የዩኬው ግዙፉ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመብራት መቋረጥ ምክንያት ተዘጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደሙ ግዙፉ ሂትሮው አለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቅራቢያው በሚገኝ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ እሳት መቀስቀሱን ተከትሎ በተከሰተው መብራት መቋረጥ ዛሬ አርብ፣ መጋቢት 9/ 2017 ዓ.ም ሙሉ ቀን ተዘግቶ ይውላል ተባለ።
የእሳት አደጋ የደረሰበት ማከፋፈያ ጣቢያ ለአየር ማረፊያው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ እንደሆነ ተገልጿል።
በአገሪቷ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ስራ የሚበዛበት አየር ማረፊያ በሚቀጥሉት ቀናት "ከፍተኛ መስተጓጓል" እንደሚኖር አስጠንቅቆ እንደገና እስኪከፈት ድረስ ተሳፋሪዎች "በምንም ዓይነት ሁኔታ" እንዳይጓዙ መመሪያ አስተላልፏል።
"የተሳፋሪዎቻችንና እና የስራ ባልደረቦቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ አርብ ሙሉ ቀኑን ከመዝጋት ውጪ ምንም አማራጭ የለንም" ሲሉ የአየር ማረፊያው ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
"የእሳት አደጋ ሰራተኞች ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በአስተማማኝ ሁኔታ መቼ እንደሚመለስ ግልጽ አይደለም" ሲሉ አክለዋል።
አየር ማረፊያው ለተፈጠረው መስተጓጓል ይቅርታ ጠይቆ መንገደኞች የበለጠ መረጃ ለማግኘት አየር መንገዶቻቸውን እንዲያነጋግሩ ምክር አስተላልፏል።
ሂትሮው የዩኬው ትልቁ የአየር ማረፊያ ሲሆን በቀን ውስጥ ማረፊያ እና መነሻቸውን ያደረጉ 1 ሺህ 300 አውሮፕላኖችን ያስተናግዳል።
ባለፈው ዓመት ክብረ ወሰን በሚባል ሁኔታ 83.9 ሚሊዮን መንገደኞች ማስተናገዱን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
የአየር ማረፊያው አርብ ዕለት ተዘግቶ በመዋሉ ቢያንስ 1 ሺህ 351 በረራዎች እንደሚስተጓጎሉ የበረራ መከታተያ ድረ ገጽ ፍላይት ራዳር 24 በኤክስ ገጹ አስፍሯል።
120 የሚሆኑ አውሮፕላኖች ማለዳ ላይ ለማረፍ እየተጠባበቁ እንደነበር ድረገጹ አክሎ ገልጿል።
በምዕራብ ለንደን ሃይስ የሚገኘው ማከፋፈያ ጣቢያ የተቀሰቀው የእሳት ቃጠሎ በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን መብራት አልባ አድርጓል።
በተጨማሪም 150 ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ ተደርገዋል።
የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት በስፍራው የተጠራው በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ሐሙስ ከሌሊቱ አምስት ተኩል ገደማ ሲሆን ከጣቢያው ከፍተኛ የእሳት ነበልባል ሲቀጣጠል እንዲሁም ጭስ ሲወጣ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተጋሩ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።
የእሳቱ መንስዔ እስካሁን አልታወቀም።
የለንደን ፋየር ብርጌድ እንዳስታወቀው የማከፋፈያ ጣቢያው ግማሹ ትራንስፎርመር ሌሊት አስር ሰዓት ላይ በእሳት እየነደደ ነበር ብሏል።
የእሳት አደጋውን ለመከላከል 70 የእሳት አደጋ ተከላካዮች እንዲሁም አስር መከላከያ ሞተሮች ወደ ስፍራው መላካቸውን ብርጌዱ አስታውቋል።
እሳቱ ባስከተለው የመብራት መቋረጥ ምክንያት ከ16 ሺህ 300 በላይ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ማጣታቸውን የስኮትላንድ እና የደቡባዊ ቀጠና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ድርጅት በኤክስ ገጹ አስታውቋል።












