ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለቀጣይ አንድ ዓመት እንደሚቀጥል ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, PMOffice/X
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሁለት ዓመት የቆይታ ጊዜው የተጠናቀቀው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንደሚቀጥል ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሐሙስ መጋቢት 11/2017 በፓርላማ ተገኝተው ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጠው የሁለት ዓመት ጊዜ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የቆይታ ጊዜው የተጠናቀቀውን ጊዜያዊ አተስዳደር ለማስቀጠል አስፈላጊ የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል። በዚህ መልኩ የሚቀጥለው አስተዳደር እስከ ቀጣይ ምርጫ ድረስ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ይህንን ለማድረግ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው እና ምክትሎቻቸው ጄነራል ታደሰ ወረደ እና ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳይ ጋር ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።
ዐቢይ፤ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ መሰረት አስፈላጊው የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት ይቀጥላል ብለዋል።
በተደረገው ንግግር መሰረት ለሚቀጥለው አንድ ዓመት መጠነኛ የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ "ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይቀጥላል የሚል እምነት ነው ያለው በእኛ በኩል" ብለዋል
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተጨማሪ ውጊያ እንዳይቀሰቀስ በማድረግ ረገድ ለሰራው ስራ መመስገን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "የሰጠናቸው የሁለት ዓመት ጊዜ አብቅቷል። ተጨማሪ የሕግ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፤ የሕግ ማሻሻያው ተገምግሞ እና መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎ በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከ ሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ስራውን እየሰራ ሕዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀት እና ሕዝቡ የስልጣን ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ንግግራቸው "በግለሰቦች ረገድ ለውጥ ሊደረግ ይችላል" ያሉ ሲሆን በጠንካራ ጎናቸው ተወድሰው በደካማ ጎናቸው ተወቅሰው የሚቀያየሩ ሰዎች እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ ብዙዎች በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ሲሆን ዐቢይ ይህንን ፍርሃት አጣጥለዋል።
"የትግራይ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በትግራይ ጦርነት ይፈጠራል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።
ትግራይ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ያበቃው በ2015 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሁለቱ ዋና ዋና ተፋላሚ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሠላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ክልሉን እንዲመራ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም አስችሏል።
ነገር ግን ከቅርብ ወራት ወዲህ በህወሓት ውስጥ ባሉ ከፍተኛ አመራሮች እና በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር መካከል የስልጣን ሽኩቻ ተከስቷል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ አንዳንድ የህወሓት ሰዎች ስልጣን በኃይል ለመንጠቅ ሞክረዋል ሲል ይከስሳል።
ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛቸውን "ከውጭ ተዋናዮች" ጋር ይሰራሉ በሚል ይካሰሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, PMOffice/X
"በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ አንደኛዋ ስንዴ አምራች አገር ኢትዮጵያ ነች"
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛዋ ስንዴ አምራች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው የፓርላማ ቆይታቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስምንት ወራት የተገኘውን የኢኮኖሚ እቅድ አፈጻጸም በቀጣይ አራት ወራት አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ ከዕቅዱ በላይ ማሳካት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማብራሪያቸው ባለፉት ስምንት ወራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ 8.1 እድገት መስመዝገቧን ያስታወሱት ዐቢይ፤ በዚህ ዓመት እድገቱን 8.4 ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስምንት ወራት ያሉትን የኢኮኖሚ አፈጻጸሞች ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በእያንዳንዱ አመላካች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል" ብለዋል።
