"ሴቶቹን ሁሉ ወሰዷቸው" በዲሞክራቲክ ኮንጎ እስር ቤት የተደፈሩ ሴቶች ሰቆቃ

የ22 ዓመቷ ፓስካሊን

የፎቶው ባለመብት, Göktay Koraltan / BBC

*ማስጠንቀቂያ፡ በታሪኩ ውስጥ ያሉት አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች አንባቢዎችን ሊረብሹ ይችላሉ።

"ለማምለጥ ከሞከርኩ እንደሚገድለኝ ነገረኝ"

ከአንድ ወር በፊት በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትልቋ ከተማ ጎማ እስር ቤት ውስጥ የተደፈረችው የ22 ዓመቷ ፓስካሊን እነዚህን የደፋሪዋን ቃላት ታስታውሳቸዋለች።

ፓስካሊን "ሕይወቴን ከማጣት ይልቅ የፈለገውን እንዲያደርግ ተገድጃለሁ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ደፋሪው በሙንዘንዜ እስር ቤት ፓስካሊን ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ሁለተኛው ሰው ነው። የመጀመሪያው ጥቃት በጣም የከፋ ከመሆኑ የተነሳ ራሷን ስታለች።

አጥቂዎቿ በአቅራቢያ ካለው እና "ሳፊና" ከሚባለው የወንዶች እስር ቤት አጥር ጥሰው የመጡ ናቸው ትላለች።

"በውሃ ታንከሮቹ ላይ ሲዘሉ ድምጽ ሰማን። በጣም ብዙ ነበሩ፤ እኛም በእጅጉ ፈርተን ነበር። ያልታደሉት ተደፈሩ። ዕድለኛ የሆኑት ግን ሳይደፈሩ ወጡ።"

በእስር ቤቱ እና በአካባቢው ከተማ ትርምስ እየተስፋፋ ነበር። በሩዋንዳ የሚደገፉት የኤም 23 አማጽያን በአካባቢው ካደረጉት ፈጣን ግስጋሴ በኋላ ወደ ጎማ እየተጠጉ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አብዛኞቹ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች እና የከተማው ባለሥልጣናት ቀድመው ሸሽተዋል።

ከእስር ቤቱ ውጪ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።

ከሰዓታት በኋላ እስር ቤቱው ውስጥ ወንድ እስረኞች ለማምለጥ ሲሞክሩ ያቀጣጠሉት እሳት የእስር ቤቱን ግቢ አዳርሶታል።

ጠዋት ላይ ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ ወንድ እስረኞች ከእስር ቤት አምልጠው ነበር።

ነገር ግን ከሴት እስረኞች ማምለጥ የቻሉት ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ።

በአጠቃላይ 132 ሴት እስረኞች እና ቢያንስ 25 ሕጻናት በእሳት ተቃጥለው መሞታቸውን ሁለት ምንጮች ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን "በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ታማኝ ምንጮችን" ጠቅሰው "ቢያንስ 153 ሴቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በኋላ ፓስካሊን በእሳት ዶግ አመድ ወደ ሆነው እና ባዶ የሰዓት ማማ ብቻ ወደ ቆመበት የእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ተመልሳለች።

ታሪኳን ለማጋራት እና በቃጠሎ ሰለባ ለሆኑት ሟቾች ድምጽ ለመሆን ፈቃደኛ ናት።

ዓይኖቿ የተቃጠለው ግድግዳ፣ የተበተኑ ማብሰያ ድስት እና የልብስ ክምሮች ላይ እያማተሩ በሴቶች ክፍል ዋና ግቢ ውስጥ ትራመዳለች።

ጭንቅላቷን ግራ ቀኝ እየነቀነቀች ቃላት ሊገልጹት በማይችሉት ታላቅ ድንጋጤ እጆቿን ወደ አፏ ሰደደች።

"የሆነ ወቅት ላይ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አላውቅም ነበር" የምትለው ፓስካሊን።

"ሌሎች ሲሞቱ ካየሁ በኋላ ነው እንደምንም ብዬ ያለ የሌለ ጉልበቴን ሰብስቤ የተነሳሁት፣ እንድድን የፈለገው አምላክ ነው" ትላለች።

