በኢትዮጵያ ተቃውሞ የገጠመው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ቡድን የሥራ ጊዜው ተራዘመ

የኢትዮጵያ መንግሥት ገለልተኛ አይደለም በማለት የተቃወመው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን የሥራ ጊዜ ለአንድ ዓመት ተራዘመ።
አርብ መስከረም 27/2015 ዓ.ም. ጄኔቫ ውስጥ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክር ቤት አባላት ውሳኔውን በተመለከተ በሰጡት ድምጽ ነው መርማሪ ቡድኑ ሥራውን እንዲቀጥል የተወሰነው።
ኢትዮጵያ መርማሪ ኮሚሽኑ ሲመሰረት ጀምሮ ተቃውሞዋን ስታሰማ የቆየች ሲሆን፣ ሦስት አባላት ያሉት ቡድን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ያደረገውን ምርመራ የመጀመሪያ ሪፖርት ካቀረበ በኋላም የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞውን አሰምቷል።
የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽኑ ሥራውን እንዲቀጥል የተጠየቀበት የውሳኔ ሐሳብ የቀረበው የአፍሪካ ኅብረትን በመወከል በቼክ ሪፐብሊክ በኩል ሲሆን በተሰጠው ድምጽ በጠባብ ልዩነት ተቀባይነት አግኝቷል።
አርባ ሰባት አባላት ካሉት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት መካከል የመርማሪ ቡድኑን ሥራ መቀጠል 21ዱ ሲደግፉት 19ኙ ተቃውመውታል። የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ውሳኔውን ተቃውመውታል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ይህንኑ አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት “ፖለቲካዊ ሚና ያለው “የባለሙያዎች” ኮሚሽን ሥራውን እንዲቀጥል አንድም የአፍሪካ አገር ድጋፉን አልሰጠም” በማለት ቡድኑን ተችተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ምርመራ እንዲያደርግ ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የባለሙያዎቹ ቡድን፣ ቀደም ሲል በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አማካይነት ከተደረገው ምርመራ ጋር የሚቃረን እና ተደራራቢ ነው በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ሲቃወመው ቆይቷል።
ቡድኑ መስከረም 10/2015 ዓ.ም ባወጣው የመጀመሪያ የምርመራ ሪፖርቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎችን ማግኘቱን አስታውቋል።
ሦስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚሽን የመብት ጥሰቶቹ “የጦር ወንጀል” እና “በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች” ናቸው ሊባሉ የሚያስችሉ ስለመሆናቸው አሳማኝ ምክንያቶች ማግኘቱን በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።
የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን ያመለከተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን የሚያመለክቱ አሳማኝ መረጃዎች ማግኘቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን “ያልተሟላ፣ ተያያዥነት የሌለው እና በመረጃ ያልተደገፈ” በማለት አገሪቱን በመጥፎ መልኩ ለማቅረብ የታለመ ነው ሲል ሪፖርቱን እንደማይቀበለው አስታውቋል።
ጨምሮም ሪፖርቱ “በጥድፊያ የተዘጋጀ፣ ከደረጃው የወረደ” መሆኑን በመግለጽ የተሰማውን ቅሬታ ያመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ጨምሮም አጣሪ ኮሚሽኑ አጀንዳውን ለማሳካት በመረጠው መንገድ ሥራውን አከናውኗል ሲል ወቅሷል።
በቀረበው ሪፖርት ላይ ጠንካራ ትችት የሰነዘረው የኢትዮጵያ መንግሥት የምርመራው ውጤት “በምርመራ ሪፖርት ስም ፖለቲካዊ መግለጫ ነው” ብሎታል።
በመጪው ጥቅምት ወር ሁለት ዓመት የሚሞላው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ግድያዎች በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በሁሉም ወገኖች መፈጸሙን በተለያዩ የመብት ተቆርቋሪዎች ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ይህንንም በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምርመራ አድርገው ባለፈው ዓመት ሰፊ ሪፖርት አውጥተዋል።
የሥራ ጊዜው በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት እንዲራዘም የተወሰነለት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ የባለሙያዎች ቡድን እስከ ታኅሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ይቆያል።












