'በመጦሪያ ዘመኔ ባዶዬን ቀረሁ'፡ ለመልሶ ልማት ያለ ምትክ ቦታ እና ካሳ ቤታቸው የፈረሰባቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አቤቱታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በሚል መኖሪያ ቤቶች እና ተቋማት በጅምላ እየፈረሱ ነው።
በተለይም ለጫካ ፕሮጀክት፣ ለኮሪደር ልማት እና መልሶ ማልማት ለተሰኙ ወቅታዊ የመንግሥት ትኩረቶች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈርሰዋል፤ ነባር የመኖሪያ አካባቢዎች ፈርሰው በሌሎች ግንባታዎች ተተክተዋል ወይም በሂደት ላይ ናቸው።
በዚህ መካከል ቤታቸው ለፈረሰባቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች ካሳ እና ምትክ ቦታ የተሰጣቸው እንዳሉ ሁሉ፤ ያለምትክ ሜዳ ላይ ስለመውደቃቸው የሚናገሩትም በርካታ ናቸው።
ከእነዚህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13፣ ልዩ ስሙ ሰላም አምባ ሰፈር ነዋሪዎች ይገኙበታል። "ሰነድ አልባ" የተባሉት የቤት ባለንብረቶች ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል በአካባቢው እንደኖሩ ይናገራሉ።
በእነዚህ ዓመታት ቤተሰብ መሥርተው የተረጋጋ ኑሮ ሲመሩ እንደነበር በመጥቀስ፤ የአፈር ግብርን ጨምሮ ሌሎች የነዋሪነት ግዴታቸውን እና የልማት ሥራዎችን ሲደግፉ መቆየታቸውን ማስረጃ ያቀርባሉ።
በተለምዶ የጨረቃ ቤት ለሚባሉት ቤቶች መንግሥት ባለፉት ዓመታት የይዞታ ማረጋገጫ እንደሚሰጣቸው ቃል መግባቱን የሚገልፁት ከ450 በላይ የሆኑት ነዋሪዎች፤ ከአካባቢው የኮሪደር ልማት ከ200 እስከ 300 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ቤቶችን ጨምሮ "በመልሶ ልማት" እንደፈረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ቤት በማከራየትም ቤተሰብ ያስተዳድሩ እንደነበር ጠቁመው፤ እድራቸውን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎታቸው መበተናቸውንም ገልፀዋል።
"ጭካኔ የተሞላበት" ሲሉ ቤት አልባ ያደረጋቸውን እርምጃ የሚገልፁት ነዋሪዎች፤ ሕይወታቸው መመሰቃቀሉን እና ሜዳ ላይ መውደቃቸውን በመጥቀስ ባይተዋር ሆነናል ይላሉ።
ከእነዚህ ነዋሪዎች መሀል ሁለት ሰዎች ታሪካቸውን በአንደበታቸው እንዲህ ያጋራሉ። ፍትሕም ይጠይቃሉ።
"አገር አለኝ ብዬ . . ." ወርቅነሽ ዓለሙ*
የሦስት ልጆች እናት ነኝ።
ለተሻለ ኑሮ ወደ አረብ አገር ተሰደው ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን መካከል ነኝ። 11 ዓመት አረብ አገር ለፍቻለሁ። ይበቃኛል አገሬ ልግባ ብዬ ወስኜ ወደ አገሬ ተመለስኩ። ገንዘብ ስለነበረኝ የአንገት መግቢያ ቤት መግዛት ፈለኩ።
ለልጆችሽ ማሳደጊያ ይሆንሻል ብለው በ2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ገርጂ ሰላም አምባ ሰፈር ያለኝን ጥሪት አሟጥጬ ቤት ገዛሁ። ቤቱ ተጨማሪ ሦስት ክፍሎች ወይም ሰርቪስ አለው።
ስገዛው ካርታ እንደሌለው አውቂያለሁ። ነገር ግን "ይፀድቃል" አሉኝ እና እኔም አመንኳቸው። ከመንግሥት ቃል ተገብቶላቸው ለምን አላምናቸውም?
