ማንኪያ ተጠቅመው ከአስፈሪው የአልካታራዝ እስር ቤት ያመለጡት እስረኞች ያልተዘጋ ታሪክ

ከአልካታራዝ እስር ቤት ያመለጡት እስረኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥር ወር ለሁለተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ በኋላ አሜሪካንን ብሎም ዓለምን ያነቃነቁ ውሳኔዎችን አሳልፈው ተግባራዊ እያደረጉ ነው።

ትራምፕ በተለይ በአገራቸው አሉ ያሏቸውን "ሕገወጥ እና ወንጀለኛ" ስደተኞን በመያዝ ከአገራቸው ለማስወጣት የሚያስችለውን ትዕዛዝ የፈረሙት ሥልጣን እንደያዙ ሳይውሉ ሳያድሩ ነበር።

በዚህም የኢሚግሬሽን መኮንኖች እና የፀጥታ ኃይሎች በየቦታው አሰሳዎችን በማድረግ በርካታ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች በመያዝ ወደ እስር ቤት ወስደዋል። ይህም የተያዙትን ስደተኞች የማቆያ ቦታ ጥበት ተፈጥሯል።

ይህንንም ለመቅረፍ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዓመታት በፊት ተዘግቶ ሥራውን አቁሞ የነበረውን አስፈሪውን አልካትራዝት የተባለው እስር ቤት ዳግም ተከፍቶ አደገኛ ወንጀለኞች እንዲታሰሩበት ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ከ50 ዓመታት በፊት በአነጋጋሪ ሁኔታ እስረኞች ያመለጡበት አልካትራዝ ተዘግቶ ለዓመታት ከሳን ፍራንሲስኮ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ሆኖ አገለግሏል። አሁን ግን "የሕግ፣ የሥርዓት እና የፍትሕ ምልክት ይሆናል" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 12/1962 ማለዳ ላይ በአሜሪካው የአልካትራዝ እስር ቤት ውስጥ የነበሩት ፍራንክ ሞሪስ፣ ጆን አንግሊን፣ እና ወንድሙ ክላረንስ አንግሊን ከክፍላቸው ባለመውጣታቸው ተረኛው ፖሊስ ሊያረጋግጥ ወደ ክፍላቸው ገባ።

ክፍላቸውን ሲመለከት ሦስቱም መተኛታቸውን አስተዋለ።

ከዚያም ወደ ፍራንክ ሞሪስ ክፍል ጠጋ ብሎ በያዘው ዱላ ጭንቅላቱን ነካ አደረገው፤ ለመቀስቀስ በማሰብ።

የፍራንክ ጭንቅላት ከአልጋው ላይ ወደቀ።

ተረኛ የነበረው የጥበቃ ጓድ በድንጋጤ ልቡ በአፉ ልትወጣ ደረሰች።

ምናልባትም እስረኛውን እንደ ገደለው ሳይሰማው አልቀረም።

የሆነው ግን እርሱ አልነበረም። ሦስቱም እስረኞች ከእስር ቤቱ ወጥተው አምልጠዋል።

አልጋቸው ላይ እንደተኙ መስሎ የተቀመጠው ከወረቀት በሰው የራስ ቅል የተሠራ ቅርጽ ነው።

በእስር ቤቱ ቀውስ ሆነ፤ እንዴት ከዚህ ጥብቅ እስር ቤት ውስጥ ሊያመልጡ ቻሉ።

ታራሚዎቹ ተብጠርጥረው ሲፈተሹ አለን ዌስት የተባለ ታራሚ በተመሳሳይ ከወረቀት የተሠራ የራስ ቅል በክፍሉ ውስጥ ተገኘ።

ይህ ማስረጃ እርሱም ከሦስቱ እስረኞች ጋር ለማምለጥ አሲሮ እንደነበር አሳይቷል።

እነዚህ ደጋጋሚ ወንጀለኞች፣ ረዥም የሽቦ አጥር፣ ስድስት የመቆጣጠሪያ ማማ ያሉትን በባሕር የተከበበ ጥብቅ እስር ቤትን እንዴት ጥሰው ወጡ?

አልካታራዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አልካታራዝ

ከእስር ቤቱ ቢወጡም እንኳ የሳንፍራንሲስኮ ቤይን ውቅያኖስ እንዴት አቋረጡ? በሕይወት ተርፈዋል ወይስ ሞተዋል?

