በእስራኤል እና ሃማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ምን ገጠመው?

የፎቶው ባለመብት, EPA
የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተጀመረ ከሁለት ወራት በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ ተከታታይ የአየር ድብደባ ፈፅሟል።
በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለጸው ከሆነ ከ400 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብሏል። በፍርስራሽ ውስጥ ብዙ ሰዎች እንደተቀበሩ እና ከሟቾች መካከል ሕጻናት እንደሚገኙበት ከስፍራው የወጡ ምስሎች ይጠቁማሉ።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ የሃማስ ንብረት የሆኑትን "የሽብር ዒላማዎች" መምታቱን አስታውቋል።
በርካታ የሃማስ ከፍተኛ አመራሮችም ተገድለዋል ተብሏል።
ከሳምንታት አንጻራዊ መረጋጋት በኋላ የፈጸመው የአሁኑ ጥቃት ባለፈው ዓመት መስከረም 26 ሃማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ከፈጸመ እና ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በጋዛ በርካታ ሰዎች ከሞቱበት ቀናት መካከል አንዱ ሆኗል።።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ምን ይዟል?
ጥር 19 የጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት ደረጃዎች አሉት።
ስምምነቱ ጋዛ ውስጥ በሃማስ የተያዙ ታጋቾችን በእስራኤል በሚገኙ የፍልስጤም እስረኞች መለዋወጥን ያካተተ ሲሆን የመጨረሻው ግብ ደግሞ ጦርነቱን ማስቆም ነበር።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሃማስ አንድ ሺህ 800 በሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞች ምትክ 25 የእስራኤል ታጋቾችን እና ስምንት አስከሬን ለቅቋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ሕዝብ ከሚበዛባቸው የጋዛ አካባቢዎች በመልቀቁ የተፈናቅሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።
የሁለተኛው ምዕራፍ ድርድር በየካቲት 4 ይጀመራል ተብሎ ነበር። ነገር ግን ይህ አልተሳካም።
ሁለተኛው ምዕራፍ ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲኖር፤ የእስራኤል ኃይሎች ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ እና የተቀሩ ታጋቾች ሙሉ በሙሉ እንዲፈቱ የታሰበ ነበር።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ የቀሩትን የታጋቾች አስከሬን መመለስ እና ዓመታትን ይፈጃል ተብሎ የሚጠበቀውን የጋዛ መልሶ ግንባታን መጀመር ነበር።
ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ?
እስራኤል ከጥር 2 ጀምሮ ምንም አይነት የሰብአዊ ዕርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ከለከለች።
በትራምፕ አስተዳደር የቀረበውን የተኩስ አቁም እንዲያራዝም ሐማስ ላይ ጫና ለመፍጠር በሚል ነበር።
በዚህ ሃሳብ መሰረት ከታጋቾቹ ውስጥ ግማሹ መጀመሪያ ላይ ቀሪዎቹ ደግሞ መጨረሻ ላይ ይለቀቃሉ ።
ሃማስ በበኩሉ ሁለተኛው ምዕራፍ ድርድር በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የበላይነት በተካሄደው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በተገለፀው መሰረት እንዲቀጥል አጥብቆ ገለጸ።
በቀጣይ በሚለቀቁት የታጋቾች ቁጥር እና የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ የሚወጡበትን ጊዜ በተመለከተ በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።
የቢቢሲ ኒውስ አረብኛ የጋዛ ዘጋቢ የሆነው አድናን ኤል-ቡርሽ "ከእስራኤል፣ ከሃማስ እና ከአስታራቂዎች በርካታ ሃሳቦችን አይተናል። እነዚህ ሁሉ የተደባላለቁ ናቸው" ሲል ገልጾታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተኩስ አቁም አክትሞለታል?
