የሱዳን ጦር ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ቤተ መንግሥቱን መልሶ ተቆጣጠረ

የሱዳን ጦር አባላት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሱዳን ጦር ተፋላሚውን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በማሸነፍ ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ካርቱም የሚገኘውን ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት መልሶ መቆጣጠሩን ወታደራዊ መሪዎች ገለጹ።

በደስታ የተሞሉ ወታደሮች ጠመንጃቸውን ሲያወዛውዙ፣ ሲጮሁ እንዲሁም ተንበርክከው ሲጸልዩ በማህበራዊ ሚዲያ የተጋሩ እና ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ቪዲዮዎች አሳይተዋል።

በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተሸንፎ ከመዲናዋ ተባርሮ የነበረው የሱዳን ጦር ከሁለት ዓመት በኋላ መዲናዋን ካርቱምን መልሶ ለመቆጣጠር የተቃረበ ይመስላል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

የጦሩ ቃል አቀባይ ነቢል አብደላህ በመንግሥታዊው ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ሰራዊታቸው በማዕከላዊ ካርቱም የሚገኘውን ቤተ መንግሥት እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን መቆጣጠሩን ነው።

"ሰራዊታችን የጠላት ተዋጊዎችን ድባቅ በመምታት ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያዎችን ማርኳል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ካርቱም ለበርካቶች ህይወት መቀጠፍ የሆነው የአገሪቱ የእርስ በርስ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረባት እንዲሁም ከፍተኛ ፍልሚያዎች የተካሄዱባት ናት።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አብዛኛውን የካርቱምን ክፍል እንዲሁም የሱዳንን ምዕራባዊ ክፍል ተቆጣጥሮ ቆይቷል።

የሱዳን ጦር

የፎቶው ባለመብት, Sudan TV

ለሱዳን የጦር ተፋላሚዎች ካርቱምን ማስመለስ ትልቅ ድል እንዲሁም በግጭቱ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

ጦሩ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በማዕከላዊ ሱዳን አንዳንድ ድሎች አስመዝግቧል።

ሐሙስ ዕለት በሪፐብሊካን መንግሥት አቅራቢያ የሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የአየር ጥቃቶች ፍንዳታዎች ማስከተላቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ መሀመድ ሃምዳን ደጋሎ ሄምቲ ቅዳሜ ዕለት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በሰራዊታቸው ቁጥጥር ስር የነበሩትን የፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት እና አካባቢውን ለመከከላከል ቃል ገብተው ነበር።

በተለያዩ የሰሜን ከተሞችም ተጨማሪ ጥቃቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

ተፋላሚ ኃይሎቹ ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ለመቆጣጠር በሚል በውጊያው እንቀጥላለን ማለታቸውን ተከትሎ በርካታ የሰላም ጥረቶች ፍሬ ሊያፈሩ አልቻሉም።

ጦርነቱ በዓለማችን ላይ ከፍተኛውን የሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን ጦሩም ይሁን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሰፋ ያሉ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ፈጽመዋል ተብለው ይከሰሳሉ።