ሰርቪሱን በማከራየት የገቢ ምንጭ አግኝቼ ልጆቼን ማሳደግ ጀመርኩ። ቤት በማከራየት በወር ዘጠኝ ሺህ ብር ገቢ አገኛለሁ። ከዚህ በተጨማሪም በፅዳት ሥራ በማገኘው ገቢ የአምስት እና የሰባት ዓመት ልጆቼን አሳድጋለሁ።
ሕይወትን እንዲህ እያልኩ እየገፋሁ እያለሁ በዚህ ዓመት ሕይወቴን የገለባበጠ ሁኔታ ተከሰተ። አረብ አገር የለፋሁበት የላቤ ውጤት ቤቴ እንደሚፈርስ ጥቅምት 2017 ዓ.ም. መርዶ ተረዳሁ። ቅዳሜ 10 ሰዓት መጥተው፤ ሰኞ የሚያፈርስ ግብረ ኃይል እንደሚመጣ አረዱን።
"ነገውኑ ንብረታችሁን አንሱ" ተባልን። እኔን ጨምሮ አንዳንድ ሰዎች "አንወጣም" አልን። የት እንውደቅ? ብንል "ዶዘር ሊመጣ ነው፤ ሊፈርስ ነው" ተነሱ ተባልን። ቤትን ያህል ነገር እንደ ትንሽ ነገር ነቃቀልን። ቤተሰብ መጥቶ እቃዬን አውጥቶ የጭነት ክፍያ ከፍለው ይዘውልኝ ሄዱ። ይህ ሲሆን እኔ ከራሴ ጋር አልነበርኩም።
11 ዓመት አረብ አገር ለፍቼ የገዛሁት ቤት ፈረሰ። ከራሴ ጋር አልነበርኩም። ራሴን አላውቅም። ደም ግፊት እርጉዝ በነበርኩ ጊዜ ያመኝ ነበር። ይፈርሳል የሚለውን ዜና ከሰማሁ ቀን ጀምሮ ጤና አላደርኩም።
ህመሜ ተባባሰ። ያለሁበት ሁኔታም ከዕለት ዕለት መፍትሄ የማይገኝበት በመሆኑ ተስፋ ከሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ። አሁን የምኖረው ለእራሴ ሳይሆን ለህፃናት ልጆቼ ብዬ ነው።
ወደ አረብ አገር ተመልሼ ለመሄድ አስቤ ነበር። ነገር ግን ልጆቹን ለማን ትቼ? አቅሜም እንደ ዱሮው አይደለሁም። ዕድሜየም እየሄደ ነው። በጣም ተስፋ ያስቆርጣል። አገር አለኝ ብዬ ተመልሼ መጥቼ አጓጉል ሁኔታ ውስጥ ወደቅኩ።
ሰው አገሩ ሲገባ ተስፋ ይዞ ነው የሚገባው። 11 ዓመት ሙሉ በአረብ አገር፤ ሰው ቤት ስንት ውጣ ውረድ አልፌያለሁ። አረብ አገር ሕይወት ተሽጦ ነው የሚኖረው። እዚህ ስመጣ ያገኘሁትም ከዚህ የተለየ አይደለም። ምን ቀረኝ?
