በደፈጣ ጥቃት ከፈረንሳይ ፖሊስ ያመለጠው እስረኛ ማን ነው?

ከፖሊስ መኪና ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ ሁለት የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ሲገደሉ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP / Getty

የምስሉ መግለጫ, ከፖሊስ መኪና ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ ሁለት የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ሲገደሉ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል።

በፈረንሳይ በደፈጣ ጥቃት ከፖሊስ ያመለጠው መሐመድ አምራ እየተፈለገ ይገኛል።

ከፖሊስ መኪና ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ ሁለት የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ሲገደሉ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል።

መሐመድ አምራ በፈረንሳይ ማርሴ ከወንጀለኛ ቡድኖች ጋር ቁርኝት እንዳለው ተገልጿል። ከአደገኛ ዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ ነውጥ በማስነሳት የተጠረጠሩ ቡድኖች ናቸው።

‘በራሪው’ የሚል ቅጽል ስም አለው። ፓሪስ አቅራቢያ ከፍርድ ቤት ወደ ማረሚያ ቤት እየተወሰደ ሳለ ነው ያመለጠው።

እስረኛው የነበረበትን መኪና አንድ ሌላ ተሽከርካሪ ከገጨ በኋላ ተኩስ ተከፍቷል።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለው የ30 ዓመቱ መሐመድ በዝርፊያ ክስ ተፈርዶበታል። ለሞት በዳረገ እገታም ክስ ተመሥርቶበታል።

ሮውን ውስጥ ቫል ደ ሬዩል በተባለ እስር ቤት ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ አዲስ ክስ ተመሥርቶበት ፍርድ ቤት ደርሶ ሲመለስ ነው መኪናው ላይ በተከፈተ ተኩስ እንዲያመልጥ የተደረገው።

ዐቃቤ ሕግ ላውራ ቤሲው እንዳሉት መሐመድ እንደ ሌሎች አደገኛ የሚባሉ ታራሚዎች “ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግበት እስረኛ” አልነበረም።

ሆኖም ግን ከፍርድ ቤት ሲመለስ ይጓዝበት የነበረው መኪና ጥበቃ እየተደረገበት ነበር።

አምስት ፖሊሶች አጅበውት እየሄዱ ነበር።

በፈረንሳይ በደፈጣ ጥቃት ከፖሊስ ያመለጠው መሐመድ አምራ እየተፈለገ ይገኛል።
የምስሉ መግለጫ, በፈረንሳይ በደፈጣ ጥቃት ከፖሊስ ያመለጠው መሐመድ አምራ እየተፈለገ ይገኛል።

‘የመሐመድ እናት በተፈጠረው ነገር ደንግጠዋል’

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠበቃው ሂውጅስ ቪጊር እንዳሉት፣ መሐመድ የእስር ቤቱን ግድግዳ በመቆፈር ከቀናት በፊት ለማምለጥ ሞክሮ ነበር።

ሆኖም ግን አሁን እንዲያመልጥ ባደረገው “ይቅር የማይባልና ያልተጠበቀ ነውጥ” መደንገጣቸውን ጠበቃው አክለዋል።

“ከማውቀው ማንነቱ ጋር አብሮ አይሄድም” ብለዋል ጠበቃው።

የጠበቃው ተባባሪ ከመሐድ ጋር ተገናኝተው እንደነበርና ለአንድ ሰዓት በቆየ ንግግራቸው “መሐመድ ደኅና እንደነበር” ገልጸዋል።

“ወደ ማረሚያ ቤት የሚመለስበትን ቀን ለሌሎች ተናግሮ ይሆናል” ብለዋል።

ከፖሊስ መኪና እንዲያመልጥ ያገዙት ሰዎች በመንገዱ መኪናው እስከሚያልፍ እየጠበቁ ነበር።

የመሐመድ እናት እንዳሉት፣ ልጃቸው ከፖሊስ ሊያመልጥ እንደሚችል ምንም ጥቆማ አልሰጠም።

“ልጄ ነው ግን ስለምንም ነገር አያዋራኝም” ብለዋል።

እስር ቤት ሳለ ሊጠይቁት ይመላለሱ ነበር። “ግን ያኔም ምንም አላለኝም” ብለዋል።

የደፈጣ ጥቃት እንደተፈፀመ የሰሙበትን ቅጽበት ሲገልጹ “ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። ጤናዬ ተቃወሰ። እንዴት በዚህ መንገድ ሕይወት ይጠፋል?” ብለዋል።

ልጃቸው በማረሚያ ቤት ቁርጥ ፍርድ ተሰጥቶት ከመታሰር ይልቅ “በጣም ይንገላታ እንደነበር” አክለዋል።

በማርሴ፣ ፓሪስ እና ሮውን በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ቆይቷል።

የታሰረበት የዝርፊያ ክስ 18 ወራት የሚያሳስር ነው። ከዚያ በፊት 13 በአነስተኛ ወንጀል የሚመደቡ ክሶች ቀርበውበታል።

ያለ መንጃ ፈቃድ መንዳት፣ ፖሊስ ቁም ሲለው አለመታዘዝና ዝርፊያ ይገኙበታል።

በማርሴ ታግቶ የሞተ ሰውን በተመለከተ የቀረበበት ክስ ከአደገኛ ዕፅ ዝውውር ጋር የተገናኘ ሲሆን በከፍተኛ ወንጀልም ይመደባል።

እስረኛው ያመለጠበት ቀን ላይ በፈረንሳይ “ከዕፅ ዝውውር ጋር የተያያዘ ወንጀል ጨምሯል” የሚል ሪፖርት የወጣበት ነው።

“የዕፅ ዝውውር ያልነካው የአገሪቱ ክፍልና የማኅበረሰብ አካል የለም” ይላል ሪፖርቱ።

“የውጭ አገር ወንጀል ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ የፈረንሳይ አደገኛ ቡድኖችም እጃቸው አለበት” በማለት ሪፖርቱ ጠቅሷል።

የማርሴ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ኒኮላስ ቤሶን እንደተናገሩት ዕፅ አዘዋዋሪዎች በጣም ሃብታምና ኃያል እየሆኑ መጥተዋል።

በማርሴ ብቻ አምና ከዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ 50 ሰዎች ተገድለዋል።