ለ123 ቀናት የረሃብ አድማ ያደረጉት ህንዳዊው አርሶ አደር

ለ123 ቀናት የረሃብ አድማ የመቱት ህንዳዊው አርሶ አደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ70 አመቱ ህንዳዊ አርሶ አደር ለ123 ቀናት ምግብ በአፋቸው ሳይዞር የረሃብ አድማ አድርገዋል።

የዕድሜ ባለጸጋው ጃግጂት ሲንግ ዳሌዋል የፌደራል መንግሥት በተቃውሞ ላይ ያሉ አርሶ አደሮችን ጥያቄ እንዲመልስ ጫና ለማድረግ ነው የረሃብ አድማ ያደረጉት።

በቅርቡም በተቃውሞ ላይ ያሉ አርሶ አደሮች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ አርሶ አደሩ ውሃም ቢሆን ለመቅመስ አሻፈረኝ ብለው ስምንት ቀናትን አስቆጥረዋል።

በዚህም ወቅት በሆስፒታል የነበሩ ሲሆን አርሶ አደሮቹ መፈታታቸውን ተከትሎ ውሃ መቅመሳቸው ተገልጿል።

ዳሌዋል በመጨረሻም ውሃ ለመጠጣት እሺ ማለታቸውን የፑንጃብ ግዛት አስተዳደር ጉዳያቸውን እያየ ላለው የህንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሳውቋል።

በታህሳስ ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አርሶ አደሩ ጤንነታቸው እያሸቆለቆለ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የሚኖሩበት የፑንጃብ ግዛት አስተዳደር ወደ ሆስፒታል እንዲያዛውራቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

አርሶ አደሮቹ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ከባለፈው ዓመት የካቲት ጀምሮ በጎዳናዎች ላይ ጊዜያዊ መጠለያዎችን ሰርተው እንዲሁም ትራክተሮቻቸውን አቁመዋል።

ፖሊስም ይህንን ስፍራ በቅርብ ጊዜ ማጽዳቱ ተገልጿል።

የአርሶ አደሩ የረሃብ አድማ ባለፈው ዓመት የካቲት በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በፑንጃብ እና በሃሪያ ግዛቶች ድንበር ላይ በመሰባሰብ የተጀመረው የተቃውሞ አካል ነው።

አርሶ አደሮቹ እያቀረቡት ያሉት ጥያቄዎች በተወሰኑ ሰብሎች ላይ የተረጋገጠ የዋጋ ተመን፣ የብድር ስረዛ እና ቀደም ባሉ ተቃውሞዎች ህይወታቸው ላለፉ አርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፈል የሚሉ ናቸው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ወደ ዋና መዲናዋ ደልሂ ለማቅናት አንዳንድ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በኬላዎች ላይ ባሉ የጸጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴያቸው ተገትቷል።

የህንድ አርሶ አደሮች ተቃውሟቸውን ወደ አደባባይ ሲወስዱት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከአምስት ዓመታት በፊት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የሕንድን መዲና ዴልሂ መግቢያና መውጫዋን ተቆጣጥረውት ነበር።

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ያጸደቋቸው ሶስት የእርሻ ህጎች ከጥቅማቸው ጋር የሚጻረር እንደሆነ የገለጹት አርሶ አደሮች ህንድን በተቃውሞ ማንቀጥቀጣቸው የሚታወስ ነው።

መንግሥት ህጎቹ የግብርና ምርትን ሽያጭ በማሻሻል የአርሶ አደሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ያደርጋል ብሎ ቢከራከርም አርሶ አደሮቹ ግን ለብዝበዛ የሚዳርግ ነው በማለት እንዲሰረዙ ጠይቀዋል።

ተቃውሞቹ መበርታታቸውን ተከትሎ በመጨረሻ ቢሰረዙም በዚያን ወቅት አርሶ አደሮቹ ያቀረቧቸው ሌሎች ጥያቄዎች እስካሁን አለመመለሳቸውን ይናገራሉ።

ለ123 ቀናት የረሃብ አድማ የመቱት ህንዳዊው አርሶ አደር

የፎቶው ባለመብት, SM

የረሃብ አድማ የመቱት ጃግጂት ሲንግ ዳሌዋል ማን ናቸው?

ዳሌዋል የፑንጃብ ግዛት ተወላጅና ነዋሪ ናቸው።

ግዛቲቷ በዋነኝነት በግብር ስራ የምትተተዳደር ብትሆንም በቅርብ ጊዜ በእርሻ ላይ ያለው ገቢ እያሽቆለቆለ በመሄዱ አርሶ አደሮች ለዕዳ፣ ስደት ሲዳረጉ ይባስ ብሎም ራሳቸውን እያጠፉ ነው።

ዳሌዋል ሳምዩክታ ኪሳን ሞርቻ የተባለ የአርሶ አደሮች ማህበራት ጥምረት መሪ ናቸው።

አርሶ አደሩ ቀደም ሲል በፑንጃብ የመንግሥት የመሬት ይዞታን በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍን መርተዋል። እንዲሁም ራሳቸውን በማጥፋት ህይወታቸው ላለፈ አርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፈላቸው መንግሥትን ተጋትረዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 በርካታ ትራክተሮች ወደ ደልሂ ያቀኑበትን ሌላ ተቃውሞ እንዲሁ በመምራት ይታወቃሉ። በዚህ ወቅት በ2004 የመንግሥት ኮሚቴ ለአርሶ አደሮች ምርት የሚከፈለው ዋጋ አመርቂ እንዲሆን እንዲሁም እዳቸው እንዲሰረዝ ያቀረበው ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን ለመጠየቅ ነበር።