ጉዳዬን ቢሰሙ ብዬ ከቀበሌ እስከ ከንቲባ ቢሮ ተመላለስኩ። እኔን ማን ሰምቶኝ? የክፍለ ከተማውን ሥራ አስፈፃሚ አግኝቼ እባክዎት የት ልውደቅ? ብዬ ጠየኳቸው። 'ሴቶች ነን፤ ልጆች ይዘናል። ልጆቹ ይርባቸዋል፤ ጅብ ይወስድብናል' ብለን ለመናቸው። "ሕገ ወጥን አናበረታታም. . . ." ብለው አስወጡኝ። በጣም ነው ያዘንኩት።
ያልተመላለስኩበት ቀን የለም። እንደ እኔ ቤታቸው ከፈረሰባቸው ሰዎች ጋርም ሄደናል። ልጅ ይዘን ሜዳ ላይ ወድቀናል። ከዚህ የባሰ ጉዳይ ምን አለና ነው? አልናቸው። "አስር ጊዜ አትመላለሱ፤ ሥራ አታስፈቱን" ይላሉ።
አሁን አራተኛ ወሬን ይዣለሁ። ወዳጅ ዘመዶቼ አዋጥተው የስድስት ወር የቤት ኪራይ ከፍለው አስቀምጠውኛል። ለገበሬ ልጆች ተብሎ የተሠራ ኮንዶሚኒዬም አለ፤ እዚያ ይቀንሳል ተብሎ ስቱዲዮ ተከራይተውልኛል።
ዙሪያው ገደል ሆኖብኛል፤ ደሞዜ ሁለት ሺህ 79 ብር ነው። ከሥራዬ ቦታዬም እርቄያለሁ። ሥራ ለመድረስ ረጅም ርቀት እጓዛለሁ። ከትራንስፖርቱ የሚተርፈኝ ትንሽ ነው። ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የበዓል ቀናትን ያለ እረፍት ከሠራሁ ተጨማሪ ገንዘብ አገኛለሁ።
ልጆቼን ቤት ቆልፌባቸው ሥራ የምሄድበት ጊዜ አለ። እንዲያም ሆኖ ጭንቅ ነው። የሚቀምሱትን እንኳን መስጠት አልቻልኩም። ከየት አምጥቼ?
በትንሽ ነገር ብስጭት እላለሁ። በትንሽ ነገር ከሰው እጣላለሁ። ዙሪያው ጨልሞብኛል።. . . ግን ወዴት ይኬዳል? እንቅልፍ የለኝም።
ወርቅነሽ ብቻ አይደለችም ጥሪቷን አጠራቅማ መኖሪያ ቤት ይሆነኛል ብላ የገነባቻትን ቤት ፈርሶባት መግቢያ ያጣችው።
ሌላኛው የዕድሜ ባለጸጋ፣ የ85 ዓመቱ አቶ ዘላለም በሽምግልና ዘመናቸው ቤታቸው ፈርሶ መከራ ላይ መውደቃቸውን ይናገራሉ።
'በመጦሪያ ዘመኔ ባዶዬን ቀረሁ' አቶ ዘላለም* (የ85 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ)
በዕድሜዬ ያላየሁት ነገር የለም። ይህ ዘመን ግን የባሰበት ነው። በዚህ ዕድሜዬ ቤት ያስፈልገኛል፣ ምግብ ያስፈልገኛል፣ ልብስ ያስፈልገኛል. . . ግን ሁሉም የለም።
በሌላ አገር እንደምንሰማው መንግሥት ጡረተኞችን፤ ሽማግሌዎችን ይረዳል። እኔ ግን የሰራሁትንም ቤት አፍርሰው ባዶ እጄን ቁጭ ብያለሁ። የቀን ሥራ እና ዘበኝነት ሠርቼ ከ22 ዓመት በፊት ነበር አምስት ክፍል ቤት የሠራሁ። ልጆቼንም ያሳደኩት እዚህ ቤት ውስጥ ነው።
ስድስት ሺህ ብር ቤት እያከራሁ ገቢ አገኝ ነበር። ከ2011 ዓ.ም. ወዲህ በዋናነት በዚህ ገቢ ነበር የምትዳደረው።
በአካባቢዬ በመንግሥት የተጠየቅናቸውን መዋጮዎች ሁሉ አዋጥቻለሁ። ለአባይ ግድብ ገንዘብ ከፍያለሁ። አምቡላንስ ግዙ ተብለን አዋጥቻለሁ። አካባቢያችሁን ጠብቁ፤ የሰላም ሠራዊት ሰልጥኑ ሲሉ ሰልጥኜ አገልግያለሁ።
