የነቀምቴ ተማሪዎች የቀድሞ መምህራቸውን ውለታ በማሰብ መኪና ሸለሙ

መምህር አቤል ከተበረከተላቸው መኪና ጋር

የፎቶው ባለመብት, Abel

የምስሉ መግለጫ, መምህር አቤል ከተበረከተላቸው መኪና ጋር

ሠሞኑን የነቀምቴ ከተማ የቀድሞ ተማሪዎች የሒሳብ መምህራቸው የነበሩትን ግለሰብ 'ለእኛ ትውልድ ለዋልከው ውለታ' በሚል በ750 ሺህ ብር መኪና ገዝተው መሸለማቸው ተሰምቷል።

እነዚህ በአገር ውስጥ እና በባሕር ማዶ የሚኖሩ የቀድሞ ተማሪዎች፣ ለሒሳብ መምህራቸው ለነበሩት አቤል ቡልቻ መኪና ገዝተው በስጦታ ማበርከት የፈለጉት ያላቸውን ክብርና ፍቅር ከመግለጽ ባለፈ፣ የመምህራቸውን ውለታ በቋሚነት ለመዘከር በመፈለጋቸው መሆኑን ይናገራሉ።

በቁጥር አንድ መቶ የሚሆኑት እነዚህ የቀድሞ ተማሪዎች የመምህራቸውን ውለታ አስታውሰው፣ ስጦታ በመስጠት ሲያመሰግኑ የሌሎች ተማሪዎች ሞራል በማነሳሳት ረገድ ትልቅ ድርሻ መወጣቱን ሽልማቱን የሰሙ ግለሰቦች ይናገራሉ።

አቶ አቤል ባልቻ በነቀምቴ ከተማ በሚገኙ ሦስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተምረዋል። ነቀምቴ ኮምፕርሄንሲቭ፣ ዳርጌ እና ፉልባና የሚባሉ ትምህርት ቤቶች ያስተማሩት አቶ አቤል፣ ከዚህ በተጨማሪም በመኖሪያ ቤታቸው ተማሪዎችን ለማገዝ ያስተምሩ እንደነበር ተማሪዎቻቸው ይናገራሉ።

የቀድሞ ተማሪዎችን በማስተባበር ሽልማቱን ያዘጋጀው ብዙኃን ተሾመ፣ በበኩሉ መምህር አቤል "የወደፊት ሕይወታችን የተሳካ እንዲሆን" የአንበሳውን ድርሻ ተጫውተዋል ሲል ያሞካሻቸዋል።

ብዙኃን የመምህር አቤል የቀድሞ ተማሪዎች ከነበሩት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ አጥንቶ በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ እየሰራ ይገኛል።

እንደ እርሱ ገለጻ መምህር አቤል ሒሳብን ሲያስተምሩ የቁጥር ዘርን በጥቁር ሰሌዳው ላይ በትነው ስሌቱን ለመፈለግ ላይ ታች እንዲሉ ብቻ አያደርጓቸውም ነበር።

በጥቁር ሰሌዳው ላይ በጠመኔ የዘሩት የቁጥር ዘር፣ ተቀምሮ እና በጥንቃቄ ተሰልቶ ውጤት ማስገኘት ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥ ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ትስስር እንዳለው በማሳየት፣ ቁጥርን እንዲወዱና እንዲያጣጥሙት ማድረጋቸውን ይመሰክራል።

ብዙኃን የመምህሩን የማስተማር ስልት ሲመሰክር ሒሳብ እንደ ቀንዳም በሬ ከመሸሽ ይልቅ እንደ ጥሩ ጓደኛ እንዲቀርቡት ማድረጋቸውን ይመሰክራል።

