በእንግሊዝ እስር ቤቶች በመጨናነቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ሊለቀቁ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስር ቤቶች በመጨናነቃቸው ምክንያት በእንግሊዝ እና በዌልስ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንደሚለቀቁ የአገሪቱ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን አስታወቁ።
ባለሥልጣኗ ሻባና ማህሙድ በእስረኞች የተጨናነቁ እስር ቤቶችን ጫና በአስቸኳይ ማቃለል ካልተቻለ የአገሪቱ “ሕግ እና ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ የመፍረስ አደጋ ሊገጥመው ይችላል” በማለት የእርምጃውን አስፈላጊነት አሳስበዋል።
በእንግሊዝ እና በዌልስ ውስጥ በሚገኙ እስር ቤቶች ያለውን የታሳሪዎች ብዛት ለማቅለል የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ባቀረበው ዕቅድ መሠረት ከተፈረደባቸው የእስር ጊዜ 40 በመቶውን ያጠናቀቁ የተወሰኑ እስረኞች የሚለቀቁ ይሆናል።
በዚህም መሠረት በመጪው መስከረም ወር በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በመጀመሪያው ዙር የሚፈቱ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ባሉ 18 ወራት ውስጥ ደግሞ ተጨማሪ እስረኞች ደረጃ በደረጃ የሚለቀቁ እንደሚሆን ባለሥልጣኗ አሳውቀዋል።
በሚቀጥሉት 18 ወራት ተጨማሪ አራት ሺህ ወንድ እስረኞች እና ከአንድ ሺህ ያነሱ ሴት እስረኞች በአዲሱ ውሳኔ መሠረት ከእስር የሚወጡ መሆናቸውን የአገሪቱ የፍትሕ ሚኒስቴር ለቢቢሲ አረጋግጧል።
ነገር ግን በዚህ ውሳኔ መሠረት የሚፈቱት እስረኞች በከባድ ወንጀል የተፈረደባቸው እንደማይሆኑ ተገልጿል። ከባድ ወንጀል ፈጽመው አራት ዓመት እና ከዚያ በላይ የተፈረደባቸው እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት ፈጻሚዎች ከሚፈቱት ውስጥ አይካተቱም ተብሏል።
ይህ ውሳኔ ባለፈው ሳምንት በተደረገው ምርጫ ተሸንፈው ከሥልጣን በተነሱት ጠቅላይ ሪሺ ሱናክ ተግባራዊ መደረግ ነበረበት ያሉት ሻባና ማህሙድ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሳቢውን ጉዳይ መፍትሄ ሳይሰጡ አዘግይተውታል በማለት ወቅሰዋል።
ባለሥልጣኗ እንደተናገሩት ያሉት እስር ቤቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ በ99 በመቶ አቅማቸው እየሰሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በሳምንታት ውስጥ ሞልተው እስረኞችን መቀበል አይችሉም ብለዋል።
ይህ የሚከሰት ከሆነ ፖሊስ ጣቢያዎችም በእስረኞች እንደሚሞሉ እና አደገኛ ወንጀለኞች የሚቆዩበት ቦታ ሊታጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቶች በሚመለከቷቸው የወንጀል ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ስለሚችገሩ ሥራቸውን እስከ ማቆም ሊያደርሳቸው እና ፖሊሶችም እርምጃ ለመውሰድ ስለሚቸገሩ ወንጀለኞች ያለስጋት የሚፈልጉትን ሊፈጽሙ ይችላሉ ብለዋል።
እስር ቤቶች ሞልተው ቦታ ከጠፋ እና “መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ወስዶ ማስተካከል ካልቻለ፣ ወጀለኞችን የሚቆጣጠረው የፍትሕ ሥርዓቱ ሥራ ስለሚያቆም፤ ሕግ እና ሥርዓት ይፈርሳል” በማለት አስጠንቅቀዋል።
ነገር ግን ይህ እስረኞችን የመልቀቁ ሃሳብ በሁሉም ዘንድ ድጋፍን አላገኘም፤ የወግ አጥባቂው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ቶም ተገንድሃት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “በየትኛው ዓለም ነው 20 ሺህ የሚደርሱ ወንጀለኞችን ፈትቶ መልቀቅ ጥሩ ሃሳብ የሚሆነው?” ሲሉ ውሳኔውን ተችተዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ሳምንታዊ አሃዝ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ እና በዌልስ ውስጥ 1,161 የእስር ቤት ክፍሎች ብቻ ክፍት ሆነው ይገኛሉ።
እስር ቤቶች በመጨናነቃቸው ምክንያት እስረኞቹ የሚጠበቅባቸውን የቅጣት ጊዜ ከማጠናቀቃቸው በፊት ከመልቀቅ ይልቅ ተጨማሪ የእስር ቤቶችን መገንባት እንደ አማራጭ መታየት አለበት በማለት ሃሳብ ያቀረቡ ፖለቲከኞችም አሉ።
የእስረኞች ማቆያ ቦታ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የፍትሕ ሚኒስቴር 20 ሺህ እስረኞችን የሚይዙ ስድስት እስር ቤቶችን እየገነባ ሲሆን፣ መንግሥት ተጨማሪ 20 ሺህ ፖሊሶችን ለመቅጠር እየሠራ ነው ተብሏል።












