በሚያንማር ርዕደ መሬት 1700 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የአንድ ሳምንት ብሔራዊ ሃዘን ታወጀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሚያንማር ባለፈው ሳምንት አርብ በደረሰው አስከፊ ርዕደ መሬት የሞቱ ሰዎች ከ1 ሺህ 700 በላይ ደረሰ።
ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን አውጇል።
በዚህ አንድ ሳምንት ወቅት ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
በሚን አንግ ህላይንግ የሚመራው ወታደራዊ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2021 መፈንቅለ መንግሥት ነው ስልጣን የተቆጣጠረው።
ወታደራዊው መንግሥት አገሪቷን እየመሩ የነበሩትን አንግ ሱን ቺን ማሰርን ጨምሮ በተቃዋሚዎች ላይ የኃይል እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑ ይታወሳል።
ከሚንያማር ሪፖርት ለማድረግ አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርዕደ መሬቱ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ማረጋገጥ ፈታኝ ነው።
ሆኖም የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ጥናት አርብ ዕለት እንዳስታወቀው ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተው ሊሆን አንደሚችል ገልጿል።
አርብ ዕለት በ7.7 ማግኒትዩድ የተለካ ርዕደ መሬት የተከሰተ ሲሆን ከሚያንማር አልፎ በአጎራባች አገራትም ንዝረቱ ተሰምቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሰዎችን ሕይወት ለማዳን እየተተረባረቡ ቢሆንም የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ከፍተኛ የመሳሪያ እጥረት፣ የተቆራረጠ የመገናኛ አውታሮች እና የተበላሹ መንገዶች እና ድልድዮች ፍለጋው ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል።
በሚያንማር የሚገኙ ሆስፒታሎች በርዕደ መሬቱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ ሲሆን በርካቶቹም በተጎጂዎች መጨናነቃቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ ማርጋሬት ሐሪስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢያንስ ሶስት ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጭ ሲሆኑ ሌሎች 22ቱ ደግሞ "በከፊል በመጎዳታቸው አገልግሎት መስጠት ተስኗቸዋል" ብለዋል።
የተጎዱትን ከማከም በተጨማሪ እንደ ኮሌራ ያሉ በሽታዎች እንዳይዛመቱ የረድዔት ሰራተኞች እየተረባረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 8 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ እርዳታ እንዲቀርብ ጥሪውን አድርጓል።
በጦርነት እየታመሰች ባለችው ሚያንማር የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ሊደርስ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።
በጎዳናዎች ላይ የአስከሬኖች ሽታ እየተዛመተ እንደሆነ ቢቢሲ ሰምቷል። የሚያንማር ወታደራዊ መሪዎች ለአራት ዓመታት ሲዋጉት የነበረው ታጣቂ ላይ የአየር ድብደባቸውን ቀጥለዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ርዕደ መሬት እንዳልገታቸውና ክስተቱንም ተከትሎ የአየር ድብደባዎች መፈጸማቸው ተነግሯል።
በአጎራባች ታይላንድ 19 ሰዎች በርዕደ መሬቱ ህይወታቸው አልፏል።
በዛሬው ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በርዕደ መሬቱ ምክንያት በባንኮክ ከተሰነጠቁ ህንጻዎች እንዲወጡ ተደርገዋል።
በመዲናዋ በተደረመሰው ከፍ ያለ ህንጻ ፍርስራሽ ስር ተቀብረው ያሉ 75 የግንባታ ሰራተኞችን በህይወት የመታደግ ስራ ቀጥሏል።
የከተማዋ አስተዳዳሪ እነዚህን ሰራተኞች አሁንም በህይወት ለማግኘት ተስፋ አለ ብለዋል።