ሽንኩርት ሻጭ የሆነችው ፓስካሊ አሠሪዋ በስርቆት ከከሰሰቻት በኋላ ለእስር ተዳርጋለች።

የ22 ዓመቷ ናዲንም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እስር ቤት ተመልሳለች። በእስር ቤቱ ያጋጠማትን ስቃይ ከአእምሮዋ መፋቅ አልቻለችም።

"ሌሊት ስተኛ እዚህ ያየሁት ነገር ሁሉ ያቃዠኛል። ሙታንን እንደገና አያለሁ - እስክወጣ ድረስ እዚህ እንዳየሁት በርካታ ሬሳ። በሩን ከመክፈት ይልቅ እዚህ እንደ እንስሳ እንድንሞት ይተዉ።"

ናዲንም በሁለት ሰዎች እንደተደፈረች ተናግራለች።

"አልኮል ይዘው ነው የመጡት" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። "ሰዎችን በአደንዛዥ እፅ ማናወዝ ፈልገው ነበር። አስገድደው ነው የወሰዱኝ፤ እዚህ የነበሩትን ሴቶች በሙሉ ወስደዋቸዋል።"

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ከ167ቱ ውስጥ ቢቢሲ በዚያን ዕለት ምሽት ምን ያህል ሴቶች እንደተደፈሩ ማረጋገጥ አልቻለም።

ናዲን በመጀመሪያ ደረጃ ባልተከፈለ ዕዳ ለእስር በዳረጓት ኋላ ላይም እንዳትወጣ ባደረጓት ባለሥልጣናት ላይ ተናዳባቸዋለች።

"በኮንጎ ፍትህ ሊኖር የሚችል አይመስለኝም" ትላለች፤ "መንግሥት ነገሮችን እያስተዳደረ ያለበትን መንገድ አወግዛለሁ።"

በእስር ቤቱ ላይ የእሳት ቃጠሎው በተከሰተበት ጊዜ
የምስሉ መግለጫ, በእስር ቤቱ ላይ የእሳት ቃጠሎው በተከሰተበት ጊዜ

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት ከዋና ከተማይቱ ኪንሻሳ ከ1,500 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ጎማ ላይ አሁን ምንም ሥልጣን የለውም። አማጺያኑ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ወደ ምሥራቅ መገስገሳቸውን ቀጥለዋል።

ከእሳቱ በኋላ በእስር ቤቱ ወለል ላይ ከሚታዩት የአመድ ክምሮች መካከል በአንድ በኩል የተቃጠለ ትንሽ ሮዝ ጫማ አለ። ምናልባትም የልጆች ልብስ ላይ የነበሩ አንዳንድ የሚያብረቀርቁ አዝራሮች ከጎኑ ባለው ቆሻሻ ውስጥ ያበራሉ።

ሴት እስረኞች ከልጆቻው አንዳቸውን በእስር ቤት አብረዋቸው እንዲያቆዩ ተፈቅዶላቸው ነበር።

በእስር ቤቱ ውስጥ ከቃጠሎው የተረፉት ከ28ቱ ሕጻናት ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን ምንጮች ተናግረዋል። በተለየ ክፍል ታስረው የነበሩ የሕጻናት እስረኞች በዕለቱ ቀደም ብለው ተለቅቀዋል።

ስሟ እንዲገለጽ የማትፈልገው እና ከሞት የተረፈችው ሌላ እስረኛ በሰጠችው ዝርዝር ምስክርነት መሠረት በጣም ተጋላጭ የሆኑትን እስረኞች ሕይወት የቀጠፈው በእስር ቤቱ የተከሰተው እሳት እና ጭሱ ብቻ አልነበረም።

ፍሎረንስ እያለን የምንጠራት ይቺ የ38 ዓመት ሴት አስለቃሽ ጭስ ወደ ሴቶቹ ክፍል ሲተኮስ "ልጆች መሞት ጀመሩ" ብላለች።

"የእስር ቤቱ ጠባቂዎች እሳቱን ለማጥፋት ከመምጣት ይልቅ ጥይቶችን ሲተኩሱ እና አስለቃሽ ጭስ ሲወረውሩ በነበሩ በወታደሮች እና በፖሊሶች ተከቦ ነበር" ትላለች ፍሎረንስ።

