በኢራን አስከፊ እስር ቤቶች ውስጥ የሚማቅቁት ሴቶች ሕይወት ምን ይመስላል?

ናሲም

ናሲም በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ቀዝቃዛው ወለል ላይ ኩርምት ብላ ሌሎች እስረኞች ስቃይ ሲደርስባቸው ትሰማለች።

የእስር ቤቱ ዘብ ይመጣና በሩን እየደበደበ "ሰማሽው? ተዘጋጂ፤ ቀጣይ አንቺ ነሽ" ይላታል።

በቀን ቢያንስ ከ10 እስከ 12 ሰዓታት ስቃይ ይደርስባታል። ብዙ ጊዜ ትገደያለሽ የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣታል።

ሁለት ሜትር እንኳ በቅጡ የማይሰፋው ክፍል አልጋም ሆነ መፀዳጃ የለውም። የ36 ዓመቷ የፀጉር ሥራ ባለሙያ ለአራት ወራት ብቻዋን እዚህ ክፍል ውስጥ ታስራለች።

ስቃይ ከሚያደርሱባት ሰዎች ውጭ ሌላ ሰው አይታ አታውቅም። ብዙ ጊዜ "በቃ እዚህ ሞቼ ማንም ሳያውቀው ተረስቼ ልቀር ነው?" ብላ አስባለች።

በአስከፊው ኢቪን እስር ቤት ሕይወት ለናሲም እና ለሌሎች ሴቶች ምን ይመስላል? ቢቢሲ ከተለያዩ ምንጮቹ ባገኘው መረጃ መሠረት ይህን ዘገባ አሰናድቷል።

የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ በአውሮፓውያኑ መስከረም 2022 በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች ሞተች። ይህን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናዊያን "ሴቶች፣ ሕይወት፣ ነፃነት" የሚል መፈክር አንግበው ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ።

ፖሊስ ማህሳ በቁጥጥር ሥር የዋለችው ሒጃብ ማውለቅ የሚከለክለውን ሕግ በመጣሷ ነው ይላል። ይህንን ተከትሎ ተቃውሞ የወጡ በርካታ ሴቶች እዚህ እስር ቤት ይገኛሉ።

ምንም እንኳ ከኢቪን እስር ቤት ወጥተው ሁኔታው ምን እንደሚመስል የተናገሩ ቢኖሩም እዚያው እያሉ ዝርዝር መረጃ የሰጡ እጅግ ጥቂት ናቸው።

ናሲም

የፎቶው ባለመብት, UGC

የምስሉ መግለጫ, ናሲም ከመታሰሯ በፊት ፀጉር በማስዋብ ሥራ ትደዳር ነበር

ከእስር ቤቱ የሚሰማው ሰቆቃ ብቻ አይደለም። በጠባብ ክፍል ውስጥ ታስረው እንኳ ለሴቶች መብት ከመሟገት ወደኋላ ስለማይሉ፤ የተጣለባቸው ገደብ ስለማያግዳቸው ሴቶች ጭምር ነው።

አንዲት ሴት ከባሏ ጋር ጊዜ እንዳታሳልፍ ጊዜ ተሰጥቷት አርግዛለች።

ናሲም ራፕ ሙዚቃ እና ሜክአፕ ትወዳለች። በቁጥጥር ሥር የዋለችው ሚያዚያ 2023 ነው። ከጓደኞቿ ጋር የተቃውሞ ሰልፍ ለመሳተፍ ወጥታ እሷ ስትታሰር እንድ ጓደኛ ተገደለች።

ስቃይ ሲደርስባት የምትቋቋመው "መንገድ ላይ ስለተገደሉ ሰዎች በማሰብ" ነው። ብቻዋን ከታሰረችበት ክፍል ስትወጣ ሰውነቷ ተጎሳቁሏል፤ ተጫጭሯል። ስቃይ የሚደርስባት ሐሰተኛ ምስክርነት እንድትሰጥ ነው።

ሬዝቫኔህ በ2023 ነው ከባሏ ጋር በተቃውሞ ወቅት የታሰረችው። ባልና ሚስት መጨረሻው ኢቪን እስር ቤት ሆነ። የሴቶች እና የወንዶች እስር ቤት የተለያየ ነው።

