የትራምፕ ቤት እንዲበረበር ያዘዙት ዳኛ ዝርዝር መረጃዎች ይፋ እንዲሆኑ አዘዙ

የቀድሞው ፕሬዘዳንት የደበቅሁት መራጃ የለም ሲሉ የቀረበባቸውን ውንጀላ አስተባብለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መኖሪያ ቤት እንዲፈተሽ ትዕዛዝ የሰጡት ዳኛ ብርበራውን እንዲያጸድቁ ያደረጓቸው ሰነዶች ይፋ እንዲሆኑ አዘዙ።

በዐቃብያነ-ሕግ የተሰበሰቡትን ማስረጃዎች ብሎም ለችሎቹ ያቀረቡት ቃለ መሃላ ሰነድ ቅጂ ይፋ የሚሆን ከሆነ ስለምርመራው ተጨማሪ መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴርም መረጃው ይፋ የሚወጣ ከሆነ በሂደት ላይ ያለውን ምርመራ ይጎዳል ሲል ወቅሷል።

የብርበራ ማዘዣው እንደሚገልጸው ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ግዜያቸው ካበቃ በኋላ ከኋይት ሀውስ ወደ ቤታቸው የመንግሥትን መዛግብት አላግባብ ወስደዋል በሚል ወንጀል በመጠርጠራቸው ነው ኤፍቢአይ ምርመራውን የጀመረው።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ከሥልጣናቸው ሲለቁ ሰነዶችን እና ኢሜሎችን ወደ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት የማስተላለፍ ግዴታ አለባቸው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቀረበባቸውን ውንጀላ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን መርማሪዎች በፍሎሪዳ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ አግኝተነዋል ያሏቸውን ሚስጥራዊ ሰነዶች እርሳቸው ቀድመው ያሳወቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ጉዳዩ ላይ የተሰየሙት ዳኛ ብሩስ ራይንሃርት ትላንት በሰጡት ትዕዛዝ ዛሬ ዓርብ ከምሽትቱ አንድ ሰዓት ላይ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘው የቃለመሃላ ሰነዱ እንዲለቅ አዘዋል።

ዳኛው ዐቃቤ ሕግ የምስክሮችን፣ የሕግ አስከባሪ አካላትን፣ ያልተከሰሱ አካላትን ማንነትእ ንዲሁም የምርመራውን ስልት፣ አቅጣጫ፣ ወሰን፣ ምንጭ እና ዘዴ የሚገልጹ የሰነዱን ክፍሎች ይፋ እንዳይሆኑ አሳማኝ ምክንያት በማቅረቡ እነዚህ ዝርዝሮች ይፋ በሚሆነው ሰነድ ውስጥ እንደማይካተቱ ተናግረዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት የቅጣት ውሳኔዎችን የያዘ የቃለ መሃላ ቅጂ ለችሎቱ ማስገባቱን አስታውቋል።

የተሻሻለው ሰነድ ትራምፕ ምስጢራዊ ሰነዶችን በፕሬዝዳንትነታቸው የመጨረሻ ቀናት ለምን እንደወሰዱ እና በፓልም ቢች ውስጥ ተከማችተው በነበሩበት ጊዜ ምን እንደፈጸሙ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል ተበሎ ይጠበቃል።

የተለያዩ የዜና አውታሮች ጉዳዩ ላይ የሕዝብ ጥቅም ስላለው ብሎም የፍተሻውን ታሪካዊነት ከግምት ውስጥ በመክተት ሰነዱን ለሕዝብ ለማውጣት ችሎቱን ጠይቀዋል።

የፍትህ መሥሪያ ቤቱ በበኩሉ ይህ የሚሆን ከሆነ በሂደት ላይ ያለውን ምርመራ ሊጠገን የማይችል ጉዳት ሊያደርስበት ይችላል ሲል እርምጃውን ተቃውሟል።

ከውስጡ የሚወጡት መረጃዎች ሲቀነሱም ሰነዱን “ትርጉም የለሽ” ያደርጉታል ብሏል።

ትራምፕ እና ጠበቃቸው ፍተሻው ፖለቲካዊ ይዘት ያለው እና ሕገ ወጥ ነው ያሉ ሲሆን ምንም መረጃ ያልተቀነሰበት ሰነድ እንዲለቀቅ ጠይቀዋል።

የትራምፕ ቃል አቀባይ ቴይለር ቡዶዊች ይዘቱን "ለመደበቅ" የሚደረገው ጥረት "አስቂኝ" እና "የመንግሥት ሙስናን ለመደበቅ ያለመ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዶናልድ ትራምፕ የጠበቆች ቡድን ምርመራው እንዲታገድ ብሎም ገለልተኛ የሦስተኛ ወገን ጠበቃ እንዲመጣላቸው እና ኤፍቢአይ በፍተሻው ወቅት የወሰዳቸውን ሰነዶች እንዲከታተል ጠይቋል።