ለነዋሪዎች ዶሮ በነፃ የሚያድሉት የአውሮፓ ከተማዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳይ እና የቤልጂየም ከተማዎች ላለፉት ዓመታት ዶሮ በነፃ ሲያድሉ ቆይተዋል። ይህ ባሕል በሌሎች የአውሮፓ ከተማዎችም ይስፋፋ ይሆን?
በአውሮፓውያኑ 2015 የፋሲካ በዓል ሰሞን ኮልማር የተሰኘችው የፈረንሳይ መንደር ለነዋሪዎች ዶሮ በነፃ ማደል ጀመረች።
በኮልማር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የሰሜን ፈረንሳይ አነስተኛ መንደሮች ዶሮ በነፃ ይታደላል።
ይህ የሚደረገው የምግብ ብክነት ለመከላከል ነው።
የወቅቱ የኮልማር ከንቲባ የነበሩት ጂልበርት ሜየር "አንድ ዶሮ ለአንድ ቤተሰብ" በተሰኘው የምርጫ ቅስቀሳቸው ይታወቃሉ። ይህን ያደረጉት የመንደርዋ ነዋሪዎች ዶሮ እንዲያረቡ ለማበረታታት ነበር።
ሥልጣን ሲጨብጡ ከሁለት የዶሮ አርቢ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለነዋሪው ዶሮ ማደል ያዙ። የመንደሩ ሰዎች ተሰልፈው ዶሮ መቀበል ጀመሩ።
ከ200 በላይ ቤቶች በነብስ ወከፍ ሁለት ዶሮ ይዘው ገቡ።
ታድያ ሁሉም ሰው ዶሮዎቹን ለመንከባከብ ቃል ገባ። የከተማዋ አስተዳደር ሠራተኞች ድንገት መጥተው የማጣራት ሥራ ይሠራሉ።
ዶሮ እንጂ የዶሮ ቤት አልተሰጣቸውም። ነዋሪው መግዛት አሊያም መገንባት ይጠበቅበታል።
ይህ የከንቲባው ዕቅድ ስኬታማ ሆነ። አሁንም እየተከናወነ ነው።
"ባለፉት ዓመታት ሌሎችም መንደሮች ይህንን ማድረግ ጀምረዋል። እዚህ አካባቢ ያሉ 20 መንደሮች ተሳታፊ ሆነዋል ይላሉ የአሁኑ የኮልማር ከንቲባ ኤሪክ ስትራውማን።
እስከ ዛሬ ለመንደሮቹ ነዋሪዎች 5282 ዶሮዎች ተከፋፍለዋል። የሚቀጥለው ዙር የዶሮ ዕድላ በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2025 ይጀምራል።
ነዋሪዎቹ ዶሮ እና እንቁላል ተትረፈረፈላቸው። አልፎም ቀድሞ ይጣል የነበረ ምግብ ለዶሮዎች በምግብነት ስለሚሰጥ ብክነት መቀነስ ያዘ።
"የአንድ ዶሮ አማካይ ዕድሜ አራት ዓመታት ነው። አንዲት ዶሮ ቢያንስ በቀን 150 ግራም ምግብ ትመገባለች። በዚህ መሠረት እስካሁን 273 ቶን ምግብ ከብክለት አድነናል" ይላሉ ኤሪክ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቆሻሻ ተብሎ የሚጣል ምግብ ከሌሎች ቆሻሻዎች የበለጠ ሜቴን የተባለ ኬሚካል ይለቃል። ይህ የሚሆነው ምግብ ቶሎ ስለሚበላሽ ነው።
በዩናይትድ ስቴትስ 58 በመቶ የሜቴን ልቀት የሚመነጨው ምግብ እና ሌሎች ነገሮች ከሚጣሉበት ከቆሻሻ መጣያዎች ነው።
ምንም እንኳ ከካርበንዳይኦክሳይድ ሲነፃፀር አየር የሚቆይበት ጊዜ አነስ ያለ ቢሆን ሜቴን ለሙቀት መጠን መጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል። ባለፉት 20 ዓመታት የሜቴን ልቀት ከካርበን ዳይኦክሳይድ 80 እጥፍ የበለጠ ተፅዕኖ ነበረው።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ዶሮ አርቢዎች ትራፊ ምግብ ለዶሮዎቻቸው እንዳይሰጡ ይመከራሉ። ይህ የሆነው በሽታ ያስተላልፋሉ በሚል ስጋት ነው። ነገር ግን በሌሎች ሀገራት ትራፊ ምግብ ለዶሮ መስጠት የተለመደ ነው።
ትራፊ ምግብ ለዶሮዎች መስጠት የምግብ ብክነትን ለመከላከል ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
ኮልማር ለነዋሪዎች ዶሮ በነፃ በማደል የመጀመሪያዋ ከተማ አይደለችም። በአውሮፓውያኑ 2012 ሰሜን-ምዕራብ ፈረንሳይ የምትገኘው ፒንች ከተማ ለነዋሪዎች በነብስ ወከፍ ሁለት ዶሮዎች ማደል ጀምራ ነበር።
በቤልጂየም እንዲሁ ሙስክሮን እና አንትዌርፕ በተባሉ ከተማዎች ነዋሪዎች በነፃ ዶሮ ይሰጣቸዋል። ነገር ግን ነዋሪዎች ለሁለት ዓመታት ያክል ዶሮዎቹን አርደው መብላት እንደማይችሉ በፊርማ ቃል ይገባሉ።
በአንድ ዓመት ብቻ ሊምቡርግ በተባለው መንደር ከ2500 በላይ ነዋሪዎች ዶሮ ተረክበው ማርባት ጀመሩ። ቀስ በቀስ በርካታ ነዋሪዎች ዶሮ በነፃ መቀበል ጀመሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶሮ በነፃ ማደል በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ መልካም ጅማሮ ነው። በተለይ ደግሞ እንቁላል ውድ በሆነባቸው አካባቢዎች ይህ ሐሳብ ብዙ ለውጥ አምጥተዋል።
ለምሳሌ በአሜሪካዎቹ ካሊፎርኒያ እና ኒው ዮርክ ግዛቶች አንድ ደርዘን እንቁላል 9 ዶላር አሊያም 1150 ብር ገደማ ነው የሚሸጠው።
አንዳንድ ዶሮዎች በዓመት እስከ 300 እንቁላሎች ይጥላሉ። ይህ ደግሞ በዓመት 225 ዶላር ማለት ነው።
በአሜሪካ በአሁኑ ወቅት የእንቁላል እጥረት አለ። ይህ የሆነው በሀገሪቱ በተከሰተው የወፍ በሽታ ምክንያት ነው። ከአውሮፓውያኑ 2023 አንፃር የእንቁላል ዋጋ 36 በመቶ ጨምሯል።
የዶሮ እና እንቁላል ጥቅም የገባቸው እንግሊዛዊያኑ ጥንዶች ኒው ሀምፕሸር በተባለው ሥፍራ ዶሮ ለስድስት ወራት ማከራየት ጀምረዋል። በርካቶች ዶሮ እየተከራዩ ንፁሕ እንቁላል መመገብ ይዘዋል።
የኮልማር ነዋሪዎች አሁን ዶሮና እንቁላል ተርፎ ሞልቷቸዋል። የሚባክን ምግብም የላቸውም።