መርማሪዎቹ ባሏን እንደሚገሉት እና እንዲሁም "ብዙ ደብድነው ልክ እንደ ከሰል ይጠቁራል" እያሉ ያስፈሯራታል።

ናሲም ብቻዋን የታሰረችበት ክፍል ብዙ ስቃይ መከራ ከደረሰባት በኋላ ሴቶች በጋራ ወደሚታሰሩበት ክፍል ተመለሰች። በጠቅላላው 70 ይሆናሉ። ሬዝቫኔህም እዚህ ነው ያለችው። አብዛኛዎቹ ፖለቲካዊ ክስ ነው የቀረበባቸው።

የኢቪን እስር ቤት ውስጡ በሲሲቲቪ ካሜራ

የፎቶው ባለመብት, Evin prison CCTV

የምስሉ መግለጫ, በ2020 ሾልኮ የወጣ የሲሲቲቪ ምስል የእስር ቤቱን ውስጠኛ ክፍል ያሳያል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ብሪታኒያዊት ኢራናዊቷ ናዛኒን ዛጋሪ-ራትክሊፍ አራት ዓመት ገደማ የታሰረችው ኢቪን ነው። በአውሮፓውያኑ 2022 ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተመልሳለች።

አብዛኛዎቹ ሴቶች ለእስር የተዳረጉት ማኅበረሰብ ለማንቃት በሚሠሩት [አክቲቪስት] ሥራ ነው። ፕሮፖጋንዳ በማስፋፋት፣ አገዛዙ ላይ ትጥቅ በማንገብ እንዲሁም ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ በመጣል ተከሰዋል።

አራት ክፍሎች አሉ። እያንዳንዳቸው 20 የሚሆኑ ታሳሪዎች ይይዛሉ። አልጋዎቹ ተደራራቢ ናቸው። ሶስት እስረኞች ያስተኛሉ።

እንዲህ ታጭቆ መኖር ውጥረት ይፈጥራል። ጥል ይኖራል። አካላዊ እና ቃላት መሰነዛዘር አይጠፋም። ነገር ግን አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ደግሞ አለ።

ክረምት ሲመጣ ብርዱ ከባድ ነው። በዚህ ወቅት "ሙቅ ውሀ ያለባቸው ኮዳዎች" ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት። ሞቃታማው ጊዜ ሲመጣ ደግሞ በላብ ይጠመቃሉ።

በክፍሉ አንደኛው ጥግ አነስተኛ ኩችና አለ። በቂ ገንዘብ ካገኙ ከእስር ቤቱ ሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ የሚበስል ገዝተው ያበስላሉ። እስር ቤቱ ከሚያቀርብላቸው ምግብ ይህ በስንት ጣዕሙ።

በአንዱ ጥግ ያለው ጨለም ያለ ሥፍራ ማጨሻ ነው። በሲሚንቶ ልሾ የተሠራው ጥግ አትክልት እና የቅርጫት ኳስ መረብ አለው። ውጭ የወጡ ዓይነት ስሜት ይሰጣል።

የራሳቸውን ልብስ መልበስ ይችላሉ። በክፍሎቹ ውስጥ እንደፈለጉት ይንቀሳቀሳሉ። እስር ቤቱ ሁለት መታጠቢያ ክፍሎች አሉት። አመሻሹን ተሰልፈው መፀዳጃ ክፍል ይጠቀማሉ፤ ጥርሳቸውን ይፍቃሉ።

ሬዝቫኔህ ለአራት ወራት ያክል እዚህ ከታሰረች በኋላ ነፍሰ-ጡር መሆኗን አወቀች።

ለዓመታት ልጅ ለመውለድ ብትሞክርም አልተሳካላትም ነበር። እንደውም ተስፋ ቆርጣ ቆይታለች። ነገር ግን በኢቪን ሕግ መሠረት በሌላኛው ክንፍ ከታሰረው ባሏ ጋር አልፎ አልፎ በግል መገናኘት ትችላለች።

እርጉዝ መሆኗን ባወቀች ጊዜ "ለበርካታ ቀናት አለቀሰች።"