ፍራንክ ሞሪስም ከ13 ዓመቱ ጀምሮ እስር ቤት መግባት መውጣትን ልማዱ ያደረገ ወንጀለኛ ነው።

ወደ አልካትራዝ ከመላኩም በፊት በተደጋጋሚ ከእስር ቤት በማምለጥ ቅጽል ስም ማፍራቱን ዶሴው ያስረዳል።

ወንድማማቾቹም ቢሆኑ በአሻንጉሊት ሽጉጥ ባንክ ዘርፈው በቁጥጥር ስር ሲውሉ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሙከራ በማድረጋቸው ነበር በዚህ በውሃ በተከበበ በተገለለ እስር ቤት ፍርዳቸውን እንዲጨርሱ የተላኩት።

ሰኔ 12/1962 ከአልካታራዝ እስር ቤት ያመለጡት ሦስቱ እስረኞች አልተያዙም።

የፍራንክ ሞሪስ እና የአንግሊን ወንድማማቾች ዕጣ ፈንታ አሁንም እንቆቅልሽ ሆኖ ቀርቷል።

ድፍረት፣ ዘዴ እና ቁርጠኝነት የተሞላበት እና ከአሜሪካው ጥብቅ እስር ቤት የማምለጣቸው ታሪክ አስገራሚነቱ ቀጥሏል።

በወንጀል ዓለም ውስጥ በጣም የሚፈራው የአልካታራዝ እስር ቤት ደሴት ላይ ተገነባ ነው።

"ዘ ሮክ" የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት የነበረው የፌዴራል ማረሚያ ቤት በአሜሪካ በጣም አደገኛ ወንጀለኞችን የሚታሰሩበት ነበር።

በውሃ የተከበበው አልካትራዝ እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በውሃ የተከበበው አልካትራዝ እስር ቤት

የማይበገር ምሽግ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ሰኔ 12/1962 መጀመሪያ ላይ ሦስት ሰዎች የማይቻል ነው ተብሎ የታሰበውን አሳኩ። ከማይበገረው እስር ቤት አመለጡ።

አልካትራዝ የተገነባው የባሕር ወሽመጡን መግቢያን ለመጠበቅ የባሕር ኃይል መከላከያ ምሽግ እንዲሆን ተብሎ ነበር።

በዩናይትድ ስቴትስ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት፣ ገደላማ ቋጥኞች እና ፈጣን፣ ቀዝቃዛ ጅረቶች ያሉባት ደሴት በመሆኗ የተማረኩ የኮንፌዴሬሽን እስረኞች ታጉረውበት ነበር።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ደግሞ እንደ ወታደራዊ እስር ቤት እንደገና ተገንብቷል።

እአአ በ1930ዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ በግዛቷ ውስጥ የተስፋፉትን የተደራጁ ወንጀሎችን ለመቋቋም ስትሞክር የፍትሕ ቢሮው እስር ቤቱን ተቆጣጠረው።

ከፌዴራል እስር ቤቶች በጣም አስፈሪ የሚባሉ ወንጀለኞች ወደ አልካታራዝ መግባት ጀመሩ።

ከታዋቂዎቹ እስረኞች መካከል ታዋቂዎቹ ወንበዴዎች አል ካፖን፣ ሚኪ ኮኸን እና ጆርጅ "ማሽን ገን" ኬሊ እንዲሁም ነፍሰ ገዳዩ እና በኋላ ላይ "የአልካታራዝ በርድማን" በመባል የሚታወቀው ሮበርት ስትሮድ ይገኙባቸዋል።

ዓላማው በጣም ጨካኞች እና አስጨናቂ ወንጀለኞች ተራ እስር ቤት ውስጥ አይታሰሩ ለማደረግ ነው ነው።

ሰፊ ዕቅድ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፍራንክ ሊ ሞሪስ በ11 ዓመቱ ነበር ወላጆቹን ያጣው። በ13 ዓመቱ የመጀመሪያ ወንጀሉን የፈፀመው ሞሪስ አብዛኛውን ሕይወቱን በተለያዩ የማረሚያ ተቋማት ውስጥ አሳልፏል።

