አልካትራዝ፡ ትራምፕ በድጋሚ እንዲከፈት ስላዘዙት 'የአደገኛ ወንጀለኞች' እስር ቤት አምስት እውነታዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ምዕራባዊ ክፍል በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነው የተሠራው። በፓስፊክ ውቅያኖስ የሚጓዙ መርከቦችን አቅጣጫ ለማመላከል አናቱ ላይ መብራት ተሰቅሏል።
እንደ ባሕር መከላከያ ሰፈርም ሕንጻው ያገለግል ነበር። አልካትራዝ የበለጠ ዝነኛ የሆነው ግን በአሜሪካ አደገኛ የሚባሉ ወንጀለኞች መታሰሪያ ሲሆን ነው።
እአአ ከ1934 እስከ 1963 'ዘ ሮክ' በሚል ስያሜም የሚታወቀው አልካትራዝ በሌሎች ማረሚያ ቤቶች ቢታሰሩ አስቸጋሪ ይሆናሉ የተባሉ አደገኛ ወንጀለኞች ማቆያ ሆኗል።
በ1962 ሦስት ታራሚዎች አምልጠው የገቡበት አልታወቀም። በተጨማሪም የሆሊውድ ፊልሞች ማጠንጠኛ መሆኑ አልካትራዝ ዕውቅናው እንዲጨምር አስችሏል።
ዶናልድ ትራምፕ አልካትራዝ በድጋሚ ተከፍቶ በማስፋፋት "የአሜሪካ አደገኛና ጨካኝ ወንጀለኞች" መታሰሪያ እንዲሆን አዘዋል።
ስለ አልካትራዝ በስፋት የማይታወቁ አምስት እውነታዎች ቀጣዮቹ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
1. ለሌሎች ማረሚያ ቤቶች 'ምሳሌ' መሆኑ
እአአ በ1850 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገነባ ወታደራዊ እስር ቤት የነበረ ሲሆን፣ በትንሽዬ ደሴት ላይ ከፍ ብሎ ባለው አቀማመጡ ወንጀለኞች እንዳያመልጡ ያግዳል ተብሎ ነበር የታሰበው።
በ1912 በዓለም ረዥሙ የሲሚንቶ ግንብ በዙሪያው ታጠረ።
"የእስር ቤቶች ቁንጮ" በሚል ስያሜ ይታወቃል። በሌሎች የአሜሪካ ማረሚያ ቤቶች ለመቆየት አስቸጋሪ ወይም አመጸኛ የሆኑ ታራሚዎች ወደ አልካትራዝ ይወሰዳሉ።
ሦስት እስረኞች በአንድ ጥበቃ ቁጥጥር ሥር ይሆናሉ። ይሄንን የአልካትራዝ አሠራር ሌሎች ማረሚያ ቤቶችም ወርሰዋል።
የመጀመሪያው የእስር ቤቱ ኃላፊ ጄምስ ጆንሰን ነው። እስር ቤቱ ታራሚዎች ባህሪያቸውን አስተካክለው ከማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበት ሳይሆን በጥብቅ ድንጋጌዎች የተሞላ ነው ይላል።
እስረኞችን ለየብቻቸው በማሰር እንዳያሴሩ ማድረግ ከጥብቅ የቁጥጥር መንገዶቹ አንዱ ነበር።
እስረኞች ከሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ውጪ እረስ በርስ እንዲያወሩ አይፈቀድላቸውም ነበር። ይህንን ሕግ የሚጥሱ ታራሚዎች ከምድር በታች ወደተገነባ ለይቶ ማቆያ ይወሰዱና ለሳምንታት ይቆያሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
2. ጥቂት 'አደገኛ' ወንጀለኞች የሚታሰሩበት መሆኑ
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች መረጃ እንደሚጠቁመው በአልካትራዝ የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር ከማረሚያ ቤቱ አቅም በታች ነው።
በአማካይ ከ260 እስከ 275 ታራሚዎች ይታሰሩበታል። ይህም ከአጠቃላይ የፌደራል መንግሥት እስረኞች አንድ በመቶ ገደማ ነው።
