የሒሳብ ቀመር በስሙ የተሰየመለት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪው ፈይሳ ተፈሪ

ፈይሳ ተፈሪ ከተሸለመው ዋንጫ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Feyesa Teferi

በምዕራብ ሸዋ የምትገኘው የባኮ ቲቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ፈይሳ ተፈሪ ባሻሻለው የሒሳብ ቀመር የተነሳ እውቅና ተሰጥቶታል።

የ19 ዓመቱ ፈይሳ፣ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ መጀመሪያ የነበረው የሒሳብ ቀመር የተሰጠውን ጥያቄ ለመመለስ ቢያንስ ከሦስት ደቂቂ በላይ ይጠይቅ እንደነበር ይናገራል።

የ12ኛ ክፍል ሒሳብ መጽሐፍ ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ርዕስ ነው- 'አርቲሜቲክ ሲክዌንስ'።

ፈይሳ ይህንን የሒሳብ መልመጃ ለመስራት እንደ ሌሎች ተማሪዎች ረዥም ሰዓት ወስዶ ለፍቷል።

በኋላ ግን የተሰጠውን ጥያቄ በቀላሉ መስራት ብቻ ሳይሆን የሌሎች የክፍል ጓደኞቹንም ራስ ምታት ማቅለል የሚችልበትን መንገድ አገኘ።

“አሁን እኔ ያገኘሁት ቀመር የሚቀርብልንን ጥያቄ ከአንድ ደቂቃ በታች ለመመለስ ይረዳል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ፈይሳ ‘አርቲሜቲክ ሲኪዌንስ’ በመባል የሚታወቀውን የሒሳብ ቀመር አሻሽሎ በማስተዋወቅ ‘ፈይሳ ቴረም’ በማለት ሰይሞታል።

ይህ ቀመር ለተማሪዎች ውስብስብ፣ ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ እና በቀላሉ ለመረዳት አዳጋች የሆነ እንደነበር ፈይሳ ያስረዳል።

ፈይሳ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀለል ያለ ነው ያለውን ቀመር አስተዋውቋል።

ይህ ቁጥሮች እንደ ታናናሽ ወንድም እና እህቶቹ የሚታዘዙለት ፈይሳ ተወልዶ ያደገው በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ጂማ ገነቲ ወረዳ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በዚህች አነስተኛ ቀበሌ የተከታተለው ፈይሳ፣ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ወደ ባኮ ቲቤ መጥቶ ከዘመዶቹ ጋር ተጠግቶ እየተማረ ይገኛል።

ፈይሳ ያሻሻለው የሒሳብ ቀመር የ12ኛ ክፍል የሒሳብ ትምህርት የመጀመርያው ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ነው።

ይህ የ'አርቲሜቲክስ ሲክዌንስ' ጥያቄን ለማስላት የሚያገለግለው ቀመር an=a [ n-1]d ነው።

አርቲሜቲክስ ሲክዌንስ ቀመር ማለት ተከታታይ ቁጥሮች መካከል ያለን ልዩነት የምናሰላበት መንገድ ነው።

ፈይሳ ይህንን አዲስ የሒሳብ ቀመር ለማግኘት “አንድ ወር እንደፈጀበት” ይናገራል።

በዚህ ባሻሻለው የሒሳብ ቀመር የቀረበለትን ጥያቄ መስራት ሲችል፣ ለሒሳብ መምህሩ እንዳሳየ ፈይሳ ያስታውሳል።

የሒሳብ መምህሩም ከሌሎች አቻ መምህራኖች ጋር በመሆን በተሻሻለው ቀመር የሚሰጡ የሒሳብ ጥያቄዎችን ማቃለል ይቻል እንደሆነ ፈትሸዋል።

ከዚህ በማስከተልም መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦች ጠቁመውት ማስተካከያዎችን አድርጓል።

