በኒው ዮርክ በሚገኝ ህንጻ አንድ ግለሰብ ተኩስ ከፍቶ ፖሊስን ጨምሮ አራት ሰዎች ገደለ

የፎቶው ባለመብት, CBS
በአሜሪካ ኒው ዮርክ ማንሐተን አንድ ሕንፃ ውስጥ አንድ ግለሰብ በከፈተው የተኩስ እሩምታ አራት ሰዎች ሲገደሉ ፖሊስ የጥቃቱን ምክንያት እየመረመረ ነው።
ሰኞ፣ ሐምሌ 21/ 2017 ዓ.ም ስራ መውጫ አካባቢ መሀል ከተማ ማንሀተን በተፈፀመ ጥቃት ከሞቱት አራት ሰዎች መካከል የከተማው ፖሊስ መኮንን አንዱ ናቸው።
ፖሊስ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ባሉበት ሕንፃ ጥቃቱ መድረሱን እና ተጠርጣሪው ወዲያው ተኩስ መክፈቱን አስታውቋል።
ግለሰቡ መሳሪያ ታጥቆ አንድ ሕንፃ ውስጥ ከገባ በኋላ በሕንፃው እንግዳ መቀበያ ስፍራ እና በላይኛው ወለል ላይ ተኩስ መክፈቱን ፖሊስ አስታውቋል።
አጥቂው የሕንፃው ጥበቃ ላይ ከተኮሰ በኋላ በእንግዳ መቀበያው አካባቢው ሌላ አንድ ሰው ላይ ተኩሷል።
ከዚያም የሕንፃው አስተዳደር ወደ ሚገኝበት ወለል በአሳንሱር ከወጣ በኋላ ተኩስ ከፍቷል።
ተጠርጣሪው ው የህንፃው እንግዳ መቀበያ እንደገባ "ወዲያውኑ" በፖሊስ መኮንኑ ላይ ተኩስ መክፈቱ ተነግሯል።
ከዚያም በምሰሶዎች ለመደበቅ የሞከረች አንዲት ሴት ላይ ከተኮሰ በኋላ በእንግዳ ማረፊው ላይ ተኩስ ማርከፍከፉን የከተማው ፖሊስ ኮሚሽነር ጀሲካ ቲስቼ ተናግረዋል።
ፖሊስ ተጠርጣሪው የ27 ዓመት እድሜ ያለው ሼን ዲቮን ታሙራ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን፤ ግለሰቡ ከላስ ቬጋስ መጥቶ ጥቃቱን እንደፈፀመ ነገር ግን ጥቃቱን የፈፀመበት ዓላማ ግልፅ አይደለም ብሏል።
በላስ ቬጋስ ኔቫዳ ግዛ መሳሪያ የመታጠቅ ፈቃድ እንዳለው የተነገረ ሲሆን "የአዕምሮ ጤና ቀውስ ታሪክ እንዳለበት የተመዘገበ ነው" ተብሏል።
በዚህ ጥቃት በአጠቃላይ አምስት ሰዎች በጥይት ሲደበደቡ አራቱ ሕይወታቸው ማለፉን ፖሊስ ገልጿል።
በኋላ ላይ ተጠርጣሪው ራሱ ላይ ባደረሰው ጉዳት ሕይወቱ አልፎ ተገኝቷል።
ተጠርጣሪው ተሽከርካሪው ውስጥ በርካታ ጥይቶች ተገኝተዋል።
በአሜሪካ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ በሆነችው ኒው ዮርክ ጥቃቱ ሲፈፀም ፖሊስ ማስጠንቀቂያ ማሰማቱን ተክትሎ መንገደኞች ሽፋን ለማግኘት ሲሯሯጡ ታይተዋል።
የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ አሰቃቂ ሲሉ ጥቃቱን ገልፀው በአሜሪካ መሳሪያ ለመታጠቅ ምን ያህል ቀላል እንሆነ ለሁላችንም ያሳየ ነው ብለዋል።
በመሳሪያ የሚፈፀም ጥቃት በአሜሪካ የበርካቶችን ሕይወት እየነጠቀ መሆኑንም ከንቲባው አንስተዋል።















