በፈረንሳይ በደፈጣ ጥቃት ከፖሊስ መኪና እንዲያመልጥ የተደረገው እስረኛ እየታደነ ነው

መሃመድ አምራ

በፈረንሳይ በደፈጣ ጥቃት ወደ ማረሚያ ቤት ሲያጓጉዘው ከነበረው የፖሊስ መኪና እንዲያመልጥ የተደረገው መሃመድ አምራ የተባለ እስረኛ እየታደነ ነው።

‘ዘ ፍላይ’ በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው መሃመድ አምራንን ለመፈለግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች በኖርማንዲ ተሰማርተዋል።

መሀመድ ትናንት ግንቦት 6/ 2016 ዓ.ም በሩዋን ግዛት ከሚገኘው ፍርድ ቤት የነበረውን ችሎት ጨርሶ ተመልሶ ወደ ማረሚያ ቤት እያቀና በነበረበት ወቅት ነው አንድ መኪና ሲጓጓዝበት የነበረውን የፖሊስ መኪና የገጨው።

ከዚያም ከተሽከርካሪው ታጣቂዎች ወጥተው ተኩስ በመክፈት ሁለት የማረሚያ ቤት ፖሊሶችን ገድለዋል።

መሀመድ ኢምራን በማርሴይ ግዛት ውስጥ ታጋችን ለሞት በዳረገ የዝርፊያ እና የእገታ ወንጀል ተከሶ በእስር ላይ እንደነበር ተገልጿል።

“እነዚህን ወንጀለኞች አድኖ ለመያዝ ሁሉንም ዓይነት መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላሉ” ሲሉ የፈረንሳይ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒ ተናግረዋል።

ማክሰኞ ወደ 200 የሚጠጉ ተሰማርተው ቁልፍ በሆኑ ስፍራዎች ላይ የተሽከርካሪዎች ፍተሻ እያካሄዱ ይገኛል።

“ወንጀለኞቹን ለመያዝ በሁሉም መንገድ እየተሞከረ ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገልጸዋል።

የፓሪስ ከተማ አቃቤ ህግ ሎሬ ቤኩው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ማክሰኞ ከረፋዱ 5 ሰዓት አካባቢ መሃመድን የጫነው የእስር ቤት መኪና በሰሜናዊ ፈረንሳይ ዩሬ ክልል ሲደርስ ፔጆ መኪና ከፊት እንደገጨው ነው።

“ትልልቅ ጠመንጃ የያዙ ታጣቂዎች ከመኪናው የወረዱ ሲሆን ሌሎች ታጣቂዎች ደግሞ ከኦዲ መኪና ወርደው ተቀላቅለዋቸዋል። ይህ መኪና የፖሊሱን መኪና ሲከታተላቸው የነበረ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል።

ታጣቂዎቹ የጥይት እሩምታ በመክፈት የፖሊስ መኮንኖችን ገድለዋል እንዲሁም አቁስለዋል። በመጨረሻም ታራሚውን መሃመድን ይዘው ሄደዋል ብለዋል።

አቃቤ ህጉ አክለው እንደገለጹት ታጣቂዎቹ ተጠቅመዋውባቸው ነበር የተባሉ ሁለት ተሽከርካሪዎች ተቃጥለው በተለያዩ ቦታዎች ማክሰኞ ዕለት በኋላ ላይ ተገኝተዋል።

የፈረንሳይ የፍትህ ሚኒስትር ኤሪክ ዱፖንድ ሞሬቲ ከተገደሉት ፖሊሶች መካከል አንደኛው የ21ኛ ዓመታቸውን ልደት ሊያከብሩ ቀናት የቀራቸው የሁለት ልጆች አባት መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ህይወቱን ያጣው ሌላኛው የ34 ዓመቱ ፖሊስ ባለቤቱ የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች ብለዋል።