ኮንዶሚኒዬም ምዝገባ ሲጀመር የጨረቃ ቤት ያላችሁ አንዱን ምረጡ ሲሉን ተመዝግበን ተውነው። እኔ ኮንዶሚኒዬም ቤት ከምኖር በሠራሁት ቤት እስከ ፍፃሜዬ እኖራለሁ ብዬ ተውኩት።
ቤታችን እንደሚፈርስ ከሦስት ወረዳዎች ጋር ሰብሰበው "እኛ ሕገ ወጦች ነን ብላችሁ ፈርሙ" አሉ። እኛም አይሆንም አልናቸው። በድጋሚ ብንሰበሰብም አልተስማማንም። ሕዝቡ ተንጫጫ። ለምን ይፈርስብናል? እኛ ልማቱን አንቃወምም ከፈረሰም ለአንገታችን መግቢያ ምትክ ይሰጠን ስንላቸው ጥለውን ሄዱ።
አንድ ቀን መጥተው "ይፈርሳል፤ ተከራይ ይውጣ" አሉን። የእኔ ተከራዮች "እርስዎ ከወጡ ነው የምንወጣው፤ ጥለንዎት አንወጣም" አሉኝ። በግድ አስወጧቸው። እኔንም በሦስተኛው ቀን መጥተው አፍርስ አሉኝ። ኅዳር 30 ቆርቆሮውን እና በሩን ነቅዬ ወጣሁ።
158 ሰዎችን አባል ያደረገ ትልቅ እድር ነበረን፤ ሁሉም ሰው ተበተነ። ድንኳን ተሸጠ፤ ወንበር ተሸጠ፤ ብረት ድስት ተሸጠ። የሽያጩን ገንዘብ ተከፋፈልነው። አምስት ሺህ 500 ብር ደረሰኝ። እሷን እና የቆርቆሮውን ብር ይዤ ወጣሁ።
የዕድሜዬን ሲሶ የኖርኩበት ቤት ግድግዳ ብቻ ሆኖ ቀረ። እንጨቱንም ጥየው እቃዬን ጭኜ ቤቴን ወደ ኋላ እያየሁ ለቀቅኩ።
እዚያው የማውቀው ሰፈር ለመኖር ኪራይ ሰባት ሺህ እና ስምንት ሺህ ብር ነው። ውድ ሆነብኝ። ዓለም ባንክ የሚባል አካባቢ ኪራይ ይቀንሳል ተብሎ አራት ሺህ ብር ቤት ተከራይቻለሁ።
ምትክ ቦታ ወይም ካሳ እንዲሰጠን ያልሄድንበት የመንግሥት ተቋም የለም። ተመላለስን። መፍትሔ አጣን። ሜዳ ላይ ወድቀን ቀረን።
የመጨረሻው ልጄ 12ተኛ ክፍል ጨርሷል። ይህ ባይሆን ኖሮ ኮሌጅ እየከፈልኩ በደንብ አስተምረው ነበር። አሁን ሥራ ፍለጋ ሲዞር ይውላል። ምንም ማድረግ አልችልም።
ባለቤቴ በሽምግልና ዕድሜዋ ድንች ደጅ ላይ ትሸጣለች። ለሽምብራ ያህል አይጠፋም፤ እግዚአብሔር ይመስገን።
እኔም ቋጠሮ ባገኝ እሸከማለሁ እያልኩ ወደዚያ ወደዚህ ስል እውላለሁ። የሚያውቁኝ አንዳንዶች አስርም፣ ሃያም ብር ይሰጡኛል።
አሮጌ ሶፋ አለኝ። አሁን እሱን ልሸጠው ነው። ተቀምጦ ምን ያደርግልኛል? ሁለት ሺህ እንኳ ቢያወጣልኝ።
ምኑን አስቤ ምኑን እገፋዋለሁ? እኔም ባለቤቴም የደም ግፊት አለብን። መድኃኒት እንወስዳለን። ብበሳጭ የልጄን መጨረሻ ሳላይ አንድ ነገር እሆናለሁ ብዬ ትቼዋለሁ። እራሴን እንጂ ማንን እጎዳለሁ? ይህን ማየቴም አንድ ፀጋ ነው። እግዚአብሔርን ተመስገን እያልኩ እቆያለሁ።
ከኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ሁሉንም መንግሥታት አይቻለሁ። ክፉውንም ደጉንም አይቻለሁ። እንደዚህ ያለ መንግሥት አላየሁም።
ይህ ሁሉ ቤት ሲፈርስ፤ ይህ ሁሉ ሕዝብ ሲፈናቀል እሱ ከማን ጋር እንደሚኖር አላውቅም።
ሰውን ከቤቱ አስወጥቶ መድፋት? ይህ ሁሉ እምባ . . . እንደ ሥራው ይስጠው እንጂ እኔ ምን እላለሁ?
