በሚያንማር የመሬት መንቀጥቀጥ ከ1600 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ የነፍስ አድን ጥረቶች ቀጥለዋል

የነፍስ አድን ሥራ እየተሠራ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሚያንማር የተከሰተውን ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በላይ ሰዎች መሞታቸው የተነገረ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በእጃቸው ፍርስራሾችን ሲቆፍሩ መቆየታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ የ1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መኖሪያ የሆነችውን የአገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ማንዳላይን ወደ ሜዳነት ቀይሯል።

ከፍተኛ የመሳሪያ እጥረት፣ የተቆራረጠ የመገናኛ አውታሮች እና የተበላሹ መንገዶች እና ድልድዮች ፍለጋው ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል።

እአአ በ2021 ስልጣኑን የተቆጣጠረው የሚያንማር ወታደራዊ መንግሥት፣ ከአማፂ ቡድኖች ጋር ለአራት ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት እና በፀረ መፈንቅለ መንግሥት ተቃውሞ ምክንያት አብዛኛው የአገሪቱን ክፍል መቆጣጠር አልቻለም።

ከአርብ ጀምሮ የነፍስ አድን ሥራ እየተሠራ እና ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ወደ አገሪቱ እየገባ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ዕርዳታው የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ባለመድረሱ ሰዎች በሕይወት የተረፉትን ለማውጣት እጃቸውን ለመጠቀም እየተገደዱ ነው።

በሰፊው በተጋሩ ቪዲዮዎች ላይ ሁለት ሰዎች በኮንክሪት መካከል ተይዛ ያለችን ሴት ለማውጣት ፍርስራሹን ለማንሳት ሲሞክሩ ይታያል።

ሰዎች ከፍርስራሹ ስር ሆነው እርዳታ ለማግኘት እየጮሁ መሆኑን ቢቢሲ የአካባቢው ነዋሪዎች ባነጋገረበት ወቅት ለመረዳት ችሏል።

በመንደሌይ ከሚገኝ ባለ 12 ፎቅ የመኖሪያ ሕንጻ ፍርስራሽ ስር ከ30 ሰዓታት በኋላ የነፍስ አድን ሠራተኞች አንዲት ሴት በሕይወት ማውጣት ቢችሉም፤ ቀይ መስቀል ግን ከ90 በላይ ሰዎች አሁንም በፍርስራሹ ስር ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግሯል።

በአቅራቢያው ባለከተማ ውስጥ የ12 የቅድመ ትምህርት ተማሪዎችን እና የአንድ አስተማሪን አስከሬን ከመዋዕለ ሕፃናት ፍርስራሽ ስር ባለስልጣናት አግኝተዋል።

በያንጎን፣ በናይ ፒዪ ታው እና በማንዳላይ መካከል ያለው ዋናው መንገድ ላይ የተከሰተው ጉዳት ከፍተኛ የትራንስፖርት መስተጓጎል አስከትለዋል ሲል የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ አገልግሎት ድርጅት ኦቻ ገልጿል።

በተጨማሪም የአስፈላጊ መድሃኒቶች እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ የህክምና አቅርቦቶች እጥረት እንደነበሩ ገልጿል።

ጉዳት የደረሰበት የእሳት አደጋ መከላከያ መስርያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Supplied

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሌላ በኩል ደግሞ የነፍስ አድን ሠራተኞች በሕይወት የተረፉ በሚል ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። "ሰዎችን ማዳን የምንችለውን የምናደርገው ድምጻቸውን ስንሰማ ብቻ ነው" ሲል አንዱ ተናግሯል።

ቅዳሜ ዕለት በመንደሌይ ክያኡክሴ አውራጃ በሲንትካይ ከተማ የሚገኝ የነፍስ አድን ቡድን በአንድ የግል ትምህርት ቤት ፍርስራሾች ውስጥ የነበሩ በርካታ ሰዎችን አውጥቷል። ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ የነፍስ አድን ቡድኖች በደረሱበት ጊዜ ሕይወታቸው አልፎ ነበር። ከተጎጂዎች መካከል ተማሪዎች፣ መምህራን እና የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች ይገኙባቸዋል።