ይህ የእስራኤል ጥቃት ሃማስ እንዲደራደር ጫና ለመፍጠር ያለመ ወይንም ሙሉ በሙሉ ወደ ጦርነት ለመግባት የተደረገ የሚለውን ጊዜ ይነግረናል።
ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም እና ታጋቾቹን ለማስፈታት የቀረበውን ሃሳብ "በተደጋጋሚ" ውድቅ በማድረግ በእስራኤል ተከሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኦረን ማርሞርስቴይን "ከአሁን በኋላ እስራኤል በሃማስ ላይ ወታደራዊ ጫና በመጨመር እርምጃ ትወስዳለች" ብለዋል።
ማርሞርስቴይን እንደተናገሩት ከሆነ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም በሃሳብ ደረጃ ብትስማማም "ሃማስ አይሆንም ስላለ ሌላ አማራጭ የለም" በማለት በጋዛ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።
በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት የተኩስ አቁም ንግግሮቹ "አብቅቶላቸዋል" ወይ ተብለው የተጠየቁት ማርሞርስቴይን፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከሁለት ሳምንት ተኩል በፊት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
"የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለ42 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በስምምነቱ መሠረት ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላው በፍጥነት አይሸጋገርም" ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር እስራኤል ካትዝ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ከሆነ "የታገቱት በሙሉ እስካልተመለሱ እና ሁሉም የጦርነት ዒላማዎቻችን እስካልተሳኩ" በጋዛ ጦርነቱን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ሃማስ በበኩሉ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እና በመቀልበስ አሸምጋዮች እስራኤልን "ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ" ማድረግ አለባቸው ብሏል።
አሸምጋዮች ሁለቱንም ወገኖች ወደ ክብ ጠረጴዛ ሊመልሱ ይችላሉ የሚል ተስፋ አሁንም አለ።
ሃማስ ድርድሩን ለማስቀጠል ታጋቾችን እና አስከሬኖችን ለመልቀቅ ተዘጋጅቶ ሊሆን እንደሚችል የቢቢሲ ኒውስ የአረብኛው አድናን ኤል-ቡርሽ ዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
የእስራኤል ጥቃት መሰንዘር የጀመረው በረመዳን ጾም ወቅት ነው።
"ጸሐይ ሳትወጣ ምግብ ከመብላታችን በፊት ድንገት ቤቱ በላያችን ላይ ፈርሶ ከየአቅጣጫው ፍርስራሹ ሲወድቅ አገኘነው" ሲሉ የዚን አልዲን ቤተሰብ ለቢቢሲ ኒውስ አረብኛ ተናግረዋል።
እስራኤል ከመጋቢት 2 ጀምሮ ለጋዛ ሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎች የሚደርሰውን ሁሉንም ምግብ፣ መድኃኒት፣ ነዳጅ፣ መብራት እና ሌሎች ድጋፎች አቋርጣለች።
ከአሁኖቹ ጥቃቶች በፊትም በግምት 70 በመቶ የሚሆኑ ሕንፃዎች ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ሙሃናድ ሃዲ ሁኔታውን "የማይታሰብ" ሲሉ ገልጸውታል።
በዌስት ባንክ የሚገኘው የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ቃል አቀባይ ኔባል ፋርሳክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በመቶዎች የሚቆጠሩ የተጎዱ ሰዎች በአንድ ጊዜ መድረሳቸውን ተከትሎ ሆስፒታሎች "ተጨናንቀዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው የተቃጠሉ እና የተሰበሩ ሰዎችን የሚያጠቃልሉ ሲሆን በርካቶች ቀዶ ህክምና በመጠባበቅ ላይ ናቸው ሲሉ የጋዛ ሆስፒታሎች ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ዛክት ተናግረዋል።
"ጥቃቶቹ በጣም ድንገተኛ ስለነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆናቸው በቂ አልነበሩም። እናም ተጨማሪ ሐኪሞች በአስቸኳይ ተጠርተዋል" ብለዋል።
ቢቢሲ አረብኛ ከፍርስራሽ ውስጥ የወጣውን የአህመድ ሞይን አል-ጀምላ እህትን አነጋግሯታል።
"ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ለመግባት ተራውን ወለሉ ላይ ተኝቶ እየጠበቀ ነው" ብላለች።
