ፖላንድ የስደተኞች ጥገኝነት የመጠየቅ መብትን ልታግድ ነው

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ አገራቸውን ከቤላሩስ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ቅዳሜ ዕለት ጎብኝተዋል

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ መንግሥታቸው በቤላሩስ ድንበር በኩል ወደ ፖላንድ የሚገቡ ስደተኞችን ጥገኝነት የመጠየቅ መብት ለጊዜው እንደሚያግድ ገለፁ።

ቱስክ ይህን ያስታወቁት የፖላንድ ባለስልጣናት ጥገኝነት የመጠየቅ መብትን እስከ 60 ቀናት ድረስ እንዲያግዱ የሚፈቅደው አወዛጋቢ ሕግ በፕሬዚደንት አንድርዜጅ ዱዳ ከተፈረመ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቱስክ መንግሥታቸው ሕጉን "ያለ ምንም መዘግየት" እንደሚያፀድቅ ሲናገሩ፣ ዱዳ በበኩላቸው ለውጡ በአገሪቱ ድንበሮች ላይ ያለውን ፀጥታ ለማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ሕጉ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ የአውሮፓ ኅብረት በፖላንድ ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ተችተውታል።

የመብት ተሟጋቾቹ፤ "ፖላንድ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ እና የአውሮፓ ኅብረት ግዴታዎችን ይጥሳል" በማለት የአገሪቱ ፓርላማ ሕጉን ውድቅ እንዲያደርግ ባለፈው ወር ጠይቀው ነበር። ይህ እርምጃ "ከዚህ ቀደም የፖላንድ ባለስልጣናት ሕገወጥ እና ተገቢ ያልሆነ ጫና ሲያደርጉበት የነበረውን የፖላንድ ቤላሩስ ድንበርን ሙሉ በሙሉ ሊዘጋው ይችላል" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

መንግሥት ከዚህ ቀደም እገዳው የሚተገበረው በመንግሥት ደህንነት ላይ ስጋት በሚፈጥሩ ሰዎች፣ ድንበሩን በኃይል ጥሰው ለመግባት በሚሞክሩ አመጸኛ ስደተኞችን የመሳሰሉ ላይ ብቻ ነው ሲል ተናግሯል።

ብቻቸውን ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ እድሜያቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ታዳጊዎች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አረጋውያን ወይም ሕሙማን፣ ወደ መጣበት አገር ቢመለስ ለ"ከፍተኛ አደጋ የሚጋለጥ" ማንኛውም ግለሰብ እና እንደ ቤላሩስ ስደተኝነትን እንደ መሳርያነት በመጠቀም ከተከሰሱ አገራት ለሚመጡ ሕጉ ተፈጻሚ አይሆንም።

የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፖላንድ ከቤላሩስ ጋር የምትጋራውን 186 ኪሎ ሜትር ድንበር 5.5 ሜትር ከፍታ ባለው የብረት አጥር አጥራለች

ቱስክ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያቀረቡትን ትችት ውድቅ አድርገዋል።

"ማንም ሰው ስለ ሰብዓዊ መብቶች መጣስ፣ጥገኝነት የማግኘት መብት ክልከላ አላወራም። እኛ እያወራን ያለነው በሉካሼንኮ [የቤላሩስ ፕሬዝዳንት] ቡድኖች ተደራጅተው በሕገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ሰዎች ማመልከቻ ስላለመቀበል ነው" ሲሉ በጥቅምት ወር ተናግረው ነበር።

እአአ ከ 2021 ጀምሮ ፖላንድ፣ ሊትዌኒያ፣ ላቲቪያ እና ፊንላንድ በሕገ ወጥ መንገድ ከቤላሩስ እና ሩሲያ ወደ አገራቸው የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ፖላንድ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን እና የድንበር ጠባቂዎችን ከቤላሩስ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር እንዲጠብቁ አሰማርታለች።

ድንበሩ 5.5 ሜትር ከፍታ ባለው የብረት አጥር የታጠረ ሲሆን በአጠቃላይ 186 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች ከ2021 ጀምሮ በቤላሩስ፣ ፖላንድ፣ ሊትዌኒያ እና ላትቪያ አዋሳኝ ድንበር ላይ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች መሞታቸውን ይናገራሉ።

የአውሮፓ ኅብረት ምሥራቃዊ ክፍል አገሮች እና የአውሮፓ ኮሚሽን የቤላሩስ እና የሩሲያ ባለሥልጣናትን ፍልሰትን እንደ መሳርያነት በመጠቀም ኅብረቱን ለማተራመስ አዲስ መንገድ መያዛቸውን በመግለጽ ይከስሷቸዋል።