በምዕራብ ወለጋው ጥቃት ወቅት ታግተው የተወሰዱ ሰዎች እንዳሉ ተገለጸ

ኮሚሽነር ሚሸል ባሽሌት
የምስሉ መግለጫ, ኮሚሽነር ሚሸል ባሽሌት

በምዕራብ ወለጋው ጥቃት ወቅት ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች በታጣቂዎቹ ታግተው መወሰዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን አመለከተ።

ኮሚሽኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት አስመልከቶ ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በርካታ ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውንና የት እናዳሉ እንደማይታወቅ ገልጿል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ቅዳሜ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም ታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በተመለከተ የተለያዩ አሃዞች እየወጡ ቢሆንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለመፈናቀል መዳረጋቸው ተዘግቧል።

ከጭፍጨፋው የተረፉ ነዋሪዎችና መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው ‘ሸኔ’ በመባል የሚታወቀው ታጣቂው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቡድኑ ግን ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጎ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽሌት በመግለጫው ላይ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በጥቃቱ ዙሪያ ፈጣን፣ ገለልተኛና ዝርዝር ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ በአብዛኛው የአማራ ብሔር አባላት በሚኖሩበት ቶሌ ላይ ተፈጽሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ በዋናነት ሴቶችና ህጻናት ስለተገደሉበት ጥቃት እማኞችን ማናገሩን አመልክቶ፣ ታጣቂዎቹ በርካታ ቤቶችን በማቃጠላቸው ቢያንስ 2000 ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።

“በቶሌ መንደር ላይ በተፈጸመው የጭካኔ ግድያና ነዋሪዎችን በኃይል የማፈናቀል ጥቃት ደንግጫለሁ” ያሉት ባሽሌት፣ “የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፈጣን ምርመራ አድርገው የጥቃቱ ሰለባዎችና ቤተሰቦቻቸው እውነቱን እንዲያውቁ፣ ፍትህና ካሳ እንዲያገኙ በተጨማሪም ጥቃት ፈጻሚዎቹንም ተጠያቂ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

ኮሚሽነሯ በታጣቂዎቹ ታግተው ተወስደዋል የተባሉትን ሰዎችን በተመለከተም ባለሥልጣናት “አስፈላጊና ሕጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የታገቱት ሰዎች ነጻነታቸውን እንዲያገኙ” እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመብት ተከራካሪዎችና ሌሎችም ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ሲያርቡ ተደምጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ከተከሰተው በተጨማሪ በጋምቤላ ክልል “በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ እንዲያቀርብ” ማዘዙ ተገልጿል።

በተጨማሪም በሚገኘው ውጤት መሠረት ውሳኔ እና ምላሽ ለመስጠት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ ከምክር ቤት አባላት የተውጣጡ ሁለት ቡድኖችን ማቋቋማቸውንና ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።