በጣም ብልህ ነው ተብሎ የሚታሰበው ሞሪስ ልምድ ያለው ወንጀለኛ ነበር።

ከአደንዛዥ ዕፅ፣ ከጦር መሳሪያ ዘረፋ እና እስከ እስር ቤት የማምለጥ የሚደርስ ክስ አለበት።

ጥር 1960 ከሉዊዚያና ግዛት ማረሚያ ቤት ካመለጠ በኋላ ወደ ዘ ሮክ ተላከ። አልካታራዝ እንደደረሰ ግን እንዴት ማምለጥ እንዳለበት ማሰብ ጀመረ።

ባንክ የዘረፉት ወንድማማቾቹ ጆን እና ክላረንስ አንግሊን እና ከ1957 ጀምሮ በአልካትራዝ እስረኛ የነበረው አለን ዌስት የሚገኙበት ሕንጻ ውስጥ ታሰረ።

ሁሉም ቀደም ሲል በነበራቸው የእስር ቤት ሕይወት ይተዋወቁ ነበር። የታሰሩበት ክፍል የተቀራረበ ስለነበር ምሽት ላይ እርስ በርስ መነጋገር ችለዋል።

ሞሪስ መሪያቸው ሆነ። አራቱም እስረኞች ለማምለጥ ድፍረት የተሞላበት ዕቅድ ማዘጋጀት ጀመሩ።

በጥቂት ወራት ውስጥ ከማጠቢያው በታች ባለው የአየር ማስተንፈሻ ዙሪያ ያለውን እና በጨው የተጎዳውን ኮንክሪት እየደረመሱ ወጡ።

ከመመገቢያ አዳራሻቸው የተሰረቁ የብረት ማንኪያዎችን፣ ከቫክዩም ክሊነር ሞተር የተሠራው መሰርሰሪያ እና የተጣሉ መጋዞችን በመጠቀም ጥበቃ ወደማይደረግለት ኮሪደር አመለጡ።

በሚሰረስሩበት ወቅት ድምጽ እንዳይሰማ ሙዚቃ ለእስረኞች በሚከፈትበት ወቅት ይሰረስራሉ።

በተመሳሳይ ሰዓት ሞሪስ አኮርዲዮኑን ይጫወትም ነበር። ወደ ኮሪደሩ ለመግባት የሚያስችል ትልቅ ቀዳዳ ከፈጠሩ በኋላ፣ ባዶ ወደ ሆነው የእስር ቤቱ ጣሪያ በመውጣት ምሥጢራዊ ክፍል አዘጋጁ።

ቀዳዳውን ለመሸፈን ከእስር ቤቱ ቤተ መጻሕፍት መጽሔቶችን ተጠቅመው ብረት የሚመስሉ መሸፈኛዎችን ሠሩ።

ጣሪያ ላይ ባዘጋጁት ክፍል ከገቡ በኋላ ከ50 በላይ በሚሆኑ በተሰረቁ የዝናብ ካፖርት በመጠቀም 182 በ426 ሴንቲ ሜትር የሆነ ጊዜያዊ የፕላስቲክ ጀልባ እና የአደጋ ጊዜ ጃኬት ሠሩ።

ላስቲኩን ለመስረቅ የእስር ቤቱን ትኩስ የእንፋሎት ቧንቧዎች በመጠቀም አቀለጡት። መቅዘፊያዎችን ደግሞ ከእንጨት አዘጋጁ።

ሲሠሩ ጠባቂዎች እንዳይደርሱባቸው በምሽት የፍተሻ ጊዜ እንዳይያዙ አንድ መላ ዘየዱ።

የጭንቅላታቸውን ቅርጽ ከሳሙና፣ ከጥርስ ሳሙና እና ከመጸዳጃ ወረቀት ቀርጸው አልጋ ውስጥ የተኙ አስመስለው ያስቀምጣሉ።

አልካትራዝ ሲጎበኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አልካትራዝ በተዘጋበት ጊዜ ይጎበኝ ነበር

እውነተኛ እንዲመስሉ ደግሞ ከእስር ቤቱ ፀጉር ቤት ውስጥ እውነተኛ ፀጉር ሰብስበው ተጠቀሙ። ከዚያም አልጋቸው ውስጥ ያስቀምጧቸዋል።