እስር ቤቱ ሲበዛ የተጨናነቀ ነው። አብዛኛዎቹ እስረኞች አልጋቸው ላይ ቁጭ ብለው ነው የሚውሉት። እንዴት ነው እርጉዝ ሆና እዚህ የምትቆየው።

የአፕል ጁስ፣ ዳቦ እና ስጋ ያምራታል። እኒህን ማግኘት የማይታሰብ ነው። ከሱቅ ስጋ መግዛት ብትችልም ዋጋው ከውጪው ዓለም ሁለት እጥፍ ነው።

በአራተኛው ወር እስር ቤቱ 'አልትራሳውንድ ስካን' እንድታደርግ ፈቀደላት። ዶክተሮች ሴት ልጅ እንደምትገላገል ነገሯት።

"እያንዷንዷን የልብ ምት" ስትሰማ "ተስፋዋ እየጨመረ መጣ።" ነገር ግን የእስር ቤቱ ሁኔታ የልጇን ጤና እንዳይጎዳባት ትሰጋለች። ተመጣጣኝ ምግብ የማግኘት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሚጥል በሽታ ስላለባት ጭንቀት ማስወገድ ግድ ይላታል። የእስር ቤቱ ዶክተሮች ፅንሱ የመጨናገፍ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ነገሯት።

ሰዓሊዋ ቪዳ የሳለችው የፓክሻን አዚዚ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, UGC

የምስሉ መግለጫ, ሰዓሊዋ ቪዳ የሳለችው የፓክሻን አዚዚ ስዕል። ፓክሻን ሞት ተፈርዶባታል

ቪዳ ጋዜጠኛ ናት። ስዕል በጣም ትወዳለች። አንሶላ እንደ ሸራ ተጠቅማ የሌሎቹን ሴቶች ምስል ትስላለች።

ከእስር ቤቱ ሾልከው ከወጡ ስዕሎች መካከል አንዱ የከርዲሽ እስረኛዋ ፓኽሻን አዚዚን ስዕል ያሳያል። ፓኽሻን ከከርዲሽ አካባቢ ወደ ኢራቅ እና ሶሪያ ሄዳ የኢስላሚክ ስቴት ቡድን ሰለባዎችን ትረዳ ነበር።

ፓኽሻን የጦር መሣሪያ ተጠቅማ የኢራን አገዛዝን በመታገል ጥፋተኛ ተብላ የሞት ፍርድ ተፈርዶባታል። ፍርዱ ተፈፃሚ ይሆናል የሚል ስጋት አለ።

ቪዳ ውስጣዊ ሚስጥር ያለው ስዕል እንዳትስል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል። በግቢው ውስጥ ካሉ ግድግዳዎች በአንዱ ከተደረደሩ ጡቦች ጀርባ የሚታይ አረንጓዴ ጫካ ስላ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች አጥፍተውባታል።

የሕንፃው መተላለፊያ ላይ ደግሞ የኢራን አቦሸማኔ ሲሮጥ ስላለች። በአንዱ ምሽት የእስር ቤቱ ኃላፊዎች መጥተው ስዕሉን አጥፍተው የቪዳን ብሩሽና ቀለም ይዘው ሄዱ።

አንደኛው ስዕሏ ግን አሁንም አለ። ግዙፍ፣ ሰማያዊ ውቅያኖስ ከነማዕበሉ የተሳለበት ነው። ሴቶቹ እስረኞች የሚያጨሱበት ጥግ ላይ የተሳለ ነው።

ቪዳ

የፎቶው ባለመብት, UGC

የምስሉ መግለጫ, የ35 ዓመቷ ቪዳ ፀረ-መንግሕት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ተከሳለች

ሕክምና ማግኘት ለሴት እስረኞች እጅግ ፈታኝ ነው። ከእስረኞቹ መካከል አንዷ የሆነችው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ እና የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ናርጅስ ሞሐመዲ ለሕይወቷ አስጊ የሆነ የልብ ሕመም እና የሳንባ በሽታ አለባት።

