የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ የማዋሃድ የቅድመ ማስጀመሪያ ምክክር በመቀለ ተጀመረ

የትግራይ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣መበተን እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ የማዋሃድ የቅድመ ማስጀመሪያ ምክክር በትግራይ መዲና መቀለ ተጀመረ።

ትናንት ግንቦት 5/ 2016 ዓ.ም በተጀመረው በዚህ ምክክር ላይ የፌደራል መንግሥት ተወካዮች፣ የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት አመራሮች እና የአፍሪካ ኅብረት የስምምነት ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴ አባላት መገኘታቸውን የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በኤክስ ገጻቸው አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንቶች ጄነራል ታደሰ ወረደ እና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዚህ ምክክር ላይ የትግራይ ኃይሎች ተዋጊዎችን በመበተን እና ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ወደ ህብረተሰቡ ለማዋሃድ ፕሮግራም፣ ፕሮጀክቶች መንደፍ እንዲሁም የመጀመሪያው የትግበራ እቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተጠቅሷል ።

ኮሚሽነሩ በተጨማሪም “ተዋጊዎች የሚበተኑበት የተመረጡ ስፍራዎች የመስክ ጉብኝት እንደሚካሄድም” በትናንትናው ዕለት ባሰፈሩት የኤክስ መልዕክታቸው ጠቁመዋል።

ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ የቋጨው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት እና የናይሮቢ የትግበራ ሰነድ የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ጠቅሷል።

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ ጋር

የፎቶው ባለመብት, National Rehabilitation Commission

ከዚህ ቀደም የከባድ መሳሪያዎች ርክክብ መደረጉ የተገለጸ ቢሆንም ከትጥቅ መፍታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም መዘግየት ጋር ተያይዞ በትግራይ አመራሮች እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል አለመግባባቶች መፈጠራቸው አልቀረም።

በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል አሁንም ድረስ አለመተማመን መኖሩን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርብ ጊዜ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት “ትጥቅ ለመፍታት ፍላጎት የላችሁም፣ ሰራዊታችሁን ማጠናከር እና ከሌሎች ኃይሎች ጋር እየሰራችሁ ነው” በሚል ወቀሳ መቅረቡን አቶ ጌታቸው ተናግረው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የትግራይ አመራሮች በበኩላቸው “የፌደራሉ መንግሥት ትግራይን ለማዳከም እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ እና ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኗል የሚሉ ክሶች ማቅረባቸውን አቶ ጌታቸው በወቅቱ ገልጸዋል።

ከ270 ሺህ በላይ የትግራይ ኃይሎች አባላት እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ጌታቸው ሰራዊቱን ለመበተን እና መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገው በጀት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የፌደራሉ መንግሥት ኃላፊነት ነው ማለታቸው ይታወሳል።

በሰባት ክልሎች የሚገኙ 371,971 የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ከ760 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከጥቂት ወራት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ዙር 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከትግራይ ክልል መልሶ እንደሚያቋቁምም ገልጾ ነበር።

የፕሪቶሪያን ስምምነት ተከትሎ ተግባራዊ ካልሆኑ ጉዳዮች ሌላኛው ጉዳይ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ ጉዳይ እንደሆነ በቅርቡ የተናገሩት ጄነራል ታደሰ ወረደ ይህም በቅርብ ወራት መፍትሄ እንደሚያገኝ መናገራቸው ይታወሳል።

የትግራይን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ስር ተጠቅለው የተቋቋሙ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እስከ ሰኔ 30/ 2016 ዓ.ም ለማፍረስ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ አመራሮች ጋር በተደረገው ውይይት ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ክልል ስር የተዋቀሩት የደቡብ ትግራይ እና ጸለምቲ ወረዳዎች አስተዳደሮች እስከ ግንቦት 30 እንዲሁም በምዕራብ ትግራይ እስከ ሰኔ 30 ባለው ጊዜ እንደሚፈርስ ገልጸዋል።

ሁለቱ አካላት ባደረጉት ውይይት ትጥቅ መፍታትን አስመልክቶ የትኞቹ አስተዳዳራዊ መዋቅሮች መፍረስ እንዳለባቸው እና የተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚመለሱ ዝርዝር እቅድ የወጣ ሲሆን ይህንንም የሚቆጣጠረው እና የሚያረጋግጠው የአፍሪካ ኅብረት የስምምነት ክትትል አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴ እንደሚሆን መገለጹ ይታወሳል።