ከፍልስጤም ድጋፍ ጋር በተያያዘ 300 የውጭ አገር ተማሪዎች ቪዛ መሰረዙን አሜሪካ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፍልስጤም ድጋፍ ጋር በተያያዘ 300 የውጭ አገር ተማሪዎች ቪዛ መሰረዙን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ገለጹ።
በዩኒቨርስቲዎች ቅጥር ግቢ ለፍልስጤም የሚደረጉ የድጋፍ ሰልፎችን ለመግታት የትራምፕ አስተዳደር እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች አንዱ ነው ተብሏል።
"በዚህ ወቅት ከ300 በላይ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ነው በጋያና ጉብኝታቸውን እያደረጉ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
"ከእነዚህ ቀውሶች አንዱን ባገኘን ቁጥር ፤ በየቀኑ የምናደርገው ነን" ብለዋል።
አስተዳደራቸው ጸረ እስራኤል ነው የሚል ትርክት ከሚያራምድባቸው ዩኒቨርስቲዎች መካከል የምን ያህል ተማሪዎች ቪዛ እንደተሰረዘ ተጠይቀው ነው ይህንን ያሉት።
በቱፍትስ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ተማሪ ቱርካዊ ከቀናት በፊት በኢሚግሬሽን ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን ሩቢዮ ይህንን ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለዋል።
ሩሜሳ ኦዝቱርክ ከቦስተን ማሳቹተስ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ላይ ጭምብል ባጠለቁ እና የሲቪል ልብስ በለበሱ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት በማይታወቅ መኪና መወሰዷን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።
በፉልብራይት የስኮላርሺፕ ፕሮግራም የተማሪ ቪዛዋን ያገኘችው ኦዝቱርክ በህጻናት ጥናት እና በሂውማን ዴቨሎፕመንት ዶክትሬቷን እያጠናች ነው።
የቱርካዊቷ ተማሪ ቪዛ ለምን እንደተሰረዘ ሩቢዮ ተጠይቀው ነበር።
"በሁሉም ቦታ ተናግሬዋለሁ፤ ድጋሚ እናገራለሁ። በተማሪ ቪዛ ወደ አሜሪካ ከመጡ በኋላ፤ የመጡት ለመማር ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርስቲዎችን በሚያወድሙ እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ፣ ተማሪዎችን ለማዋከብ፣ ህንጻዎችን ለመቆጣጠር እና በአጠቃላይ ሁከት ለመፍጠር ከሆነ ቪዛ አንሰጥም" ብለዋል።
በተማሪዋ ላይ ክስ ስለመቅረቡ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።
ተማሪዋ ሉዊዚያና በሚገኝ የስደተኞች ማሰሪያ ማዕከል ተወስዳለች።
አንድ የፌደራል ዳኛ በማሳቹስተስ እንድትቆይ ውሳኔ ቢያስተላልፉም ነገር ግን ተማሪዋ በሉዊዚያና እንደምትገኝ የፌደራል መዛግብት ያሳያሉ።
በፍልስጤም የድጋፍ ሰልፎች ላይ ትሳተፍ የነበረችው የ30 ዓመቷ ተማሪ በምን እንደተወነጀለች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ተማሪዋ ባለፈው አመት ዩኒቨርስቲዋ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ካላቸው ኩባንያዎች ጋር ሽርክና እንዲያቆም እና "በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ጭፍጨፋ" እውቅና እንዲሰጥ ከሌላ ጸሃፊ ጋር በመሆን በጋራ በተማሪዎች ጋዜጣ ጽፈው ነበር።
"በመላው አገሪቷ እንዳያነው ሀሳቧን በነጻነት የመግለጽ መብቷን መጠቀሟ ለእስር እንዳደረጋት የሚያሳይ ነው" ሲሉ የተማሪዋ ጠበቃ የሆኑት ማህሳ ካንባባይ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ይህ እስር በአሜሪካ ውስጥ ለፍልስጤም ድጋፋቸውን የሰጡ የውጭ አገር ተማሪዎች ላይ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ እየወሰደው ያለው እርምጃ ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣናት የኢሚግሬሽን እና የዜግነት ህግን እየተጠቀሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ይህም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት "የውጭ ፖሊሲ እና የብሔራዊ ደህንነት ጥቅም" ተጻራሪ ናቸው የሚላቸውን የሌላ አገር ዜጎች ከአገር እንዲባረሩ ይፈቅዳል።
በኮለምቢያ ዩኒቨርስቲ ባለስልጣናት እና የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች መካከል የተካሄዱ ድርድሮችን ያሸማገለው ታዋቂው የኮለምቢያ ዩኒቨርስቲ እና የፍልስጤም ደጋፊ ማህሙድ ካሊል በትራምፕ አስተዳደር ያለ ክስ ታስሮ ይገኛል።
ትራምፕ በነዚህ ተቃውሞዎች ላይ የሚሳተፉ አሜሪካውያን ተማሪዎች እንደሚባረሩ አስጠንቅቀዋል።
ማህሙድ በኢሚግሬሽን ባለስልጣናት የታሰረው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "አሜሪካዊ ባልሆኑ ተግባራት" ይሳተፋሉ ያሏቸውን ተማሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው።
ማህሙድ ምንም አይነት የወንጀል ክስ ያልተመሰረተበት ሲሆን እስሩ አገር አቀፍ ተቃውሞን አስነስቷል።
የማህሙድ ባለቤት የአሜሪካ ዜጋ ስትሆን የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ነች።
የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናቸውን ዩኒቨርስቲዎች እንዲያቆሙ እየጠየቁ ይገኛሉ።
እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።












