በሱዳን ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ በተነሳ እሳት የሁለት ሕጻናት ሕይወት አለፈ

በሱዳን በትግራይ ጦርነት የተፈናቀሉ በሚኖሩበት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በተከሰተ የእሳት አደጋ ምክንያት ሁለት ሕፃናት ሕይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።
ቃጠሎው የተከሰተው ከመጠለያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ በሆነው ኡምራ ኩባ እንደሆነ የሱዳን ነዋሪ የሆነው ጋዜጠኛ መድኃኔ ግደይ ለቢቢሲ ተናግሯል።
አደጋው የተከሰተው ሐሙስ መጋቢት 11/2017 በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 7፡00 ገደማ መሆኑን ጋዜጠኛ መድኃኔ ገልጿል።
መድኃኔ "በቃጠሎው ምክንያት 14 የሚሆኑ በሸራ የተሠሩ መጠለያዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወድመዋል" ሲል አደጋው ያስከተለውን የንብረት ውድመት ያስረዳል።
"በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነው። ያላቸው ንብረት ሙሉ በሙሉ ወድሟል።"
በመጠለያ ጣቢያው የሚኖሩ ስደተኞች የእሳት አደጋውን ማስቆም እንደተሳናቸው እና መደዳውን ተሰድረው የነበሩ የሸራ መጠለያዎች መውደማቸውንም ይገልጻል።
ከግላዊ ንብረታቸው በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩኤንኤችሲአር) እና ሌሎች የተራድዖ ድርጅቶች ለስደተኞች የሰጡት ንብረት እና ወርሀዊ እርዳታ መውደሙን ይናገራል።
በእሳት አደጋው ምክንያት ሁለት ሕፃናት ሕይወታቸው ማለፉን ጋዜጠኛ መድኃኔ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ከሁሉም በላይ በጣም የሚያሳዝነው ሁለት ሕፃናት በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ነው። የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው። አንድ የ6 ዓመት እና የሁለት ዓመት ሕፃን ሕይወታቸው አልፏል" ብሏል።
ከአራት ዓመታት በፊት በትግራይ በፌደራሉ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያት በርካታ የምዕራብ ትግራይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ ሱዳን መሰደዳቸው ይታወሳል።
በዚህ ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ወደ ሱዳን ከተሰደዱት በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በተለይ በትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይነገራል።
የፌዴራሉ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ የሚል ቢኖርም "የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት አካላት የሚጠበቅባቸውን ያህል አልፈጸሙም በሚል ተስፋቸው እየተሟጠጠ መምጣቱን" ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መናገራቸው ይታወሳል።
በመቶ ሺዎችን ለህልፈት ዳርጓል የተባለው የትግራይ ጦርነት ካበቃ በኋላ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሰዎች ተፈናቅለው እዚያው በክልሉ ውስጥ እና ድንበር ተሻግረው ከ60,000 በላይ ደግሞ በጦርነት ውስጥ በምትገኘው ሱዳን ውስጥ ይገኛሉ።
ኡምራ ኩባ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው የመጡ መሆናቸው ጋዜጠኛ መድኃኔ ይናገራል።
ጋዜጠኛው እንደሚናገረው አካባቢው በጣም ሞቃታማ በመሆኑ የእሳት አደጋ ከተነሳ የመዛመት ዕድሉ እጅግ የሰፋ ነው።
"በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አካባቢ የእሣት አደጋ ሠራተኞች ባለመኖራቸው አደጋ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል" ይላል።
አክሎ ሱዳን የሚገኙ አብዛኛዎቹ መጠለያ ጣቢያዎች ተቀጣጣይ ከሆነ እንደ እንጨት እና ብረት ካሉ ቁሳቁሶች እንደሚሠሩ መመልከቱን ይናገራል።
መድኃኔ በአደጋው ምክንያት ልጆቻቸውን ያጡትን ቤተሰቦች አግኝቶ ማናገሩን አሳውቆ ከባድ ሀዘን ላይ እንዳሉ ያስረዳል።
"ስደተኞቹ እዚህ አምስት ዓመታት ቆይተዋል። ወደ ቀያችን ወደ ሁመራ እንመለሰላን የሚል ተስፋ ነበራቸው። የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ከዛሬ ነገር ወደ ቀያችን እንመለሳለን በሚል ተስፋ ነው ያሉት። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነው ልጆቻቸውን በእሳት አደጋ ያጡት።"
በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በርካታ የእርዳታ ድርጅቶች ከሱዳን በመውጣታቸው ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ሰብዓዊ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነም ይገልፃል።
መድኃኔ እንደሚለው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ በመውደሙ ከሚያውቋቸው ሌሎች ስደተኞች ጋር ተጠግተው ነው እየኖሩ ያሉት።
"ተስፋቸው አዲስ መጠለያ ጣቢያ እንዲቋቋምላቸው ሳይሆን ወደ መኖሪያቸው ተመልሰው ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት ነው።" ይላል












