እስራኤል እና ሃማስ አዲስ የተኩስ አቁም ድርድር ለማድረግ ተስማሙ

ባለፉት ቀናት ደቡባዊ ጋዛ በእስራኤል ከባድ የአየር ጥቃት ደርሶበታል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ባለፉት ቀናት ደቡባዊ ጋዛ በእስራኤል ከባድ የአየር ጥቃት ደርሶበታል

ሃማስ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ከሁለት ቀናት በፊት በግብጽ እና በኳታር የቀረበለትን ምክረ ሃሳብ መቀበሉን የቡድኑ ከፍተኛ መሪ አስታወቁ።

የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ፣ አደራዳሪዎች ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት በጋዛ የተኩስ አቁሙ እንዲቀጥል አምስት እስራኤላውያን ታጋቾችን ለመልቀቅ እና ለ50 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚል የቀረበውን ሃሳብ እንደሚደግፍ ገልጿል።

ከጋዛ ውጭ የሚገኙት ከፍተኛ የሃማስ መሪ፣ ካሊል አል-ሀያም ቡድኑ በግብፅ እና በኳታር አደራዳሪዎች የቀረበውን ረቂቅ ምክረ ሃሳብ ማፅደቁን ተናግረዋል።

ሮይተርስ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ግብጽ አዲሱን የተኩስ አቁም ስምምነት በተመለከተ ከእስራኤል ወገን በጎ ምላሽ አግኝታለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት እቅዱን እንደተቀበለው ገልፆ "ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ሙሉ በሙሉ በመተባበር ለአደራዳሪዎቹ ሌላ ምትክ ምክረ ሃሳብ" ማቅረቡን ገልጿል።

ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች ከተስማሙ አዲሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ዛሬ እሁድ ከሚጀመረው የሙስሊሞች የኢድ አልፈጥር በዓል ጋር ሊገጣጠም ይችላል።

ቅዳሜ ዕለት የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ከአደራዳሪዎቹ ጋር የተኩስ አቁም ሃሳብ ላይ ምክክር መደረጉን አስታውቋል።

እስራኤል ያቀረበችው ምትክ ምክረ ሃሳብ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት እንደተደረሰበት ቢገለጽም፣ ምንም ምን ሃሳቦች እንደተካተቱበት የተባለ ነገር የለም።

አሜሪካ በጉዳዩ ላይ በይፋ አስተያየት አልሰጠችም።

እአአ ጥር 19 በሥራ ላይ የዋለው የተኩስ አቁም ስምምነት በዚህ ወር መጀመሪያ ካበቃ በኋላ የእስራኤል ኃይሎች በራፋ በእግረኛ ጦር ዘመቻ ሲጀምሩ፣ በጋዛ ሰርጥ ደግሞ የአየር ድብደባ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

ሁለቱም ወገኖች የመጀመሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት ካበቃ በኋላ ሁለተኛው ዙር ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሃማስ በመጀመሪያው የተኩስ አቁም ምዕራፍ 33 ታጋቾችን ለቅቋል።

በኢራን የሚደገፈው ቡድኑ አሁንም 59 እስራኤላውያን በቁጥጥሩ ስር ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሁሉም በሕይወት ይኖራሉ ተብሎ አይታመንም።

ሃማስ ቀደም ሲል መጀመርያ ላይ ቀርቦ በነበረው መደራደርያ ሃሳብ መሰረት ሁለተኛው የድርድር ምዕራፍም እንዲቀጥል በመጠየቅ፣ የተቀሩት ታጋቾች ሙሉ በሙሉ እንዲለቀቁ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ለቅቆ እንዲወጣ እና ጦርነቱን እንዲቆም ጠይቆ ነበር።

ነገር ግን እነዚያ ድርድሮች ሊካሄዱ አልቻሉም።

እስራኤል እና አሜሪካ በምትኩ ከአንድ ወር በፊት ያበቃው የተኩስ አቁም የመጀመሪያው ምዕራፍ እንዲራዘም ሐሳብ ቢያቀርቡም ጦርነቱ እንደሚያከትም ግን ግልጽ ዋስትና አልተሰጠም።

እስራኤል ሃማስን የተኩስ አቁሙ እንዲራዘም የቀረበውን ሃሳብ አልቀበልም ብሏል ብላ በመወንጀል እአአ ከመጋቢት 18 ጀምሮ በጋዛ ላይ የአየር ድብደባዋን ቀጥላለች።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእስራኤል በደረሰ የአየር ጥቃት ከ900 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀሩት ታጋቾች ቤተሰቦች ኔታንያሁ የተኩስ አቁምን በመጣስ የታጋቾችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል ሲሉ ከስሰዋል።

ከእነዚህ ታጋቾች መካከል አንዱ የሆነው ኤልካና ቦህቦት እንዲፈታ ሲማፀን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ሃማስ ይፋ አድርጓል።

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ይህ ጦርነት የተቀሰቀሰው፣ እአአ ኦክቶበር 7 2023 ሃማስ ደቡብ እስራኤልን ካጠቃ በኋላ ሲሆን፣ በዚህ ጥቃት 1,200 ያህል ሰዎች ሲገድሉ እና 251ዱን አግቶ ወደ ጋዛ ወስዷል።

እስራኤል በበኩሏ በወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ከ50,000 በላይ ፍልስጤማውያንን መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።