ከዚያ በኋላ አዲሱ ‘የፈይሳ ቴረም’ በትክክል እንደሚሰራ እና የሚቀርበውን የሒሳብ መልመጃ ሁሉ እንደሚፈታ አረጋገጡ።

የባኮ ቲቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ በላይ በየነ፣ ፈይሳን ሲያሞካሹ ጎበዝ ተማሪ በማለት ብቻ አይደለም።

“የዚህች አገር የወደፊት ተስፋ” በማለት ካደነቁት በኋላ “እርሱ ያገኘውን የሒሳብ ቀመር እስከ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድረስ ተልኮ መገምገሙን” ተናግረዋል።

ፈይሳ በዚህ ባሻሻለው ሒሳብ ቀመር የተነሳ ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ እንዲሁም ከአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እውቅና እንደተሰጠው አቶ በላይ ጨምረው አስረድተዋል።

“አሁን ተማሪዎች ይህንን ቀመር አውቀው እንዲጠቀሙበት ተደርጓል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ስለሚሰራ ተማሪዎች የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና ላይ ተጠቅመውበታል” ይላሉ።

አቶ በላይ ይህ የተሻሻለው የሒሳብ ቀመር፣ በሒሳብ መምህራን እና በሌሎች ባለሙያዎች ተገምግሞ እንደሚሰራ መረጋገጡን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላም ለፈይሳ የተለያዩ ሒሳብ ፈተናዎች ተሰጥተውት በዚሁ የሒሳብ ቀመር ሰርቶ ማሳየት ችሏል።

አምቦ እና አዳማ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ የዘርፉ ምሁራን ቀመሩ እንደሚሰራ አረጋግጠው መመስከራቸውንም አቶ በላይ ይናገራሉ።

 ፈይሳ በበኩሉ በዚሁ የተነሳ አዳማ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው የፈጠራ ውድድር የብር እና የዋንጫ ሽልማት አግኝቷል።

ፈይሳ ያሻሻለው የአርቲሜቲክስ ሲክዌንስ ቀመር

የፎቶው ባለመብት, Feyesa Teferi

'ለሒሳብ ልዩ ፍቅር አለኝ'

ፈይሳ ከሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ሁሉ በሒሳብ የላቀ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ይናገራል።

ቁጥሮች ቤተኞቹ ናቸው። ጨዋታውም ቁም ነገሩም ከቁጥር ጋር ነው።

“እስከማስታውሰው ድረስ አነስተኛው የሒሳብ ውጤቴ 90 ነው” ይላል።

ለሒሳብ ትምህርት ያለው ፍቅር ግን ዩኒቨርስቲ አብሮት ዘልቆ ዲግሪውን ሊሰራበት አይፈልግም።

ከዚያ ይልቅ ልቡ ወደ ሕክምና ሳይንስ፣ ካልሆነም ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ያደላል። እነዚህ ፍላጎቶቹ ካልተሟሉ ግን ሒሳብ ቀጣይ ማረፊያው ነው።

“አንድ ተማሪ አንድ የትምህርት ዓይነት ጎበዝ ሆኖ በሌላው ሊደክም እችላል። እርሱም ብቻ ሳይሆን በአንድ ትምህርት ዓይነት እንኳን፣ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጎበዝ ሆኖ ሌላው ላይ ላይሳካለት ይችላል። እኔም ለዚያ ነው ሌላ ዘርፍ ማጥናት የምፈልገው።”

ለፈይሳ አርዓያዎቹ በዙሪያ ያሉ ተናሪዎች ናቸው “ገጠር ውስጥ ተወልጄ ባድግም፤ በአካባቢያችን ተማሪዎች በተለያየ ፈጠራ ሲሸለሙ እንሰማለን። ይህንን ስሰማ ሁሌም ሞራል አገኛለሁ። እኔም ምሳሌ ሆነውልኛል።”

ቤተሰቦቹም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉለት እና መምህራኖቹ በሒሳብ ላይ በርትቶ እንዲቀጥል ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ይናገራል።