ልብሶችን እና ፎጣዎችን ከብርድ ልብሶቻቸው ስር በመክተት የተኙ ያስመስላሉ።

ጊዜያዊ የማምለጫ መሳሪያቸውን ሲያዘጋጁ መውጫውንም ይፈልጉ ነበር። የቧንቧ መስመሮችን እንደ መሰላል በመጠቀም 9.1 ሜትር ወደ ላይ በመውጣት ከአንድ ዘንግ ላይ ያለውን የአየር ማቀዝቀዣ ከፈቱት። ያልተከፈተ ለማስመሰል ከሳሙና የተሠራ ክዳን ተጠቀሙ።

በመጨረሻም ሰኔ 11/1962 ምሽት ላይ፣ የረቀቀ ዕቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጁ።

ሞሪስ እና ሁለቱ የአንግሊን ወንድማማቾች ዘበኞችን ለመሸወድ አልጋቸው ውስጥ የሚያስቀምጡትን ጭንቅላቶች ትተው ባዘጋጁት የግድግዳ ቀዳዳ ወጡ።

ዌስት በፍጥነት መውጣት ባለመቻሉ ሌሎቹ ጥለውት ሄዱ። ወደ እስር ቤቱ ጣሪያ ላይ ወጥተው ጊዜያዊ ጀልባቸውን ተሸክመው ሮጡ። በውሃ መውረጃ ቱቦ ወረዱ።

የእስር ቤቱን ጓሮ አቋርጠው ሁለት ተከታታይ 3.7 ሜትር የሚረዝሙ የሽቦ አጥሮችን ከፍተው ከደሴቱ ሰሜናዊ ምሥራቅ የባሕር ዳርቻ ቁልቁል ተወረወሩ። በውሃው ዳርቻ ላይ ጀልባቸውን ነፉ እና ወደ ውሃው ዘልቀው ጠፉ።

በሚቀጥለው ቀን ጠዋት በምትካቸው ያስቀመጡት ጭንቅላት እስኪገኝ ድረስ የማንቂያ ደውሉ አልተደወለም።

ደሴቲቱ በእስር ቤቱ ውስጥ የሚሠሩ የጥበቃ ሠራተኞች ቤተሰቦችም መኖሪያ ነበረች።

በጊዜው በአልካታራዝ ጠባቂ የነበረው የጆሊን ቤቢያክ አባት ማንቂያውን ደውሉን አሰማ። በ2013 ለቢቢሲ ዊትነስ ሂስትሪ ስትናገር "ስነቃ ደውሉ እየተደወለ ነበር። በጣም ጆሮ የሚወጋ፣ እጅግ በጣም የሚጮኽ፣ አሰቃቂ እና በጣም አስፈሪ ነበር" ስትል ተናግራለች።

የእስር ቤቱን የመኮንኖች ማረፊያን ጨምሮ በሁሉም ሕንፃዎች ላይ ከፍተኛ ፍተሻ ለማድረግ ማረሚያ ቤቱ ወዲያውኑ ተዘግቷል።

የጆሊን አባት በመቶዎች ከሚቆጠሩ የሕግ አስከባሪዎች ጋር በአካባቢው ለቀናት ከፍተኛ ፍተሻ ማድረግ ጀመሩ።

ሰኔ 14 ቀን የባሕር ጥበቃ አባላት ከእስረኞች መቅዘፊያዎች አንዱን አገኙ። በተመሳሳይ ቀን ላስቲክ ውስጥ የታሸጉ የአንግሊንስ የግል እቃዎችም ተገኙ።

ከሰባት ቀናት በኋላ የጀልባው ቁርጥራጮች በጎልደን ጌት ድልድይ አቅራቢያ ተገኙ። በቤት ውስጥ ከተሠራው የነፍስ አድን ጃኬቶችም መካከልም አንዱ ተገኘ። ሦስቱ እስረኞች ግን ዳግመኛ ላይገኙ ጠፉ።

ተዋናይ በርት ላንካስተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በእስር ቤቱ ዙሪያ ከተሠሩት ፊልሞች መካከል 'በርድማን ኦፍ አልካትራዝ' ላይ ተዋናይ በርት ላንካስተር ሲተውን

መቋጫ ያላገኘው ጉዳይ

እስረኞቹ ከእስር ቤት ቢያመልጡም ባለሥልጣናቱ ደሴቲቱን ለቅቀው ለመውጣት ሲሞክሩ ውሃው ውስጥ ሳይሞቱ አልቀሩም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