በአሜሪካ ታላቁ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ወቅት የተደራጁ ወንጀለኞች በዚህ እስር ቤት ታስረዋል።
በጣም የሚታወቀው አልፎንስ ኤል ቻፖ ሲሆን፣ በቺካጎ የወንጀል ቡድን መሪ ነበር።
ኤል ቻፖ ወደ አልካትራዝ የተላከው አትላንታ ታስሮ ሳለ የወንጀል ድርጊቱን ከማረሚያ ቤት በመቀጠሉ ነው።
አልካትራዝ አራት ዓመት ከታሰረ በኋላ የቂጥኝ በሽታ ስለያዘው ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት ተዛውሯል።
ሌላው ታዋቂ እስረኛ በግድያ ወንጀል የተፈረደበት ሮበርት ስታውድ ነው።
ሮበርት አእዋፋት ይወድ ስለነበር 'የአልካትራዝ ወፍ ተመልካች' የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለታል።
በካንሳስ እስር ቤት ሳለ አእዋፋትን ያሳድግ ነበር። በአልካትራዝ ግን እንሰሳት ማስገባት ክልክል ነበር።
ሌላው ታዋቂ እስረኛ አልቪን ካርፖዊዝ ነው። በሕዝብ ዘንድ በጣም ይጠላ የነበረው አልቪን በ1930ዎቹ ኤፍቢአይ ክትትል ከሚያደርግባቸው ወንጀለኞች ግንባር ቀደም ነበር።
ለ25 ዓመታት በአልካትራዝ በመታሰር ለረዥም ጊዜ በማረሚያ ቤቱ የቆየ ወንጀለኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
በ1950ዎቹ በዋሽንግተን ካፒቶል ላይ ጥቃት በማድረስ የታሰሩት ጋንግስተር ጆርጅ (ማሽን ጋን ኬሊ ባርንስ) እና ራፋኤል ካንሴል ሚራንዳም ታዋቂ የአልካትራዝ እስረኞች ናቸው።
የፖርቶ ሪኮ ናሽናሊስት ፓርቲ አባላት ነበሩ።
3. ከአልካትራዝ ለማምለጥ 'ከባድ' መሆኑ
አልካትራዝን በኤሌክትሪክ ሽቦ በማጠር እና በታጠቁ ወታደሮች በማስጠበቅ ከማረሚያ ቤቱ ማምለጥ ከባድ እንዲሆን ታስቦ ነው የተገነባው።
ሆኖም ግን ታራሚዎች ማምለጣቸው አልቀረም። በሦስት አሥርታት 36 እስረኞች 14 ጊዜ የማምለጥ ሙከራ አድርገዋል።
23ቱ ተይዘው የታሰሩ ሲሆን፣ ስድስቱ ተገድለዋል። ሁለቱ ደግሞ ውቅያኖስ ውስጥ ሰጥመው ሞተዋል።
አምስት እስረኞች ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም። አምልጠው ሊሆን ይችላል ተብሎ ቢገመትም መንግሥት "ጠፍተዋል" ብሎ ነው የሚያምነው።
እስር ቤቱ በተከፈተ በሁለተኛው ዓመት በአውሮፓውያኑ 1936 ነበር የመጀመሪያው የማምለጥ ሙከራ የተፈጸመው።
ጆ ባወርስ የተባለ ታራሚ በአጥር ላይ ዘልሎ ሊያመልጥ ሲል በጠባቂዎች ተተኩሶበታል።
በ1945 ጆን ጊሊስ የተባለ ታራሚ የወታደር ልብስ ሰርቆ፣ ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ የወታደር መርከብ ተሳፈረ። ከደሴቱ ከወጣ በኋላ ልብሱ ከሌሎች ወታደሮች የተለየ መሆኑን ያስተዋሉ አዛዦች ደረሱበት።

'ባትል ኦፍ አልካትራዝ' በመባል የሚታወቀው እአአ በ1946 የተደረገው የማምለጥ ሙከራ በታሪክ ይጠቀሳል።
ስድስት እስረኞች መሣሪያ ሰርቀው ሁለት ጠባቂዎችን ሲገድሉ 18 አቁስለዋል። ማምለጥ ግን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በ1962 ፍራንክ ሞሪስ እንዲሁም ወንድማማቾቹ ክላራንስ አንግሊን እና ጆን አንግሊን የተባሉ ታራሚዎች አምልጠዋል።
