እስራኤል ጦሯ "በጋዛ ተጨማሪ ግዛቶችን" እንዲወር አዘዘች

የጋዛ ሰርጥ ተፈናቃዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ሃማስ የተቀሩትን ታጋቾች በሙሉ እስካልለቀቀ ድረስ ወታደሩ "በጋዛ ተጨማሪ ቦታዎችን እንዲወር" እንዲሁም የተወሰኑ ክፍሎችን በቋሚነት እንደሚይዝ ዛቱ።

እስራኤል ካትዝ የአገራቸው ወታደሮች በጋዛ የጀመሩትን የእግረኛ ጦር ጥቃት "በሕይወት ያሉ እና የሞቱት" ታጋቾች እስኪመለሱ ድረስ "አጠናቅረው እንደሚቀጥሉ" ተናግረዋል።

በጋዛ ከሚገኙት 59 ታጋቾች መካከል 24ቱ በሕይወት አሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ ሁለተኛው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የተደረገው ድርድር ውጤት ባለማሳየቱ እጣ ፈንታቸው አጠራጣሪ ሆኗል።

ከጥር ወር ጀምሮ ሲተገበር የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት በዚህ ሳምንት እስራኤል በጋዛ ላይ የጀመረችውን የምድር ዘመቻ እና የቦምብ ጥቃት ተከትሎ በይፋ አብቅቷል።

በጋዛ ሰርጥ ያለው ሁኔታን አስመልከቶ የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ባልደረባ ሳም ሮዝ "በመላው ጋዛ ፍፁም ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ናቸው የሚከሰቱት. . . በጣም፣ በጣም አሳዛኝ" ሲሉ ተናግረዋል።

እስራኤል እና አሜሪካ ሃማስን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም የቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አድርጓል ሲሉ ከስሰዋል።

ሃማስ በበኩሉ "ከአደራዳሪዎች ጋር በሙሉ ኃላፊነት እና ታማኝነት እየተወያየሁ ነው" ብሏል።

ይኹን እንጂ ካትዝ አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ "ሃማስ በእምቢታውን በቀጠለ ቁጥር በእስራኤል ስር የሚቆየው ግዛት እየጨመረ ይሄዳል" ብለዋል።

ካትዝ አክለውም አገራቸው አሁንም በዩናይትድ ስቴትስ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ የቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ "በሕይወት ያሉ እና የሞቱትን ታጋቾች፣ በመካከል የተኩስ አቁም ኖሮ፣ በሁለት ዙሮች መልቀቅ" በሚለው ሀሳብ ተስማምታለች ብለዋል።

ካትዝ "ታጋቾቹ እስኪለቀቁ እና ሃማስ እስኪሸነፍ ድረስ በአየር፣ በባህር እና በየብስ ውግያዎችን በማድረግ ትግሉን እናጠናክራለን" ሲሉ ጽፈዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ በተጨማሪም እስራኤል "የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በጋዛ ነዋሪዎች በፈቃደኝነት የማዘዋወር እቅድ ተግባራዊ ታደርጋለች" ብለዋል።

ትራምፕ አገራቸው የጋዛን ሰርጥ እንደገና እንድትገነባ እና ሁለት ሚሊዮን ፍልስጤማውያንን በዘላቂነት ለማንሳት እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፍልስጤም ባለስልጣን እና ሃማስ ጋዛ "አትሸጥም" ሲሉ የመንግሥታቱ ድርጅት በበኩሉ ማንኛውም ዜጋ ከሚኖርበት ግዛት በግዳጅ ማፈናቀል በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ እና "ከዘር ማጽዳት ጋር አቻ ነው" ሲል አስጠንቅቋል።

በአሜሪካ፣ በኳታር እና በግብፅ የተመራው እና ለወራት የዘለቀው ድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት በሥስት ደረጃዎች አቅርቧል።

እስራኤል እና ሃማስ የእርቁን ስምምነት ከመጀመሪያው ምዕራፍ ባለፈ እንዴት መውሰድ እንዳለባቸው መስማማት አልቻሉም።

አሜሪካ እና እስራኤል የመጀመርያውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማራዘም ባቀረቡት ሀሳብ ምክንያት ድርድሩ ባለበት ሊቆም ችሏል።

ሃማስ ለውጡን ውድቅ በማድረግ እስራኤል "ከስምምነቱ ለመሸሽ ያደረገችው ግልጽ ሙከራ" ነው ብሏል።

ማክሰኞ ዕለት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ከፍተኛ የአየር ድብደባ መክፈቷን ተከትሎ በሁለት ቀናት ውስጥ ከ430 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ይህም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳከተመለት አሳይቷል።

ሐሙስ ዕለት ሃማስ ሦስት ሮኬቶችን ወደ ቴል አቪቭ አስወነጭፏል ።

የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ዴቪድ ሜንሰር ሃማስን በመወንጀል ቡድኑ "እያንዳንዱን ታጋቾችን የማስለቀቅ ስምምነት ውድቅ አድርጓል" ብለዋል።

አርብ ዕለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጠባባቂ የአሜሪካ አምባሳደር ሃማስን ለቀጠለው ግጭት እና እንደገና ለጀመረው ጦርነት ተጠያቂ አድርገዋል።

ዶሮቲ ሺአ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደተናገሩት "ሃማስ የመሸጋገርያውን ምክረ ሃሳብ ቢቀበል ኖሮ እያንዳንዱ ሕይወት መጥፋት ይቀር ነበር" ብለዋል።

ሃማስ ድርድሩን መቋረጥ ኃላፊነቱን እንደማይወስድ በመግለጽ "በተሳትፎው እንደቀጠለ" መሆኑን እና "ከአደራዳሪዎቹ ጋር በሙሉ ኃላፊነት እና በታማኝነት እየተሳተፍኩ" ነበር ብሏል።

ሃማስ በቴሌግራም ገጹ ላይ በሰጠው መግለጫ "የእስረኞች ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል እና የእስረኞች መፈታትን የሚያረጋግጡ እንዲሁም ለቅቀው እንዲወጡ የሚያስችሉ [የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሰርጥ] በዊትኮፍም ሆነ በሌሎች የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ላይ እየተወያየን ነው" ሲል ጽፏል።

ካትዝ በመግለጫቸው የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ዒላማ ከሚያደርግባቸው አካባቢዎች ሠላማዊ ዜጎች እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ከዚህ ቀደም የተሰጡ ትዕዛዞች በፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ዘንድ አለመረጋጋትን ፈጥረዋል።

አብዛኛዎቹ ፍልስጤማውያን በጦርነቱ በተደጋጋሚ የተፈናቀሉ ሲሆን አሁን አስተማማኝ የሚሉት የቀራቸው አማራጭ የለም።

እስራኤል በሃማስ ላይ ጫና ለመፍጠር በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ጋዛ የሚገቡትን የምግብ፣ የነዳጅ እና የሕክምና አቅርቦቶች በሙሉ አግዳለች።

እአአ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ሃማስ በእስራኤላውያን ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ 251 ደግሞ ታግተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የእስራኤል ጦር ሃማስን ለማጥፋት በሚል በጋዛ ሰርጥ ዘመቻ ከፍተዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ከ49,500 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የገለፀ ሲሆን፣ በሰርጡ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እና መሠረተ ልማቶች ላይ መጠነ ሰፊ ውድመት እየደረሰ ነው።