የዩክሬን ኃይሎች ቁልፍ የሆነችውን ምስራቃዊ ከተማን ለቀው እንዲወጡ ታዘዙ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty images
የዩክሬን ኃይሎች ቁልፍ የሆነችውን ሴቬሮዶኔትስክ ከተማን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መተላለፉን የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት አሳውቀዋል።
ሩሲያ የምስራቅ ዩክሬን አካባቢዎችን ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት ከተማዋ በጦርነቱ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎባታል።
"ለወራቶች ያለማቋረጥ ከፍተኛ ድብደባ በተፈጸመባቸው ቦታዎች ላይ መቆየት ትርጉም የለውም” ሲሉ የሉሃንስክ ክልል አስተዳዳሪ ሰርሂ ሃይዳይ ተናግረዋል።
የሩስያ ጦር በቅርብ ቀናት ውስጥ ሴቬሮዶኔትስክን የከበቡ ሲሆን አሁን ደግሞ መንታ ከተማዋ ላይሲቻንስክ ላይ አነጣጥረዋል።
“ወደ አዲስ ስፍራዎች እንዲያፈገፍጉ ትእዛዝ ደርሷቸዋል። ከዚያም ሆነው ዘመቻውን መቀጠል ይችላሉ” በማለት ሃይዳይ አርብ ጠዋት ለዩክሬን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
የከተማዋ አጠቃላይ መሰረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቤቶች በከባድ መሳሪያ ተጎድተዋል ከነዚህም 80 በመቶ የሚሆኑት ላይ የከፋ ጉዳት መድረሱንም አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሴቬሮዶኔትስክ ግዛት ኃላፊ ሮማን ቭላሴንኮ የዩክሬን ወታደሮች አሁንም በከተማዋ እንዳሉ ተናግረዋል።
አርብ እለት ሊበርቲ ለተባለው ሬድዮ እንደተናገሩት የጦሩ መውጣት “የአንድ ሰአት ወይም ቀን ጉዳይ አይደለም” የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብለዋል።
አርብ እለት ቀደም ብለው የዩክሬን ጦር “በሴቬሮዶኔትስክ ከተማ ውጊያ ቀጥሏል” ብለዋል።
በያዝነው ሳምንት ሃሙስ እለት የሩስያ ሃይሎች ከሴቬሮዶኔትስክ እና ከሊሲቻንስክ በስተደቡብ የሚገኙትን ተጨማሪ ግዛቶችን የተቆጣጠሩ ሲሆን ይህም የዩክሬን ሃይሎች በቅርቡ እዚያ ሊከበቡ ይችላሉ የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ነገር ሃይዳይ እንደሚሉት ለሩሲያ ላይሲቻንስክን በፍጥነት መቆጣጠር ፈታኝ እንደሚሆንባት ነው ምክንያቱም ከተማዋ በርካታ የመከላከያ ቦታዎች ስላሏት ነው።
በያዝነው ዓመት የካቲት የጀመረው የሩስያ ወራራ በሁለቱ ከተሞች ላይ ለበርካታ ሳምንታት ትኩረቱን አድርጎ ቆይቷል።
በሉሃንስክ ክልል ውስጥ ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎች ሲሆኑ ፣ እሱም ከዶኔትስክ ክልል ጋር በጋራ ዶንባስ ተብሎ የሚጠራውን ያቀፈም ነው።












