደረገው ሕገ መንግሥታዊ እና አስተዳደራዊ ማሻሻያ የጁባላንድን ራስን በራስ የማስተዳደር እንዲሁም የፌደራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ጁባላንድ ከሳለች።
ሶማሊያ ከጥቂት ወራት በፊት ያደረገችውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሌላኛዋ ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ዕውቅና እንደማትሰጥ እና ከፌደራሉ ሥርዓቱ መውጣቷን በወቅቱ አስታውቃ ነበር።
የሕገ መንግሥት ማሻሻያው በሶማሊያ ታሪክ ለረዥም ዓመታት ተግባራዊ የነበረው በጎሳ ላይ የተመሠረተ ቀጥተኛ ያልሆነ የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓት እንዲያከትም እና ለሁሉም ሰው የመምረጥ መብትን የሚያስተዋውቅ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ቀጥተኛ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ያለ ፓርላማው ይሁንታ ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሾሙበት እና የሚሽሩበትን አሠራር ያመጣ ነው።
ሕዝቡን እና ግዛቶችን ያላሳተፈ ያለችውን የፑንትላድ ግዛትን ጨምሮ የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ፣ ሸሪፍ ሼክ አህመድን እንዲሁም ፖለቲከኞች ማሻሻያውን በወቅቱ አጥብቀው ተቃውመዋል።
የጁባላንድ መንግሥት “በፌደራሉ መንግሥት ምክር ቤቶች የተደረጉ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች አና የወጡ የምርጫ ሕጎችን እንደማይቀበል” በትናንትናው መግለጫ አጽንኦት ሰጥቷል።
ሕገ መንግሥታዊ መርሆች “የማይነኩ እና የማንደራደርባቸው ናቸው” ያለው የጁባላንድ መንግሥት በወደፊቱ አስተዳደራዊ ጉዳይ ላይ፣ አገራዊ አንድነት እና የሶማሌ ሕዝብ አብሮነት ላይ የሚመክር ሁሉንም የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የምክክር መድረክ ለመመሥረት ማቀዱን አስታውቋል።
በሞቃዲሾ የሚገኘው ፍርድ ቤት በበኩሉ ማዶቤ በአገር ክህደት እና ምሥጢራዊ መረጃዎችን ለውጭ አካላት አሳልፈው በመስጠት የእስር ትዕዛዝ ረቡዕ፣ ኅዳር 18/2017 ዓ.ም. አውጥቷል።
የፌደራሉ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድም ሆነ ማዶቤ የየራሳቸውን ጦር ስለሚያዙ የፍርድ ቤቱ የእስር ትዕዛዝ ተፈጻሚነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ የእስር ትዕዛዙ የሕግ የማስከበር እና የመበየን ሥልጣን ያላቸው የፍትህ አካላት ኃላፊነት መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ሆኖም የጁባላንድ መንግሥት ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ በሚለው ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጡም።
ምርጫውን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ጁባላንድ አሰማርቷል።
ከሦስት ዓመታት በፊት የወቅቱ የፌደራሉ መንግሥት ፕሬዚዳንት የነበሩት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ሥልጣናቸውን የማራዘም ዕቅድ ማውጣታቸውን ተከትሎ ጁባላንድ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ለመግባት ተቃርበው ከነበሩ ክልሎች አንዷ ናት።
የሶማሊያ የዳቦ ቅርጫት ተደርጋ የምትታየው ጁባላንድ በመዲናዋ ኪስማዮ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው የሚባል ወደብ መገኛ ናት። በተጨማሪም ሶማሊያ እና ኬንያ የሚወዛገቡበት እና የነዳጅ እና የጋዝ ከፍተኛ ክምችት የሚገኝበት ስፍራን ይዛለች።