ዳሌዋል የረሃብ አድማ ከመጀመራቸው በፊት ህዳር ወር ላይ በግዛቲቷ ፖሊስ ለምርመራ በሚል ወደ ሆስፒታል ተወስደው ነበር። ነገር ግን በሆስፒታል ውስጥ እስር ላይ ነበርኩኝ ያሉት አርሶ አደሩ በቀናት ውስጥ ተቃውሞ ወደሚካሄድበት ስፍራ ተመልሰዋል።

አርሶ አደሩ የፕሮስቴት ካንሰርን ጨምሮ ከባድ የጤና ችግሮች እንዳለባቸው የህንድ ሚዲያዎች ዘግበዋል። በ101ኛ ቀናቸው እግራቸው እብጠት እንዳጋጠመው፣ ውሃ መጠጣት እንደቀነሱ የተነገረ ሲሆን ዶክተሮችም ሁኔታቸውን እየተከታተሉ ነበር ተብሏል።

እስከ ሞት ድረስ መጾም በሚል የረሃብ አድማ ላይ የነበሩት አርሶ አደር 17 ሄክታር መሬታቸውን ለልጆቻቸው እና ለቤተሰቦቻቸው ለማካፈል ኑዛዜ መፈጸማቸው ተገልጿል።

የህንድ አርሶ አደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሁኑ ተቃውሞ ከቀድሞዎቹ በምን ይለያል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአርሶ አደሮቹ ጥያቄዎች አንጻር ቀደም ሲል ከነበሩ ተቃውሞዎች ብዙም የተለየ ነገር የለም።

አርሶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም ያነሷቸው ጥያቄዎች እንዲመለሱ ነው መንግሥትን እየጠየቁ ያሉት። ይመለስልን ካሏቸው ጥያቄዎች መካከል የዕዳ ስረዛ፣ ለአርሶ አደሮች እና ለግብርና ሰራተኞች የጡረታ አበል፣ የመብራት ታሪፍ እንዳይጨምር፣ የመሬት ይዞታ ህግ ወደ ቀደመው እንዲመለስ እና ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ተቃውሞዎች ለሞቱ አርሶ አደር ቤተሰቦች ካሳ ይከፈል የሚሉ ናቸው።

ነገር ግን ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ የሞዲ መንግሥት ለዚህኛው ዙር ተቃውሞ እየሰጠ ያለው ምላሽ ከቀደምቶቹ በተለየ መንገድ መሆኑን ነው።

ከአምስት አመታት በፊት በነበረው ተቃውሞ የፌደራል መንግሥቱ ከአርሶ አደሮቹ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርጓል። የህንድ የግብርና እና የምግብ ሚኒስትርን ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የድርድሩ አካል ነበሩ።

ባለፈው የካቲት አርሶ አደሮቹ ወደ ደልሂ ለማቅናት ማቀዳቸውን በገለጹበት ወቅት ቁልፍ የፌደራል ሚኒስትሮች ከመሪዎቹ ጋር ሁለት ዙር ውይይት ቢያካሂዱም ለውጥ ሊመጣ አልቻለም።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፌደራል መንግሥቱ ከተቃውሞው ራሱን ያገለለ ይመስላል። የግብርና ሚኒስትሩ ሺቭራጅ ሲንግ ቾውሃን አርሶ አደሮቹን ለውይይት ይጋብዟቸው እንደሆነ ባለፈው ሳምንት በጋዜጠኞች ተጠይቀው ነበር።

ሚኒስትሩም በምላሹ መንግሥት በከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ማንኛውንም መመሪያ እንደሚከተል ተናግረዋል።

መንግሥት በባለፈው ተቃውሞ የነበሩ ሁነቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ እያደረገ እንደሆነ ባለሙያዎች ያምናሉ።

በዚያን ወቅት በአገሪቱ የግብር ጸሐፊ እና በአርሶ አደሮች ማህበራት መካከል የተካሄደ ውይይት መክሸፉን ተከትሎ ለአንድ ዓመት የዘለቀ ተቃውሞ መነሻ ሆኗል።

የህንድ አርሶ አደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቀጣዩ ምን ይሆናል?

በዘንድሮው ዓመት መስከረም ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአርሶ አደሮቹን ጥያቄ የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ ሰጥቷል።

ኮሚቴው በህዳር ወር ላይ ባቀረበው የመጀመሪያ ሪፖርት የህንድ አርሶ አደሮች እያጋጠማቸው ያለውን የከፋ ቀውስ አካቷል።

ሪፖርቱ በዋነኝነት ከጠቀሳቸው መካከል አርሶ አደሮቹ የሚያገኙት ክፍያ በጣም ዝቅተኛ መሆን በተቃራኒው የተጫናቸው ዕዳ ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።

የህንድ ብሔራዊ የወንጀል መዝገብ ቢሮ መረጃ መሰብሰብ ከጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 1995 ጀምሮ ከ400 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች እና የግብርና ሰራተኞች ራሳቸውን ማጥፋታቸውም በዚህ ሪፖርት ተካቷል።

ኮሚቴው ለአርሶ አደሮቹ ቀጥተኛ የገቢ ድጋፍ ማድረግ ጨምሮ ሌሎች መፍትሄዎችን አስቀምጧል።