"አስለቃሽ ጭስ በላያችን ላይ በተጣለ ጊዜ እሳቱ በረታ። ዓይናችን በርበሬ የገባበት ይመስል በጣም ያቃጥል ነበር። የምንተነፍስበት መንገድ የለም ማለት ይቻላል" ስትል አክላለች።

እሳቱ እና መደፈሩ ግራ መጋባት ውስጥ ከተታቸው። ሁሉም ወገን ሌላውን ላይ ጣት ለመቀሰር ዓይናቸውን አያሹም።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተፋለሙ ያሉት የኤም 23 አማጺያን እና የመንግሥት ኃይሎች መድፈር በስፋት እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል።

ሆኖም ፍሎረንስ በባለፈው ወር ክስተት ላይ ደፋሪዎቹ እስር ቤት ውስጥ የነበሩ ወንድ እስረኞች ናቸው ትላለች።

"እስረኞች መሆናቸውን መለየት ይቻላል። አንዳንዶቹ ጫማ አልተጫሙም። የሴቶች እስር ቤት ጣሪያ ላይ ሲወጡ የሚያውቋቸውን ሰዎች ስም ይጠሩ ነበር፣ እናም አንድም ታጣቂ ወይም ዩኒፎርም የለበሰ አልነበረም።"

ፍሎረንስ ከምሽት አምስት ሰዓት ጀምሮ ከእስር ቤቱ ውጪ "ጥይቶች ሲያፏጩ" እንደሰማች እና የሚያመልጡ እስረኞች ውጪ በፖሊስ እንደተገደሉ ተናግራለች።

"እስረኛ ከወጣ ይተኩሱበታል፤ ጥይት በላያችን ላይ ሲንጣጡ እኔ ተንበርክኬ አምላክ ከዚህ መጥፎ ሁኔታ እንዲያድነን እየተማጸንኩ ነበር" ትላለች።

የሴቶቹን ክፍል ሰብረው ከገቡት እስረኞች መካከል አንዳንዶቹ ማምለጫ መንገድ እየፈለጉ ነበር ስትልም ተናግራለች።

ፖሊሶች በመደበኛነት ያልቆሙበትን እና ከእስር ቤቱ ውጪ ያለውን አካባቢ ከሚጎራበቱ ግድግዳዎች አንዱን ጥሰውታል። ግን ብዙም ሳይቆይ ያ ክፍተቱ በእሳቱ ተከለለ።

ፍሎረንስ እሳቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችው ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ነው። ከዚያም ከሰዓታት በኋላ በወደቁ ሰዎች መካከል ስትራመድ ራሷን አገኘችው።

"ሰዎች ፊት ለፊታችን እየሞቱ ነበር፤ እኔ ልቆጥራቸው አልቻልኩም። ውሃ በመስጠት እነሱን እንዲነቁ ለማድረግ ሞከረን ነበር። አንዳንድ ሴቶች በእሳት እና በጋዝ ታፍነው ነበር፤ አንዳንዶቹ በልብ ድካም ሞተዋል" ስትል ፍሎረንስ ለቢቢሲ ተናግራለች።

"መንግሥት እሳቱን ሲያይ በሩን ከፍቶ ወይም መጥቶ ማጥፋት ነበረበት" ስትል እሷም ለብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋት የኮንጎን ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አድርጋለች።

ቢቢሲ በኪንሻሳ የሚገኘውን መንግሥት በሕይወት የተረፉ ሰዎች ላቀረቡት ክስ እና ወቀሳ ምላሽ እንዲሰጡ ያቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

ፍሎረንስ የሴቶች እስር ቤት በማን እንደሆነ ባይታውቅም በመጨረሻ በአምስት ሰዓት እንደተከፈተ እና ከ18 ሌሎች የተረፉ ሰዎች ጋር አብራ እንደወጣች ተናግራለች። ነገር ግን ምንም እርዳታ አልተሰጣቸውም።