የእስራኤል ጦር በደቡብ ወደ ሚገኘው ዃን ዮኒስ ወይም በጋዛ ከተማ ምዕራባዊ አካባቢዎች እንዲሄዱ ለነዋሪዎች ትእዛዝ አስተላልፏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል ታጋቾ መጨረሻስ?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት እንደገለጸው ከሆነ ለጥቃቱ መንስኤ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ ሃማስ "ታጋቾቻችንን ለመፍታት በተደጋጋሚ ፈቃደኛ ባለመሆኑ" ነው።
እንደ እስራኤል ገለጻ በጋዛ 59 ታጋቾች ይገኛሉ ተብሎ ሲገመት ከእነዚህ ውስጥ 24 ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
የታጋቾቹን ቤተሰቦችን የሚወክል ቡድን በበኩሉ የእስራኤል መንግስት አዲስ የአየር ድብደባ በማድረግ "ታጋቾቹን ለመተው" መርጧል ሲል ከስሷል።
በመላው እስራኤል አዲስ የተቃውሞ ሰልፎችን ማደራጀት የጀመረው ሆስቴጅስ ኤንድ ሚሲንግ ፋሚሊስ ፎረም ባወጣው መግለጫ "የቤተሰቦች፣ የታጋቾች እና የእስራኤል ዜጎች ትልቁ ፍርሃት እውን ሆኗል" ብሏል።
ዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ የእስራኤል አምባሳደር ማይክል ኦረን ለቢቢሲ ሬዲዮ 4 ቱዴይስ ፕሮግራም እንደተናገሩት "ለእስራኤል ጥሩ አማራጭ የለም።
"በመጥፎ እና በከፋ ነገር መካከል ያለ ምርጫ ነው። ምክንያቱም ሃማስ ታጋቾቹን እንዲለቅ ወታደራዊ ጫና ብታደርግ ታጋቾቹን ሊገድሉ ይችላሉ።"
"ስለዚህ እስራኤል አሁን ወታደራዊ እርምጃ በድጋሚ በመጀመር በቀሪዎቹ ታጋቾች ላይ ሞት ልትፈርድ ነው" ብለዋል።
ሃማስ በጋዛ ለሞቱት ታጋቾች እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን የእስራኤል መንግሥት አዲስ ጥቃት ለመሰንዘር መወሰኑ ታጋቾቹን "ላልታወቀ ዕጣ ፈንታ" እንዳጋለጣቸው ተናግሯል።
ሌሎች አገሮች ምን ምላሽ ሰጡ?
እስራኤል ጥቃቱን አስመልክቶ ለዋይት ሃውስ ቀድማ ማሳወቋን ዩናይትድ ስቴትስ አረጋግጣለች።
የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ብሪያን ሂዩዝ በሰጡት መግለጫ "ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም ታጋቾችን መልቀቅ ይችል የነበር ቢሆንም ግን እምቢተኝነትን እና ጦርነትን መርጧል።"
በድርድሩ ላይ ከተሳተፉት አገራት አንዷ የሆነችው ግብፅጽ በበኩሏ ጥቃቶቹ "የተኩስ አቁሙን መጣስ" እና "አደገኛ መዘዝ ያለው" ስትል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ ታሚም ዃላፍ በኩል አሳውቃለች።
ቻይና ጉዳዩ "በጣም አሳስቧታል" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ ገልጸው፤ ሁለቱም ወገኖች "ወደ መባባስ ሊመራ የሚችል ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ" ጠይቀዋል።
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ "ውጥረቶችን የሚያባብስ ሌላ አዙሪት" ሲሉ ገልጸዋል ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጥቃቱ "የተደናገጡ" መሆኑን ገልጸው የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲከበር አጥብቀው ተማጽነዋል።
ቀጥሎ ምን ይሆናል?
የእስራኤል አዲስ ጥቃት ሃማስ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ያቀረቡትን ሃሳብ እንዲቀበል ጫና ለማድረግ ያለመ መሆኑን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የፖለቲካ ምንጮች ይገልጻሉ።
ጦርነቱን እንደገና ለመጀመር በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ መንግሥት እና በጥምረታቸው መካከል ከፍተኛ መተባበር አለ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ኢያል ዛሚር ሆነው በመሾማቸው፣ ኔተንያሁን እንደ ከዚህ ቀደሙ ከወታደራዊ አመራሮች የሚገጥማቸው ተቃውሞ አይኖርም።
ኔታንያሁ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥታቸው ውስጥ ከበጀት ክፍፍል ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተግዳሮት ያለባቸው ቢሆንም በጋዛ ዳግም ጦርነቱን መጀመር አጋሮቻቸውን እና ጥምር መንግሥቱን ለማረጋጋት ያግዛቸዋል ተብሎ ይታመናል።