የእስር ቤቱ አዛዥ ሪቻርድ ዊላርድ በ1964 ቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግለት ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው።

"አዎ እኛ አልተሳካልንም፤ እነሱም ግን ደረታቸውን ነፍተው አልቀሩም። በጣም እርግጠኛ ነኝ እኛ ባይሳካልንም ከአልካታራዝ አመለጥኩ ብሎ ደረቱን የሚነፋ ሰው የሚኖር ይመስልሃል?" ብለዋል።

እስረኞቹ ካመለጡ ከአንድ ዓመት በኋላ የአልካትራዝ እስር ቤት በ1963 ተዘጋ።

ይህ የሆነው የማረሚያ ቤቱ ግንባታ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ እና ለማስተዳደር የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ መሆን እንደ ምክንያት ቢቀርብም የእስር ቤቱ አስከፊ አገዛዝም ለረዥም ጊዜ አከራካሪ ሆኖ ቆይቶ ነበር።

እአአ በ1939 የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍራንክ መርፊ "ተቋሙ በእስረኞች መካከል መጥፎ አመለካከትን የሚገነባ ለሥነ-ልቦና ምቹ ያልሆነ" በማለት ሊዘጉት ሞክረው ነበር።

የማያባራውን ሁኔታ መቋቋም ባለመቻል ለዓመታት እስረኞች እራሳቸውን አጥፍተዋል ወይም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

እናም 1960ዎቹ አሜሪካ ከቅጣት ይልቅ እስረኞችን ወደ ማነጽ ፊቷን አዞረች።

ሦስቱን ያመለጡ እስረኞች በባሕር ወሽመጡ ውስጥ አስከሬናቸው ባይገኝም በ1979 በሕጋዊ መንገድ ሞተዋል ተብሎ የተደመደመ ሲሆን፣ ኤፍቢአይም ጉዳዩን ዘግቶታል።

ነገር ግን ያመለጡት እስረኞች የዕጣ ፈንታ ከመላምት ባሻገር አስካሁን እርግጠኛው አይታወቅም።

በሕግ ሞተዋል በተባሉበት ዓመት 'ኢስኬፕ ፍሮም አልካታራዝ' የተሰኘው ፊልም ለዕይታ በቃ።

ከክሊንት ኢስትዉድ ደግሞ ፍራንክ ሞሪስን ወክሎ ተጫወተ። በ1962 ካመለጡበት ጊዜ አንስቶ ታይተዋል የሚል እንዲሁም ከእነሱ የተላከ መልዕክት የሚል ነገር ተደጋግሞ ቀርቧል።

እአአ በ2018 የሳን ፍራንሲስኮ ፖሊስ ከአምስት ዓመታት በፊት ከአንድ ሰው ምሥጢራዊ ደብዳቤ እንደተላከለተ ገለጸ።

ጆን አንግሊን ነኝ ይላል ግለሰቡ። ደብዳቤው "ሰኔ 1962 ከአልካታራዝ አምልጫለሁ። አዎ ሁላችንም በዚያ ምሽት አሳክተነዋል" ይላል። ደብዳቤው ሰዎቹ ራሳቸውን ደብቀው እንደኖሩ ገልጿል።

ፍራንክ ሞሪስ ጥቅምት 2005፤ ክላረንስ አንግሊን ደግሞ በ 2008 እንደሞቱ ተናግሯል።

ደብዳቤው የጻፈው ሰው የካንሰር ሕክምና ለማግኘት ሲል ራሱን አሳልፎ እንደሚሰጥ ያትታል። ኤፍቢአይ ደብዳቤውን ደጋግሞ አጥንቷል። ነገር ግን ትክክለኛ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ማረጋገጥ አልቻለም።

አሁንም ጉዳዩን የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ክፍት አድርጎ እየተከታተለው ነው።

በ2022 ሦስቱ የጠፉ የአልካታራዝ እስረኞች በሕይወት ካሉ በአሁኑ ወቅት ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምሥሎችንም አውጥቷል።

ስለእነሱ ማንኛውንም መረጃ ያለው ሰው እንዲያሳውቀው እና ጉዳዩን ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት እንደሚፈልግ አስታውቋል።