የመሳሪያ እጥረት የነፍስ አድን ሥራውን በእጅጉ ጎድቶታል ሲል አንድ የነፍስ አድን ሠራተኛ ለቢቢሲ በርማ ተናግሯል።

"ባለን መሳሪያ እየሠራን ነው። በፈራረሰው ትምህርት ቤት ስር የምትገኝን ልጅ ለማውጣት ለሰዓታት ጥረት አድርገናል" ብሏል።

በመንደሌይ የሚገኝ ሌላ የነፍስ አድን ሠራተኛ በያንጎን ለሚገኘው የቢቢሲ ጋዜጠኛ እንደተናገረው ከሆነ የኮሙኒኬሽን መስመር በማይሠራበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

"ዋናው ነገር የኢንተርኔት እና የስልክ መስመሮች ስለሌለን እርስ በርስ ለመገናኘት በጣም ከባድ ነው።

የነፍስ አድን ቡድን ደርሷል። ነገር ግን የት እንደሚሄድ አናውቅም ምክንያቱም የስልክ መስመሮች ተዘግተዋል" ብሏል።

አንድ የመንደሌይ ነዋሪ በተመሰቃቀለ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ሰዎች የተቻላቸውን እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በነፍስ አድን ሥራው ላይ ቅንጅት የለም። የሚመራቸውም ሆነ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚነግራቸው የለም። የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸው መተባበር ነበረባቸው። በፍርስራሹ ውስጥ አስከሬን ካገኙ ወዴት እንደሚልኩ እንኳን አያውቁም። ሆስፒታሎች ጉዳት በደረሰባቸው ሰዎች ተጨናንቀው ከአቅማቸው በላይ ሆኗል" ብለዋል ነዋሪው።

ጁንታው የመሬት መንቀጥቀጡ ዋና ማዕከል በሆነችው በማንዳላይ ክልል የተጎዱ ሕንፃዎችን ቁጥር ከአንድ ሺህ 500 በላይ አድርሷቸዋል። የመብራት መቆራረጥ ሁኔታውን አባብሶታል። እንደ ባለስልጣናት ገለጻ መብራቱን ለማስተካከል ቀናት ሊወስድ ይችላል።

በመሬት መንቀጥቀጡ ወቅት ማኮብኮቢያዎቹ ስለተበላሹ የማንዳላይ አየር ማረፊያ አገልግሎት አይሰጥም። ወታደራዊ ካውንስሉ እንደገለጸው አየር ማረፊያውን ወደ ሥራ ለማስገባት እንደሚሠራ እና ጊዜያዊ ሆስፒታል፣ የህክምና እርዳታ ካምፕ እና መጠለያ ተቋቁሟል ብሏል።

መንገዶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

ከማንዳላይ ከ25 ኪሜ በሚርቀው በሳጋንግ ክልሎችን የሚያገናኙ ሁለቱ አሮጌ ድልድዮች ሙሉ በሙሉ ሲፈርሱ አዲሱ ድልድይ በመሰንጠቁ የነፍስ አድን ቡድኖችን ተደራሽነት አስተጓገጉሏል።

"በአሁኑ ሰዓት ለነፍስ አድን ሥራ እንኳን በቂ ሰዎች የሉም። ሬሳ ማንሳት አልቻልንም፤ በጣም ብዙ ሰዎች በፍርስራሾች ስር ይገኛሉ። ሁለቱንም ድልድዮች መሻገር ስለማንችል ሁላችንም በፍርስራሹ ተይዘናል። እባካችሁ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ይምጡና ይታደጉን" ሲሉ የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በቅርቡ የተቆረቆረው ዋና ከተማው እና የወታደራዊ ጁንታ ዋና መሥሪያ ቤት የሆነበት ናይ ፒ ታው በድህረ መንቀጥቀጥ እና በትንሽ ንዝረት ተመቷል። ከተማዋ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ህይወት ከማለፉም በላይ በርካታ ህንጻዎች ፈርሰዋል፤ የተዘጉ መንገዶችም አሉ።