ትራምፕ የፌደራሉን የትምህርት ዲፓርትመንት ለማፍረስ ትዕዛዝ ፈረሙ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፌደራሉ የትምህርት ዲፓርትመንት እንዲፈርስ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈረሙ።

የተወሰኑ የአሜሪካ ወግ አጥባቂዎች ለረጅም ጊዜ ሲያልሙት የነበረ ሲሆን፤ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ተቋሙን እንደሚያፈርሱት ቃል ገብተው ነበር።

የሪፐብሊካኑ ፕሬዚዳንት የትምህርት መምሪያውን "አስደንጋጭ ውድቀት" ያመጣ ሲሉ የከሰሱት ሲሆን ተቋሙ የሚቆጣጠረውን ገንዘብ ለግዛቶቹ ለመመለስ ቃል ገብተዋል።

ተቋሙን ለመዝጋት የአሜሪካ ምክር ቤት ይሁንታ እንደሚያስፈልግ ዋይት ሃውስ ቢያሳውቅም፤ ትራምፕ "በተቻለ ፍጥነት እንዘጋዋለን" ብለዋል።

ተቋሙ ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ የሰራተኞች ቅነሳ እንደሚያደርግ እንዲሁም ከአሁኑ ይዘጋል የሚለው እርምጃ ጋር ተያይዞ በርካታ ህጋዊ ተግዳሮች ገጥመውታል።

ሐሙስ ዕለት በዋይት ሐውስ በትምህርት ቤት ጠረጴዛ ላይ በተቀመጡ ህጻናት ተከበው የነበሩት ትራምፕ "አሜሪካ ከየትኛውም አገር በበለጠ ለትምህርት ብዙ ገንዘብ ታፈሳለች" ሆኖም ተማሪዎች በውጤታቸው ደረጃ ግርጌ ላይ እንደሚገኙ አክለዋል።

ዋይት ሃውስ በበኩሉ የትራምፕ አስተዳደር የተቋሙን የተወሰኑ ክፍሎችን በህግ ወሰኑ ውስጥ ለመዝጋት እንደሚንቀሳቀስ ገልጿል።

ይህ ውሳኔ እንደ በርካታዎቹ የፌደራሉን መንግሥት ተቋማት ለመቀነስ በሚል የአስፈጻሚ ትዕዛዝ ተፈርሞባቸው ህጋዊ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ የስራ አስፈጸሚ ትዕዛዙን በሚፈርሙበት ስነ ስርዓት ላይ ተቋሙን እንድትመራ የሾሟትን ሊንዳ ማክማሆንን አወድሰው፤ የተቋሙ የመጨረሻ ኃላፊ እንደምትሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በአስተዳደራቸው ውስጥ የምትሰራው "ሌላ ነገር" እፈልጋለሁ ብለዋል።

ትራምፕ ትዕዛዙን ከፈረሙ በኋላ የሊውዚያና የሪፐብሊካን ተወካይ ሴናተር ቢል ካሲዲ ተቋሙን ለመዝጋት ያቀደ ህግ ለማውጣት መታቀዱን አስታውቀዋል።

ነገር ግን ሪፐብሊካኖች በሴኔቱ ያላቸው ብልጫ እዚህ ግባ የማይባል፣ 53 ለ47 ሲሆን፤ የፌደራሉን ተቋም ለመዝጋት 60 ድምጽ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ይህንን በቀላሉ ለማሳካት እንደማይችሉ እየተነገረ ነው።

ሆኖም ዲፓርትመንቱ በመደበኛነት መዝጋት ባይቻልም የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ላይ እንዳደረገው ሁሉ የገንዘብ ምንጩን በማድረቅ እንዲሁም ሰራተኞቹን የማባረር ተግባራትን ሊፈጽሙ ይችላል። ይህ እርምጃ ኤጀንሲው በርካታ ፕሮግራሞቹን እንዲሁም የረድዔት ተግባራቱን እንዲያቆም አስገድደውታል።

ትራምፕ የፈረሙት የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ አስተዳደራቸው ምን አይነት እርምጃዎችን እንደሚወስድ እንዲሁም የትኞቹ ፕሮግራሞች ሊታጠፉ እንደሚችሉ ዝርዝር መረጃዎችን አላካተተም።

ኃላፊዋ ሊንዳ ማክማሆን የዲፓርትመንቱን መዘጋት ለማመቻቸት ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወስዱ እና ለግዛቶች እና ለከባቢ መንግሥታት ኃላፊነቱን እንዲሰጡ ያዛል።

እንዲሁም "አሜሪካውያን የሚተማመኑባቸው የአገልግሎቶች፣ ፕሮግራሞች ውጤታማ እና ባልተቋረጠ መልኩ እንዲሄዱ ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸውም መመሪያ ተቀምጦላቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 1979 የተመሰረተው የትምህርት ዲፓርትመንት የተማሪዎች ብድርን ከማስተዳደር በተጨማሪ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ተማሪዎችን የሚረዱ ፕሮግራሞችን ይመራል። ነገር ግን ትራምፕ ተቋሙ ዘርን፣ ጾታዊ እና ፖለቲካዊ አመለካከቶችን በታዳጊዎች ላይ ለማስረጽ እየሞከረ ነው ሲሉ ይከሱታል።