ዶክተር ለማግኘት ብዙ መከራ ታያለች። ለሕክምና ስትሄድ በሻርፕ ባለመከናነቧ ዶክተሮችን ማየት እንዳትችል ኃላፊዎች እንደከለከሏት የናርጅስ ቤተሰቦች ይናገራሉ።

ሴት እስረኞች ይህንን ተቃውመው ለሁለት ሳምንታት ያክል የረሀብ አድማ መምታቸውን ተከትሎ ነው ናርጅስ ሕክምና ያገኘችው።

ናርጅስ በታኅሣሥ 2021 መጀመሪያ ለ21 ቀናት ሕክምና እንድትከታተል ከእስር ቤት ተለቃለች።

ናርጅስና ሌሎች ሴት እስረኞች ብዙውን ጊዜ መብታቸውን ለመጠየቅ ተቃውሞ ያነሳሉ። ምንም እንኳ ሕጉ ራሳቸውን በሻርፕ እንዲሸፍኑ ቢያስገድዳቸውም ብዙዎቹ እምቢኝ ይላሉ። ከብዙ ትግል በኋላ አልጋቸውን የሚሸፍኑበት መጋረጃ ተፈቅዶላቸዋል። ከዚያ ቀደም በሲሲቲቪ ካሜራ ዕይታ ውስጥ ነበሩ።

ለእስረኞቹ እጅግ አሰቃቂ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ፍርዳቸውን መጠባበቅ ነው። የናሲም መርማሪዎች ጥፋቷን ካላመነች በሞት እንደምትቀጣ ነግረዋት ነበር።

ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ግጥም በማንበብ፣ በመዝፈን፣ እዚያ በሠሯቸው ካርዶች በመጫወት እና ቴሌቪዥን በመመልከት ነው። ሁለት ቴሌቪዥኖች አሉ። ድራማ፣ ዘጋቢ ፊልም እና እግር ኳስ የሚያሳዩ የኢራን ጣቢያዎችን ያሰራጫሉ።

በስተመጨረሻም ናሲም ፍርዷ ተነገረ። ስድስት ዓመት፣ 74 ግርፊያ እና 20 ዓመታት ከቴህራን እጅግ ርቃ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ በስደት እንድትኖር ተፈረደባት።

ምንም እንኳ ፍርዱ ቢነገራትም ናሲም በአዲስ ተስፋ ተሞልታለች። አጣሁት ብላ ያሰበችው ነፍስ እንደተረፈላት ስታውቅ ትንፋሽ ዘርታለች።

ኢራን ውስጥ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ800 በላይ ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል። ይህ በስምንት ዓመታት ውስጥ ትልቁ ነው ይላል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ።

ሬዝቫኔህ ከጨቅላ ልጇ ጋር

የፎቶው ባለመብት, UGC

የምስሉ መግለጫ, ሬዝቫኔህ ባለፈው ጥቅምት ሴት ልጅ ተገላግላለች

ሬዝቫንህ የምትወልድበት ቀን ሲቃረብ ኃላፊዎች ለወሊድ ከእስር ቤት እንድትወጣ ፈቀዱላት። ባለፈው ጥቅምት ሴት ልጅ ተገላገለች።

ነገር ግን በልጇ መለወድ የሚሰማት ደስታ በፍርሀት፣ ሀዘን እና ንዴት የታጀበ ነው። ባሏ አልተፈታም። ነገር ግን ልጃቸውን ይዛ እየሄደች ትጎበኘዋለች።

በጭንቀት ምክንያት በቂ የጡት ወተት ለልጇ መስጠት አልቻለችም። በቅርቡ የቀራትን አምስት ዓመት ለመጨረስ ልጇን ይዛ ወደ እስር ቤት መመለስ አለባት። ምሕረት ካልተደረገላት በቀር ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት እስር ቤት ታሳልፋለች ማለት ነው።

ጨቅላ ሕፃናት እስከ ሁለት ዓመታቸው ከእናታቸው ጋር እስር ቤት መቆየት ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ግን ለቅርብ ዘመድ አሊያም ለሕፃናት ማሳደጊያ ይሰጣሉ።

ወጣም ወረደ ሴት እስረኞቹ "እንታገላለን" ይላሉ።

"እስር ቤትም ብንሆን እንታገላለን።"