በቀጣይ የበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ይህንን ስኬት ማጠናከር ከተቻለ ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 4 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት ታስመዘግባለች ሲሉም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ቢያጋጥሙም ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ 8.1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባች ብለዋል።
በመኸር ወቅት እርሻ ብቻ 4.2 ሄክታር መሬት በስንዴ ተሸፍኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድምሩ በዚህ ዓመት ከ7.7 ሚሊየን ሄክታር ያላነሰ መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ከዚህም ከ300 ሚሊየን ኩንታል ያላነሰ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የውጪ ምንዛሬ ክምችት
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያላት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ባለፉት "100 ዓመታት ይዛ የማታውቀውን" ያህል እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት ከተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በተደረገ የዕዳ ሽግሽግ ድርድር "3.5 ቢሊዮን ዶላር" ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ፤ ከዚህ ቀደም በወሰደችው "ኮሜርሻል ብድር" ምክንያት "ሰፊ ዕዳ" እንደነበረባት አስታውሰዋል። ይህ ብድር የተወሰደው "ተጀምረው ለማይጨረሱ" ፕሮጀክቶች እና "ገንዘቡ በቅጡ ሀገር ውስጥ መግባቱ ባልታወቀበት ሁኔታ" እንደሆነ አስረድተዋል።
"ስንሟገት የነበርነው ጉዳይ ፍሬ አፍርቶ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሽግሽግ አግኝተናል። ይህም በዕዳ ጫናችን ላይ የሚያመጣው አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖራል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንዱ የአገሪቱ "ስብራት"፤ ያላት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ውስን መሆኑ እንደሆነ አንስተዋል። አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ ከስድስት ዓመታት በፊት በ2011 ዓ.ም. ከነበራት የውጭ ምንዛሬ "እጥፍ" ክምችት እንዳላት ገልጸዋል።
"[የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ ከ2011] እጥፍ ብቻ መሆኑ አይደለም፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባለፉት 100 ዓመታት ዛሬ ኢትዮጵያ ያላትን ክምችት ይዛ አታውቅም" ሲሉ ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። ይህ ክምችት "የማይጠበቁ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ለተወሰኑ ጊዜ ለውጭ ግብይት የሚያግዝ የውጭ ምንዛሬ" የሚያስገኝ መሆኑን ያነሱት ዐቢይ፤ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ "ትልቅ እምርታ እና እፎይታ" መሆኑን በመጥቀስ ውጤቱን አሞካሽተዋል።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱ "ዝርዝሩን ከሚመለከታቸው [አካላት] ጋር እንዲነጋገር" በመጠቆም፤ ኢትዮጵያ አሁን ያላት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ምን ያህል ጊዜ የሚያቆያት እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።

የፎቶው ባለመብት, PMOffice/X
"በሚቀጥሉት ስድስት ወራት [የህዳሴ ግድብን] ሪቫን እንቆርጣለን"
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ "በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ" እንደሚመረቅ ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ በምክር ቤት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች አንዱ የህዳሴ ግድብን የተመለከተው ይገኝበታል። መሀመድ አህመድ የተባሉ የምክር ቤት አባል የህዳሴ ግድብ "ትውልድ ተሻጋሪ" እና "ብሔራዊ መግባባትን ሚያጠናክር" ፕሮጀክት እንደሆነ ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባሉ፤ "የህዳሴ ግድብ ግንባታን ሙሉ በሙሉ አጠናቀን፣ ሪቫን ለመቁረጥ ምን ያህል ርቀት ይቀረናል" ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ "ብዙ ዋጋ የተከፈለበት" እና "አንድ ብር እርዳታም ሆነ ብድር ከውጪ ያልተገኘበት" እንደሆነ ተናግረዋል።
ዐቢይ፤ "ለህዳሴ ግድብ የሚውሉ ግብዕቶች ከሁለት ወር ተኩል ያላነሰ [ጊዜ] ከጅቡቲ እስከ ህዳሴ አጅበን እየወሰድን ነው ሰራነው" ሲሉ ለግድቡ ግንባታ የሚውሉ እቃዎችን ማድረስ "በጣም አስቸጋሪ" እንደነበር አስረድተዋል።
ዐቢይ፤ "ቢበዛ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በጋራ ሪቫን እንቆርጣለን" በማለት "ብዙ መከራ" የታየበት ሲሉ የገለጹት የህዳሴ ግድብ መቼ እንደሚመረቅ አስታውቀዋል።
መንግሥት ግድቡን ለማስመረቅ ስድስት ወራት የሚወስደው ምርቃቱ "ዝግጅት ስለሚፈልግ እና አካባቢው ሞቃታማ ስለሆነ የክረምቱ ዝናብ ስለሚፈለግ ብቻ" እንደሆነ ገልጸዋል።
"ህዳሴ በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ታሪክ ይሆናል ማለት ነው። ታሪክ ሆኖ የሚያልፍ ይሆናል" ሲሉ ለምክር ቤት አባላቱ ተናግረዋል።