"በመንገድ ላይ ያገኘናቸው ፖሊሶች እንኳን እስረኞቹን በተመለከተ ወይም የተጎዳ ስለመኖሩ አልጠየቁንም። እኛ እንዴት እንደሆንንም አልጠየቁም" ትላለች።

በዚያን ጊዜ አማጺ ተዋጊዎች ጠዋት 2 ሰዓት አካባቢ ገብተው በከተማው አንዳንድ ክፍሎች ነበሩ። ጎማ ወደ አማጽያኑ እጅ እየገባች ነበር።

ከእስር ቤት ውስጥም ሆነ ውጪ ሴቶቹን ከቁብ የሚቆጥራቸው አልነበረም።

በእሳት ቃጠሎው የሁለት ዓመት ልጇን ያጣችው ሲፋ

የፎቶው ባለመብት, Göktay Koraltan / BBC

የምስሉ መግለጫ, በእሳት ቃጠሎው የሁለት ዓመት ልጇን ያጣችው ሲፋ

በጎማ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኝ ድንኳን ውስጥ በጓደኛዋ ከእሳት ነበልባል የተረፈች ሌላ ሲፋ የተባለች የ25 ዓመቷ ሴት አለች።

በግራ ጎኗ ተኝታለች በሌላ የሰውነቷ ክፍል ለመተኛት ብትሞክርም ስቃዩን አልቻለችውም።

ቀኝ ክንዷ በፋሻ ተደራርቦ የታሰረ ሲሆን፣ በክንድዋ እና በፊቷ ላይ የቃጠሎ ምልክቶች አሉ። በጀርባዋ ላይም ተቃጥላለች። ልብሷ ሲቀየር ነርሶች የስቃይ ማስታገሻ መድሃኒት (ሞርፊን) መስጠት አለባቸው።

የሁለት ዓመት ሴት ልጇ ኢስተር በእስር ቤት መሞቷ ስቃይዋን ከአካላዊ በላይ አድርጎባታል።

"ኢስተርን በጀርባዬ አዝያት ነበር። ለማምለጥ ስንፈልግ አንድ ነገር ወደቀባት። ቦምብ? ምን እንደሆነ አላውቅም። እሷም እዚያው ሞተች" ስትል ሲፋ ለቢቢሲ ተናግራለች።

አክላም ኢስተር ገና መራመድ የጀመረች ሕጻን ስትሆን "ከኃጢአት የጸዳች ነበረች" ትላለች።

አንዳንድ ጊዜ በእስር ቤት ውስጥ ካሉት ልጆች ጋር ትጫወት የነበረ ቢሆንም፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን ከእናቷ ስር አትጠፋም ነበር።

ለውዝ ሻጭ የሆነችው ሲፋ ከልጇ ጋር ወደ ተጨናነቀው እስር ቤት ውስጥ እንዴት ገባች?

በስርቆት ውስጥ ተሳትፋለች ተብላ ተከሰሰች፣ እሷ ግን ይህን አልተቀበለችውም። ሳይፈረድባት መታሰሯን ትናገራለች። ይህ የተለመደ ክስተት መሆኑን የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ።

በሙንዜንዜ ማረሚያ ቤት የተከሰተው ነገር ሙሉ ታሪክ በፍፁም ላይታወቅ ይችላል። ባለሥልጣናቱም ይህንን ለማወቅ ዳተኛ ይመስላሉ።

ሲፋ እና ሌሎች ቢቢሲ ያነጋገራቸው ከሞት የተረፉ ሰዎች በጥር 19/ 2017 ዓ.ም ስለተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ምስክርነታቸውን ለመስጠት አሁን ጎማን የሚቆጣጠሩት አማጺያንም ሆኑ እስር ቤቱን ይመራ የነበረው የኪንሻሳ መንግሥት፤ ለማነጋገር የቀረባቸው ማንም እንደሌለ ተናግረዋል።

ሲፋ "ማንም [ይህን ጉዳይ] አይከታተልም፤ ጉዳዬ የሚለው ማንም ሰው የለም። አብቅቶለታል" ትላለች።

"ማንም አይጠየቅም፤ ቀድሞውኑ አልቋል" ስትል ትናገራለች።