ሳይንስ ትምህርቶችን እንደ ውሃ እንዲጨልጡት እንደ አየር እንዲተነፍሱት በማድረግ ረገድ የመምህሩ ውለታ ከፍ ያለ ነው ይላል።

የሒሳብን ሕግጋት እንዲረዱ እንዲሁም ከ20 ዓመት በላይ የተሰጡ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናዎችን በራሳቸው ተነሳሽነት በመሰብሰብ በመኖሪያ ቤታቸው ተማሪዎቻቸውን ይረዱ እንደነበርም ያስታውሳል።

"ብዙዎቻችንም ለትምህርት ያለን ፍቅር፣ በተለይ ለሒሳብ እና ለሳይንስ ትምህርቶች እንዲጨምር አድርገዋል።"

ብዙኃን እንደሚለው መምህር አቤል፣ ከትምህርት ቤት ውጪ በግል በቤታቸው ውስጥ ለረዥም ዓመታት ልጆችን በሒሳብ ትምህርቶች ይቀርፁ ነበር።

መምህር አቤል ከማስተማር ውጪ "በግላቸው ተማሪዎችን የሚመክሩ እና እንደ አባት የሚመሩ፣ በተለየ ፍቅር ያሳደጉን ሲሆን ሁሉም ተማሪዎች በተለየ አኳኋን ይወዷቸዋል።"

መምህር አቤል የሒሳብ ትምህርትን፣ በቀልድና እና በሕይወት ገጠመኝ እያዋዙ ተማሪዎቻቸውን እያነሳሱ እና እያዝናኑ ያስተምራሉ።

"የሒሳብ ትምህርት እንዴት ከተጨባጭ እውነተኛ ሕይወት ጋር የተቆራኘ መሆኑን በሚገባ እያሳዩ ማስተማራቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።"

ይህ ደግሞ እርሳቸው ያስተማሯቸው ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ያደረገ መሆኑን የሚናገረው ብዙኃን፣ እንደ አገርም የነቀምቴ ከተማ ተማሪዎች በመምህር አቤል ምክንያት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማድረጉን ያስታውሳል።

"ከዚህ በፊት እኛ ሒሳብ ቁጥር ብቻ ይመስለን ነበር። ነገር ግን እኛ ከምንኖረው ኑሮ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ከሕይወት ተሞክሯችን ጋር እያገናኙ እንድንረዳ አድርገዋል።"

መምህር አቤል

የፎቶው ባለመብት, Abel

የምስሉ መግለጫ, መምህር አቤል

ለተማሪዎቻቸው 'የቀለም መልክ' ያሳዩት መምህር አቤል

መምህር የቀለምን መልክ በማሳየት፣ ተማሪዎቻቸው የሰው አውራ እንዲሆኑ ዘወትር ይታትራሉ።

ይህ ውለታቸው ግን ለጨዋታ ማድመቂያ ካልሆነ በስተቀር በአግባቡ ተነስቶ ሲዘከር እምብዛም አይስተዋልም።

የቀለም አባት እና እናት የሆኑት መምህራን ለተማሪዎቻቸው የቤተሰብን ያህል ቀርበው የሕይታቸውን መገንገድ በማቅናት ረገድ ሚናቸው ከፍ ያለ ነው።

የቀድሞ የነቀምቴ ከተማ ተማሪዎች መምህራቸውን የሸለሙት ከረዥም ዓመታት በኋላ ቢሆንም ውለታቸውን ግን በሕይወታቸው ውስጥ ሲያስታውሱት መቆየታቸውን ይናገራሉ።

ይህም ትዝታቸው ነው ከያሉበት ተሰባስበው የመምህራቸውን ውለታ ለመዘከር የበቁት።

በርካታ የመምህር አቤል ተማሪዎች በአገር ውስጥም ሆነ ከባሕር ማዶ የተለያዩ የትምህርት መስኮች አጥንተው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ መሆናቸውን የሚናገረው ብዙኃን፣ ሁሉም በተሰማሩበት መስክ ለአገራቸው የየድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጿል።

ብዙኃን፣ መምህሩን "በተለይ የሒሳብ እና የሳይንስ ትምህርች እንዲሳካልን እና የወደፊት ሕይወታችን መልካም እንዲሆን ብዙ የጣሩልን መምህር ናቸው" በማለት ይገጻቸዋል።

ከመምህር አቤል ጋር ሲነጻጸር ይህ ስጦታ ትልቅ ባይሆንም ሃሳቡ ግን ትልቅ ነው ሲልም ያክላል።

መምህር አቤል ቡልቻ ስለተበረከተላቸው ሽልማት ምን አሉ?