የሰው ልጅ ተከብሮ መኖር ሲገባው ሜዳ ላይ ውደቅ ማለት. . .። ባማርርስ ምን አመጣለሁ? ምንም የማመጣው ለውጥ የለም።
በልማት ምክንያት ለዘመናት የኖሩበት ቤት እና አካባቢ ፈርሶ ሜዳ ላይ ወድቀናል የሚሉት የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ነዋሪዎች መብታችን ነው የሚሉትን ጉዳይ እንዳይጠይቁ እስርን ጨምሮ ዛቻዎች እንደደረሱባቸውም ተናግረዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ "የሐሰት መረጃ በማሠራጨት" በሚል ከአንድ ወር በላይ የታሰሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ ፍርድ ቤት ነፃ ካላቸው በኋላ ከፋኖ ጋር ግንኙነት በማድረግ በሚል በድጋሚ ተከሰው በዋስ እንደተለቀቁ ገልፀዋል።
ቢቢሲ ነዋሪዎቹ የውሃ እና መብራት ክፍያዎችን ጨምሮ ለይዞታዎቻቸው የልማት መዋጮዎችን እና የተለያዩ ግብሮችን የከፈሉባቸውን ሰነዶች ተመልክቷል።
የቤተሰብ አባሎቻቸውን ቁጥር እና ሌሎች መረጃዎችን አባሪ ያደረጉ 455 የወረዳው ነዋሪዎች አቤቱታቸውን ለኢሕአፓ ፓርቲ ያቀረቡበትን ሰነድም የተመለከተ ሲሆን፤ በመደናገጥ እና በሌሎች ምክንያት ያልፈረሙ ነዋሪዎች በመኖራቸው ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል።
ቢቢሲ ስለጉዳዩ የቦሌ ክፍለ ከተማ ኮሪደር ልማት አስተባባሪ የሆኑትን የአዲስ አበባ ከተማ የሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነን እና የክፍለ ከተማውን ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራውን ለቀናት ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ተመሳሳይ እጣ የገጠማቸው በሁለት ወረዳ የሚኖሩ ተጨማሪ ሰዎች እንዳሉም ተነግሯል።
ከዚህ ባሻገርም "ለጫካ ፕሮጀክት" በሚል 800 የሚሆኑ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ስሙ ቁሊቲ የተባለ አካባቢ ነዋሪዎችም ከሁለት ዓመት በፊት ቤታቸው እንደፈረሰባቸው እና ካሳ እንዳልተሰጣቸው አቤቱታ አሰምተዋል።
በአዲስ አበባ በ2016 ዓ.ም. በተጀመረው እና ቢሊዮኖች ብር በተመደቡለት "የኮሪደር ልማት" ቅርሶችን ጨምሮ በተለይም በነባር ሰፈሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች እና ተቋማት ፈርሰዋል።
እስካሁን ምን ያህሎቹ ምትክ ቦታ ወይም መኖሪያ ቤት እንዲሁም ካሳ እንዳገኙ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአስተዳደራቸውን የ2017 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ለከተማው ምክር ቤት ሲያቀርቡ በስድስት ወራት ለፈረሱ ቤቶች 10 ቢሊዮን ብር ካሳ መክፈላቸውን ገልፀዋል።
*ባለታሪኮቹ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀይሯል።
ሕገ ወጥ የሚባለው ቤት የቱ ነው? የነዋሪዎች መብትስ ምን ድረስ ነው?
ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ያናገራቸው የሕግ ባለሙያው ታምራት ኪዳነማርያም እንደሚሉት በ1967 ዓ.ም. ሐምሌ 19 ከታወጀው አዋጅ በኋላ የከተማ ቦታ እና መሬት የመንግሥት ነው።
በዚህ ሕግ መሠረትም አንድ ቤት ሕገ ወጥ ነው የሚባለው ያለ መንግሥት ምሪት በዘፈቀደ በተያዘ መሬት ላይ የተሰራ ከሆነ ነው። ይህም በተለምዶ የጨረቃ ቤት ይባላል።
መንግሥትም እነዚህ ቤቶች ላይ ወዲያውኑ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው።
ነገር ግን መንግሥት እርምጃ ሳይወስድ ቆይቶ፣ ቤቱ በመንግሥት ተመዝግቦ ግብር ሲከፈልበት ከቆየ በከፊል ሕጋዊ፣ በከፊል ሕግ ያላሟላ (ድብልቅ) እንደሚባል የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ከዚያም መብራት እና ውሃ ሲገባለት፣ የስልክ መስመር ሲዘረጋለት እና ሕጋዊ በማድረግ ሒደት ውስጥ ካርታ ሲሰጠው ሕጋዊ ቤት ይሆናል።
ካርታው በመሠራት ላይ ያለ (ካዳስተር ቁጥር) የተሰጠው፣ ነገረ ግን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያልተሰጠው በከፊል ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ለመሆን ብዙ ነገር ያሟላ ቤት ይባላል።
ታዲያ መንግሥት የማፍረስ ሥልጣን ያለው የትኛውን ቤት ነው?
አቶ ታምራት እንደሚሉት መንግሥት ሕገ ወጥ ብሎ ማፍረስ የሚችለው ያለ መንግሥት ምሪት በዘፈቀደ በተያዙ መሬቶች ላይ የተሰሩ፣ ብዙም ያልቆዩ እና ሕጋዊ ሒደት ውስጥ ያልገቡ ቤቶችን ነው።
መንግሥት ዝም ብሎ ከቆየ በኋላ ድንገት ተነስቶ ቤቶቹን ማፍረስ እና ውጡ ማለት ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው አቶ ታምራት አስረድተዋል።
“ምንም ያላሟላ፣ ቀበሌም ያልመዘገበው፣ ካርታም የሌለው፣ የቤት ቁጥር ያልተሰጠው አዲስ ቤት ቢሆን እንኳ ለማፍረስ ሕጋዊ ሒደት አለው” ይላሉ ባለሙያው።
የመጀመሪያው ራሳቸው ባለቤቶቹ እንዲያፈርሱ ጊዜ መስጠት ነው።
በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ማፍረስ ካልቻሉ በመንግሥት ወጪ እንዲፈርስ ይደረጋል። ፍራሹም መንግሥት ጋር ይቀመጣል። ፍራሹ መንግሥት ጋር ቢቀመጥም ንብረትነቱ ግን የባለቤቶቹ ነው።
ስለዚህም ቤቱን ለማፍረስ የወጣውን የመንግሥትን የጉልበት ኪሳራ ከፍለው ንብረቱን አስለቅቀው መውሰድ ይችላሉ።