ልብሳቸው በአቅራቢያው ባለ ኤንጅል ደሴት ላይ ስለተገኘ ምናልባት ሰጥመው ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
ጆን ስኮት እና ዳርል ፓርከር የተባሉ ታራሚዎች በጓዳ በኩል አሾልከው ቢያመልጡም ደሴቱ ላይ ተይዘዋል።
4. በሆሊውድ ፊልሞች ገናና መሆኑ
አልካትራዝ በሆሊውድ ፊልሞች ገናና ምሥል አግኝቷል። በፊልሞች ላይ የሚታዩ የአልካትራዝ ምሥሎች ሁሌም ልክ ናቸው ማለት አይደለም።
"አልካትራዝ በፊልም እና በመጻሕፍት እንደሚሳለው አስከፊ ቦታ አይደለም። ታራሚዎች ለብቻቸው መታሰራቸው ከሌሎች ማረሚያ ቤቶች በተሻለ አልካትራዝን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል" ሲሉ የማረሚያ ቤቶች ቃል አቀባይ ይናገራሉ።
በ1979 ክሊንት ኢስትውድ የተወነበት 'ኢስኬፕ ፍሮም አልካትራዝ' ፊልም በ1962 ፍራንክ ሞሪስ እንዲሁም ወንድማማቾቹ ክላራንስ አንግሊን እና ጆን አንግሊን የተባሉ ታራሚዎች እንዴት እንዳመለጡ ያሳያል።
ፊልሙ ታራሚዎቹ ሲያመልጡ ቢያሳይም በእርግጠኛነት አምልጠው ስለመሆኑ መረጃ የለም።
'መርደር ኢን ዘ ፈርስት' የተባለው ፊልም ታራሚው ሄንሪ ቶዶሬ ለአነስተኛ ወንጀል ታስሮ ሌላ ታራሚ ከሞተ በኋላ ክሶች ሲደራረቡበት ያሳያል።
በ1996 ኒኮላስ ኬጅ የተወነበት 'ዘ ሮክ' ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ እና ጌም ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
5. የተዘጋበት ምክንያት
ከአልካትራዝ ለማምለጥ ከሚደረጉ ሙከራዎች ባሻገር አልካትራዝን ለማስተዳደር የሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪ በ1963 እንዲዘጋ ምክንያት ሆነዋል።
የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስትር አልካትራዝን ለማደስ 5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።
ከሌሎች ማረሚያ ቤቶች በተለየ ሁኔታ ለአንድ ታራሚ በቀን 10 ዶላር በማውጣት ነበር አልካትራዝ የሚተዳደረው።
ማረሚያ ቤቱ ከተዘጋ በኋላ ኦል ትራይብስ የተባለው ቀደምት ማኅበረሰብ አካባቢውን ወስዶ ትምህርት ቤት እና የባህል ማዕከል ለመገንባት ሞክሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢው የማኅበረሰቡ እንደነበረ እና በአሜሪካ መንግሥት እንደተነጠቁ ይገልጻሉ።
ሆኖም አስፈላጊውን ቁሳቁስ ወደ ደሴቱ ለማጓጓዝ እንዲሁም ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ስኬታማ አልሆኑም።
አሁን በሳን ፍራንሲስኮ በቱሪስቶች በብዛት ከሚጎበኙ ቦታዎች አንዱ አልካትራዝ ነው።
በዓመት 1.3 ሚሊዮን ቱሪስቶች ይጎበኙታል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች የዋና፣ ሳይክል መንዳት እና ሩጫ ውድድር መነሻ ነጥብ አድርገውም ይጠቀሙበታል። በቂ ልምምድ ከተደረገ ከእስር ቤቱ ማምለጥ እንደሚቻል ማሳያ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል።