መምህር አቤል ሥራ የጀመሩት መቱ አካባቢ ነው። ከስድስት ዓመት በኋላ ደግሞ ወደ ነቀምቴ ከተማ መጡ። እርሳቸው ወደ ነቀምቴ ሲመጡ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ሁለት ተማሪዎች ብቻ ከፍተኛ ውጤት ሲያመጡ መመልከታቸው "በጣም እንዳሳዘናቸው" ያስታውሳሉ።

በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የነበሩት ይህንን የተማሪዎቹን ውጤት ለመቀየር ወጣት መምህራንን ሰብስበው ማማከራቸውን አቶ አቤል ያስታውሳሉ።

አቶ አቤልና ባልደረቦቻቸውም ተማሪዎቹን በእውቀት ለማስታጠቅ፣ በውጤትም ቀዳሚ ለማድረግ ተጉ፤ ተማሪዎቹም አላሳፈሯቸውም።

የ58 ዓመቱ ጎልማሳ መምህር አቤል፣ "መምህር አያረጅም ስለሚባል እንጂ ለጡረታ እየተቃረብኩ ነው" ሲሉ ይቀልዳሉ።

ይህ ሽልማት ያልጠበቁት መሆኑን የሚናገሩት መምህሩ "እኔ ከዚህ ልጆቹ ካበረከቱልኝ ስጦታ በላይ፣ ያስተማርኳቸው ገሚሱ ዶ/ር ሆኖ፣ የተወሰኑት ፓይለት እንደዚሁም ኢንጂነር ሆነው ማየቱ ይበልጥ ያስደስተኛል። ትውልድን በትምህርት ማብቃትን የመሰለ ደስ የሚያሰኝ ነገር የለም" ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት የሒሳብ መምህሩ አቤል፣ ከዚህም በፊት መኪና እንዳልነበራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ይኖረኛል ብለው አስበውም እንደማያውቁ ይናገራሉ።

"በመምህር ደሞዝ መኪና መግዛት የማይታሰብ ስለሆነ፣ መንጃ ፈቃድ ስለማውጣትም አስቤ አላውቅም።"

መምህር አቤል ተማሪ በነበሩበት ጊዜ የአስተማሪ እና የተማሪ ግንኙነት ጥሩ እንዳልነበረ በማስታወስ እሳቸው ግን "የማስተምራቸውን ልጆች እንደ እኩያ፣ እንደ ወንድም እና እንደ አባት እቀርባቸዋለሁ። ተማሪው ስለቀረብከው ተገቢውን ክብር አይነፍግህም፤ ያከብርሃል እንጂ" ሲሉ ከተማሪዎችቻው ጋር ስላላቸው ቅርበት ያስረዳሉ።

ይህ ስጦታ ለመምህር አቤል ቢሰጥም፣ ትውልድን በመቅረጽ መስዋዕትነት ለከፈሉ የነቀምቴ ከተማ መምህራንን በመወከል እንደወሰዱ መታወቅ አለበት ይላል ብዙኃን።

ብዙኃን በመጨረሻም እሱና ጓደኞቹ ለመምህራቸው ያበረከቱት ስጦታ መጪው ትውልድ አስተማሪውን አክብሮ፣ የመምህሩን ውለታ ሳይዘነጋ፣ ማበረታታት እንደሚገባ ትምህርት ያገኝበታል የሚል ተስፋ አለው።